በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የአፋር ክልል ጤና ተቋማት
ማክሰኞ፣ ጥር 3 2014ኢትዮጵያ ውስጥ የጦርነትን አውዳሚነት በግላጭ መመለከት ተጀምሯል። በተለይ ገና ብዙ እንደሚቀረው አዘውትሮ በሚነገርለት የጤናው ዘርፍ ላይ የደረሰው ጉዳት ኅብረተሰቡ በያለበት መሠረታዊ የሚባሉ የጤና አገልግሎትን እንኳን እንዳያገኝ እንዳደረገው ሁኔታውን በቅርበት የሚመለከቱት ይገልጻሉ። ከዓመት የዘለለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተስፋፍቶ ከጎዳቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው አፋር ክልል የጤና ተቋማት የደረሰባቸውን ጉዳት የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ ለዶቼ ቬለ አብራርተዋል። የጤና ሚኒስቴር በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን በአፋር እና በአማራ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት ዳግም አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በነደፈው መርሃግብር የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉላቸው መሆኑ እየተነገረ ነው። በአፋር ክልልም ባለው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የተጎዱት የጤና ተቋማት ዳግም ወደ ሥራ እንዲመለሱ እርብርብ እየተደረገ መሆኑን የጤና ቢሮው ኃላፊ አቶ ያሲን ይናገራሉ።
አቶ ገአዝ አህመድ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝደንት ናቸው። ቤልጂየም የሚኖሩት አቶ ገአዝ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ እና በአፋርም ሆነ በአማራ ክልል ተዘዋውረው በጦርነቱ የተጎዱ ቦታቸውን መመልከታቸውን ገልጸውልናል። የመድኃኒትም ሆነ የአንዳንድ የህክምና አገልግሎት መሣሪያዎች እርዳታን በሚመለከት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አፋር ክልል ሲመጡ መመልከታቸውን አቶ ገአዝ የገለጹልን ቢሆንም፤ ግን ብዙ ይቀራል ባይ ናቸው። የአፋር ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ በበኩላቸው ቃል የገቡ ወገኖች የጤና ተቋማቱን መልሶ የማቋቋሙን ሥራ ፈጠን ብለው እንዲያከናውኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ