በጦርነትና ረሃብ መካከል የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በኻርቱም
ዓርብ፣ ግንቦት 4 2015
አራት ሳምንት የሆነዉ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነትን ሸሽተዉ ሃገሪቱን እየለቀቁ የሚወጡ የዉጭ ሃገር ዜጎች እና ሱዳናዉያን ቁጥር እየጨመረ ነዉ። በሱዳን መዲና ኻርቱም የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ከጦርነቱ በላይ ረሃብ እየገደለን ነዉ ከኻርቱም የምንወጣበትን መንገድ ኢትዮፕያዉያን ያስተባብሩልን ሲሉ እየተማፀኑ ናቸዉ። በጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሚመራው በሱዳን ጦርና በጀኔራል ሞሀመድ ሐምዳ ዳጋሎ (ሔምዲቲ) በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ጦር መካከል ሱዳን ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት አራተኛ ሳምንቱን ቢይዝም ሁለቱ ተቀናቃን ወገኖች ለሰብአዊ ርዳታ መንገድ ለመክፈት ተስማሙ እንጂ ዛሬም ጦርነቱን እንደቀጠሉ ነዉ ፡፡ አዜብ ታደሰ በሱዳን የሚገኙ ጥቂት ኢትዮጵያዉያን አነጋግራ ተከታዩን ዘገባ አሰናድታለች።
የእርስ በእርስ ዉግያ ከጀመሩ አራት ሳምንት የሆናቸዉ ሁለቱ ተቀናቃኝ የሱዳን ጄኔራሎች ለሰላማዊ ሰዎች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ቢስማሙም ተኩስ አቁም ላይ ግን እስካሁን መድረስ አልቻሉም። መዲና ካርቱን ጨምሮ በሌሎች አንዳንድ ከተሞች ከባድ ፍንዳት ተኩስ ይሰማል። ከመዲና ኻርቱም ለመዉጣት እጅግ አስቸጋሪ እና ፈታኝ ከመሆኑም በላይ በጣም ብዙ ገንዘብ በእጅ ላይ ሊኖር እንደሚገባ በኻርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ይናገራሉ። የተለያዩ ሃገር ዜጎች የሃገራቸዉ መንግሥት ባዘጋጀላቸዉ አዉቶቡሶች እየተጫኑ ከከተማዋ እየወጡ ነዉ፤ እስካሁን ያልወጡት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን እና ኤርትራዉያን ነን ያሉን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤንባሲ የቀድሞ ዲፕሎማት፤ ይሁንና ከጦርነቱ በላይ አስፈሪዉ ቤት ዉስጥ ታግቶ በረሃብ ማለቅ ነዉ፤ ጥያቄዉ አሁን በህይወት የመቆየት ጉዳይ ነዉ።
በካርቱም ጦርነት ሲካሄድ 14 ቀናት ከቤቴ መዉጣት አቅቶኝ ተዘግቶብኝ ነበር አሁን ግን በደጋጎች ሱዳናዉያን ምክንያት መዲናዋን ለቅቄ ሱዳናዉያን አስጠግተዉኝ እገኛለሁ ያሉን ኢትዮጵያዊ ሱዳን ዉስጥ በተመድ ከለላ ቢያገኙም ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ምንም አይነት ድጋፍ እና ከለላ አግኝተዉ እንደማያዉቁ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ከእናቱ ጋር ወደ ሱዳን መጥቶ ካርቱም ያደገዉ እና በስራ ላይ ተሰማርቶ የነበረዉ ትዉልደ ኢትዮጵያዊ የሱዳን ዜጋ፤ የዓለም መንግሥታት ሁኔታዉ ከባድ መሆኑን ሊረዱት ይገባል ብሏል፤ የትናቸዉ ሲሉ በምሪት ለዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጥሪ አቀርበዋል።
ከካርቱም በደጋግ ሱዳናዉያን ርዳታ ወጥተን አሁን ከካርቱም 170 ኪሎሜትር ርቀት ላይ እንገኛለን ያሉን፤ በሱዳን የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት፤ ኢትዮጵያዊዉ ተጋግዞ ካርቱም የሚገኘዉን ዜጋዉን ሊያወጣዉ ይገባል፤ ሲሉ አበክሮ ተናግረዋል። በኻርቱም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ዜጎቹን እየረዳ አይደለም ማለት ያስቸግራል ያሉት ሰዉ ይሁንና በተለይ ጦርነት ረመጥ ዉስጥ ማለትም ኻርቱም ዉስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያዉያን ለመርዳት ጥረት እየተደረገ አይደለም ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለዉ ማኅበረሰብ በሱዳን ስለሚገኘዉ የሱዳን ማኅበረሰብ በቂ መረጃ ያለዉም አይመስለም፤ ሚዲያዎች በበቂ አይዘግቡም ብለዋል።
በሱዳን በተለይም በኻርቱም በጦርነቱ ተዘግቶባቸዉ የሚገኙት ኢትዮጵያዉያን ከመዲናዋ መዉጫቸዉ እንዴት ነዉ ስንል የኢትዮጵያ መንግሥት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ለመጠየቅ ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ