በጦርነት ምክንያ የጨመረዉ የኑሮ ዉድነትና የማህበረሰቡ አቅም ማጣት
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 19 2017
በጦርነት ምክንያት በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞን የጨመረዉ የኑሮ ዉድነትና የማህበረሰቡ አቅም ማጣት
በዋጋ ንረቱ ከፋብሪካ እስከ ግብርና ምርት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ እንዳለዉ የሚናገሩት የማህበረሰብ ክፍሎች በአካባቢዉ በመንግስትና በፋኖ ሁይሎች መካከል የሚደረገዉ ጦርነት ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ምክንያት ነዉ ይላሉ። አሁን ላይ በቀን 3 ጊዜ መመገብ አይቻልም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች መንግስት ገበያ የማረጋጋት ስራ ሊሰራ ይገባል ይላሉ።
ከሰሜኑ ጦርነት መጀመር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የሸቀጦች እና የግብርና ምርት ውጤቶችየዋጋ ጭማሪየሚታይበት በአማራ ክልል የሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞን እንዲሁም ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች ኗሪዎች አሁንም በዋጋ ንረት እየተፈተን ነው ይላሉ፡፡ በየእለቱ ከፍተኛ ለውጥ በሚታይበት የንግድ ስርዓት ውስጥ መጨመር እንጂ መቀነስ የሚባል ነገር የለም የሚሉት ነዋሪዎች ከትንሹ የዳቦ ሽያጭ ጀምሮ የማህበረሰብን አቅም ያገናዘበ የንግድ ልውውጥ የለም ብለዋል፡፡
‹‹ኑሮ ውድነቱ በጣም ህዝቡን እያስቸገረ ነው፤ እያደር እየጨመረ ነው የሚሄደው እዚህ አካባቢ 10 ብር ይሸጥ የነበረ ዳቦ 3 ሰዎች አድመው 15 ብር አደረገው፡፡ በዚህ ህዝቡ እየተቸገረ ነው፡፡››
በጦርነት ምክንያ የጨመረዉ የኑሮ ዉድነትና የማህበረሰቡ አቅም ማጣት
አሁን ላይ የዋጋ ንረቱ ከማህበረሰቡ የዕለት ገቢ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ሰርተው መሸፈን ያልቻሉትን የቤት የምግብ ወጭ ከማህበረሰቡ በሚሰበሰብ ድጋፍ ለመሙላት እንደሚጥሩ ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹የመግዛት አቅማችን እየደከመ በመሆኑ ከህብረተሰቡ ተሰብስቦ የመጣ የሚሰጠን በበጎ አድራጎት ቢኖረን ይሄ ሁሉ መውጣት አይፈልግም፡፡ 3 ጊዜ ቀርቶ አንዴም ለመብላት አጥሮናል፡፡ እኛ ሳንበላ ነው ልጆቻችንን የምናበላው፡፡››
የኑሮ ውድነቱ በዚህ ወቅት ለልጆች የተሻለ ትምህርት ከማሰብ የነገ ተስፋቸውን ብሩህ ለማድረግ ከሚደረግ ጥረት በዘለለ የልጆችን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ላይ ብቻ ትኩረት እንድናደርግ አድርጎናል ሲሉ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡
‹‹የኑሮ ውድነቱ በጣም ተፅዕኖ አለው፡፡ ምክንያቱም ለልጆች የተሻለ ለመመገብ፣የትምህረት እድል ለመስጠት፣ ለምግብ ብዙ ብር በማውጣቴ ምክንያት የግል ትም/ቤት የማስተምራቸውን ልጆች አስወጥተህ ወደ መንግስት ትመልሳለህ፤ የመንግስት ትምህርት ቤት ጥሩ አይደለም ለማለት አይደለም፤ ግን የተለየ ትኩረት ለማድረግ፣ ለዝንባሌያቸው፣ ለትምህርታቸው ማሰብ ትተን ለምግብ ብቻ እንድናወራ አድርጎናል፡፡››
በአማራ ክልል ያለዉ የፀጥታ መደፍረስ
አሁን በአካባቢው ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት በዋነኛነት በክልሉ ያለው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ነው የሚሉት ኗሪዎቹ ነጋዴው ማህበረሰብ ከቦታ ቦታ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አለመቻሉ አማራጭ እንድናጣ ሆነናል ብለዋል፡፡ ‹‹የሰላም ሁኔታው ነው ይህንን ሁሉ ያመጣው የጦርነቱ ሁኔታ ነው፡፡ በአማራ ክልል ጦርነቱ ነው የኑሮ ውድነቱን ያባባሰው፡፡››
ለዋጋ ጭማሬው ምክንያት ናቸው የሚባሉት የንግዱ ማህበረሰብ በአካባቢው የሚስተዋለው ተለዋዋጭ የሆነ የዋጋ ንረት በእኛ ምክንያት የመጣ ሳይሆን ከትራንስፖርት እና ቀረጥ ጋር የመጣ ጭማሪ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹አሁን ምን መሰለህ ይህ ለእኛም አስቸጋሪ ነው፤ ነዳጅ ይጨምራል፤ ሌላም በየመንገዱ ቀረጥ ይበዛል፤ እነዚህ ነገሮች ለጭማሪ ምክንያት ናቸው፡፡ እኛም በጣም እየተማረርን ነው በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ነጋ መጨመር ነው፡፡››
የኑሮ ውድነቱን የተረጋጋ ለማድረግ የተቀናጀ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል የሚሉት የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተስፋየ መንግስቴ የዋጋ ንረቱ በሰው ሰራሽ እጥረት የመጣ በመሆኑ ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የቁጥጥር ስራ ይጠይቃል ምርት እያለም ነው የሚወደደው፣ የኢንዱስትሪ ምርት ዱቄት በብዛት ሱቅ ውስጥ እያየህ ዘይት 1500 ብር ሲሸጥ ታያለህ፤ ይህ ሰው ሰራሽ እጥረት ነው፡፡››
ገበያ የማረጋጋት ስራዉ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ
በአማራ ክልል በፋኖ እና በመንግስት ሀይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ምርትን ከቦታ ቦታ ለማዛወር እንቅፋት መፍጠሩን ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት ቢሆንም የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ህብረት ስራ ማህበራትን እና ሸማቾችን በማጠናከር ምርት በስፋት ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ እየሰራ መሆኑን የሚናገሩት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ታምራት ንጋቱን ይህንን እያደረግን ያለነው ግን የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ያለው የጸጥታው ሁኔታ ነው፡፡ ከእኛ ክልል አኳያ ዋነኛው እንቅፋት ከፀጥታው ጋር ተያይዞ ምርት ወደተፈለገበት ቦታ ለማዛወር ያለው ውስንነት ነው፡፡ በህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ዋጋው እንዲረጋጋ እያደረግን ያለነው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላይ አይደለም፡፡ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ያሉበት ቦታ ላይ ነው፡፡››
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር