በፈረንሳይ ብሔረተኛ ፓርቲና መሪዋ ማሪ ሌፐን ላይ የተላለፈ የፍርድ ቤት ውሳኔ
ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017
በፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ ማሪ ለ ፔን ላይ የፓሪስ ፍርድ ቤት ባለፈው ሰኞ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ከሐንጋሪው ኦርባን እስከ አሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ በውሳኔው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ለመሆኑ ፖለቲከኛዋ ምን አድርገው በፍርድ ቤት ውሳኔ ተላለፈባቸው? የዓለማችን ተጽእኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች አስተያየትስ ምን ይመስላል?
ባለፈው ሰኞ የፓሪስ ፍርድ ቤት በፈረንሳይ ዋና ፖለቲከኛ ማሪ ለ ፔን ላይ ያስተላለፈው ብይን ከፈረንሳይ አልፎ የመላ አውሮፓን ፖለቲካ የሚያናውጥ ሁኗል። ፍርድ ቤቱ የፈረንሳይ ብሔረተኛ ፓርቲ (ራሊይ ናሽናል) መሪ የሆኑት ማሪ ለፔን በቀረበባቸው ከአውሮፓ ፓርላማ የተመደበላቸውን አራት ሚሊዮን ዩሮ ያላግባብ መጠቀምና ማባከን ክስ ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው በሁለት ዓመት ገደብ የአራት ዓመት እስራትና የአንድ መቶ ሺህ ዩሮ ቅጣት አስተላለፎባቸዋል። ከሁሉም በላይ ግን አነጋጋሪ የሆነው ፍርድ ቤቱ በፖለቲከኛዋ ላይ ለአምስት ዓመታት ከማንኛውም የፖለቲካ ተሳትፎና አመራር እንዲታገዱ ያስተላለፈው ውሳኔ ነው።
ወይዘሮ ለፔን የፈረንሳይን ስደተኛና እስላም ጠል ብሔረተኛ ፓርቲን በምምራት ለዓመታት በፈረንሳይ ፖለቲካ የዘለቁ ሲሆን፤ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2027 ዓ.ም በሚደረገው የፈረንሳይ ፕሬዝድንታዊ ምርጫ ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብለው ከሚገመቱት ታዋቂ ፖለቲከኞች አንዷ ናቸው ።
ሰኞ ዕለት ያስቻለው የፓሪስ ፍርድ ቤት በሳቸውና ሌሎች 24 የፓርቲያቸው ሰዎች ያስተላለፈው ውሳኔና በተለይም በእሳቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ የጣለው እግድ ግን ብዙዎችን የፈረንሳይ ብሔረተኖችን ያስደንገጠ፤ የአውሮጳን ከዚያም አልፎ አትላንቲክ ማዶ ያሉ ብሔረተኛ ቀኝ ፖለቲከኞችን ያነቃነቀ ክስተት ሆኗል።
በውሳኔው የወ/ሮ ለፔንና የቀኝ ብሔረተኛ ፓርቲዎች አስተያየት
ወይዘሮ ለፔንና ፓርቲያቸው ውሳኔውን እያደገና እያሸነፈ ባለው ፓርቲያቸው ላይ የተላለፈ የፖለቲካ ውሳኔ ነው በማለት አውግዘው ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ዐሳውቀዋል። ለፔን በሰጡት መግለጫም ውሳኔውን፤ " ስርዓቱ ልናሸንፈው በመሆኑ የወረወረብን የኒውክለር ቦምብ ነው” በማለት እንደማይቀበሉት አስታወዋል።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ከፈረንሳይ አልፎ በመላው አውሮፓና አሜርካ ጭምር ባሉ የቀኝ፣ ወግ አጥባቂና ብሄረተኛ ፓርቲ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትችትና ተቃውሞ እየተሰማበት ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔውን ቀዳሚ ተወዳደሪ በሆኑ ፖለቲከኛ ላይ የተላለፈ ልክ ያልሆን ውሳኔ ሲሉ ገልጸውታል፤ « በፕሬዝዳንታዊ ውድድሩ ቀዳሚ ተፎካካሪ በሆኑ ፓለቲካኛ ላይ የተላለፈ ውሳኔ ነው» በማለት ይህም በአገረ አሜሪካ በእሳቸው ላይ ተላልፎ ነበር የሚሉትን ዓይነት ውሳኔ አንደሆነ አስታውቀዋል ።
በትራምፕ አስተዳደር ዋና ሰው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ኤሌን ሙስክም «አክራሪ ግራዎች ቤዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማሸነፍ ሲያቅታቸው ሕጋዊ ስርዓቱን ተቃዋሚዎቻቸውን እስር ቤት ለመወርወር ይጠቀሙበታል» በማለት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አውግዘው በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
የቀኝ ብሔረተኛ ኃይሎች ድምፅ ጎልቶ እየተሰማ ያለበት ምክንያት
በአውሮጳ ከሐንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስተር ቪክቶር ኦርባን እስካ ጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስተር ጆርጂያ ሜሎኒ ድረስ ውሳኔውን ያላወገዘና ከማሪያ ሌፒን ጎን እንደሚቆም ያላስታወቀ የቀኝ ኃይል የለም። በፈረንሳይ ፖለቲካ ላይ በመጻፍ የሚታወቁት ወይዘሮ ላራ ማርሎዌ እንደሚሉት የብሔረተኛ አክራሪ ፓርቲዎች በውሳኔው ላይ የሚሰጡት ግብረ መልስ የቀኝ አክራሪ አስተሳስብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ መሆኑን የሚይሳይ ነው። «ሁሉም የቀኝ ብሔረተኝ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ከቦሶናሮ እስከ ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ከሳልቪኒ እስከ ቪክቶር ኦርባን፤ ሁሉም «ሁላችንም ማሪያ ሌፔን ነን» እያሉ ነው» በማለት እነዚህ ኃይሎች እርስ በራሳቸው እንደሚተባበሩና ይህም አዲሱ አለማቀፋዊ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልዋል።
በለንዶን ዩንቨርስቲ ኮሌጅ የአውሮፓና ፈረንሳይ ፖለቲካ ፕሮፈሰር የሆኑት ዶክተር ፊሊፕ ማርሌሬም ይህንኑ ሀሳብ በመጋራት እነዚህ ኃይሎች የሕግን የበላይነት የሚያጣጥሉ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፤ "የዓለም ፖለቲካ ተገለባብጧል። እራሳቸው በሕግ የበላይነት የማያምኑ ኃይሎች የሕግ አስከባሪና ተቆርቋሪ መስለው ሲታዩ የሚገርም ነው" ሲሉ ትዝብታቸውን ገልጸዋል ።
ለፔንና የፈረንሳይ ፍርድ ቤቶች ገለልተኘነት
በፈረንሳይ ከፍተኛ ፖለቲኞች ሲከሰሱና ሲፈረድባቸው ሌፔን የመጀመሪያዋ ባይሆኑም በመጭው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የማሽነፍ እድል ያላቸው ግምባር ቀደም ተወዳዳሪ በመሆናቸው በተለይ የዕግዱ ውሳኔ አነጋጋሪ ሁኗል። ሆኖም ግን በፈረንሳይ ፍርቤቶች ገለልተኝነትና ነጻነት ላይ አብዛኝው የፈረንሳይ ሕዝብ እምንት አለው ነው የሚባለው። እንደውም ወይዘሮ ሌፔን የፈረንስይን ፖለቲከኞች በሙስና ሲከሱ፤ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ሲሟገቱ የቆዩትን ያህል እስቸውም ወንጀል ፈጽመው ከተገኙ ተገቢው ውሳኔ ሊተላለፍባቸው ይገባል በማለት በፈረንሳይ የፍትህ ሥርዓት ላይ የሚቀረበውን ትችት የሚቃወሙ ጥቂቶች አይደሉም።
ውሳኔው በፈረንሳይ ፖለቲካ ላይ የሚኖረው አንድምታ
ያም ሆኖ ውሳኔው የፈረንሳይን ፖለቲካ ውስብስብ እንደሚያረገውና ቀውስም ሊያስክትል እንደሚችል ነው በብዙዎች የሚነገረው። ወይዘሮ ላራ እንደሚሉትም ውሳኔው የወይዘሮ ሌፔን ደጋፊዎችን በተጠቂነት ስሜት ሊያነሳሳቸው ይችላል « የወይዘሮ ሌፒን ተከታዮች መሪይቸውን የጥቃት ሰለባ አድረገው ሊወስዱ ይችላሉ፤ ውሳኔውን የመብት ጥሰት፤ የዴሞክራሲ ሽረት እንደሆነ አድርገው ሊያምኑንና የበለጠ አክራሪ ሊሆኑም ይችላሉ» በማለት ይህም በፈረንሳይ ፖለቲካ ቀውስ ሊስክትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ውሳኔው የአውሮፓ የቀኝ ኃይሎችን ሊያስተባብርና ሊያጠናክር ብሎም የሕብረቱን ፖለቲካም ሊያወሳስብ ይችላልም እየተባለ ነው።
ገበያው ንጉሤ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ