1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድርቅ በፑንትላንድ

ሐሙስ፣ የካቲት 23 2009

በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የተባባሰዉ ድርቅ በርካቶችን ከቤት ንብረታቸዉን እያፈናቀለ ነዉ። የክረምቱ ዝናብ በመስተጓጎሉ ድርቁ ከጠናባቸዉ የሶማሊያ አካባቢዎች የተፈናቀሉትን ታስተናግድ የነበረችዉ ፑንትላንድ አሁን የድረሱልኝ ጥሪዋን ማሰማት ጀምራለች።

Somalia Puntland
ምስል DW/A. Kiti

Puntland drought - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

የሶማሊያ ግዛት ወደሆነችዉ ወደፑንትላንድ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ጋረዌ የሚገባን እንግዳ የደረቁ የወንዝ መዉረጃዎች፤ የምትፋጅ ፀሐይ እና አቧራ አፍሶ የሚያቦነዉ ትኩስ ንፋስ ነዉ የሚቀበለዉ። ከጋረዌ ከተማ አንድ መቶ ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ ከ75 የሚበልጡ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚገኙበት ዳንጎሮየ መጠለያ ጣቢያ ይገኛል። ከተፈናቃዮቹ አብዛኞቹ እዚያዉ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ናቸዉ። ኑሯቸዉን የሚገፉት ከዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በየወሩ በሚያገኙት የአንድ መቶ ዶላር የገንዘብ ድጎማ ነዉ።

 የ74 ዓመቱ አዛዉንት ጃማ ፋራህ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮቹ በተጠለሉበት በዚህ ጣቢያ ከባለቤት እና ከበርካታ የልጅ ልጆቻቸዉ ጋር ይኖራሉ። ከ500 የሚበልጡ ፍየሎቻቸዉ በድርቁ ምክንያት ከሞቱባቸዉ በኋላ በጣም ጥቂት ከብቶች ብቻ ቀርተዋቸዋል። በድርቁ መጥናት ምክንያት ወንድ ልጃቸዉ ለከብቶቻቸዉ ግጦሽ ፍለጋ ባህር ዳርቻ ወደሚገኙ አካባቢዎች ከተጓዘ አንድ ወር አልፎታል። ፋየራህ ጥያቄ አንድ ነዉ፤

«በአሁኑ ሰዓት ዉኃና ምግብ ነዉ የሚያስፈልገን። እነዚህ ሁለቱን ማግኘት ካልቻልን ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል። እንደምትመለከቱት እነዚህ የዉኃ ማጠራቀሚያዎች ናቸዉ፤ እንደምታዩት በዉስጣቸዉ ያለዉ ዉኃ እያለቀ ነዉ። ዉኃ ብናገኝ እንኳን ቀጣዩ ጥያቄ ምግብ ነዉ። ይህን ነዉ አሁን በቅድሚያ የሚያስፈልገን።»

ከስድስት ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ ማለትም ከሶማሊያ አጠቃላይ ሕዝብ 50 በመቶ የሚሆነዉ በድርቁ አሁን ተጎድቷል። የ60 ዓመቷ ዳሃሃብ አብዱላ አንዷ ናቸዉ።

የተፈናቃዮቹ መጠለየያ ጣቢያምስል DW/A. Kiti

«ዝናብ የለም፤ ለፍየሎቹም የሚሆን ግጦሽ የለም። 60 ዓመቴ ነዉ፤ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ድርቅ አላየሁም፤  አልሰማሁምም። ሰዎች እየሞቱ ነዉ፤ ምግብ የለም፤ ዉኃም የለም። በላይኛዉም ሆነ በታችኛዉ ሶማሊያ ያለሁ ሁኔታ ተመሳሳይ ነዉ።»

በድርቁ ከፍተኛ የተጎዱት አዛዉንቶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸዉ። ጠንካሮቹ ወንዶች ለከብቶቻቸዉ ግጦሽ እና ዉኃ ፍለጋ ርቀዉ በመጓዛቸዉ ምክንያት ለብቻቸዉ ቀርተዋል። ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑት ሕጻናትም በቂና እና የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት ለጉዳት መዳረጋቸዉ የተለመደ እየሆነ ሄዷል። ሕጻናት አድን ድርጅት በሚያንቀሳቅሰዉ ጋረዌ በሚገኘዉ አጠቃላይ ሆስፒታል፤ የስምንት ወር ጨቅላ የሆነችዉ ሀቢባ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ክፉኛ በመጎዳቷ ለእርዳታ ገብታለች። ናይሮቢ በግል ሃኪም ቤት ዉስጥ ይሠራ የነበረዉ ስነምግብ ባለሙያ ሰኢድ አህመድ ያሲን ከዚያ ሥራዉን ለቅቆ እዚህ ፑንትላንድ ጋረዌ አጠቃላይ ሆስፒታል በበጎ ፈቃደኝነት በማግለልገል ላይ ይገኛል።

«ይታይህ ናይሮቢ ዉስጥ ጥሩ ሥራ ነበረኝ፤ ነገር ግን ሰዎች ሊከላከሉት በሚቻል ከሰዉነት ዉኃ በማጣት እና በተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት እየሞቱ መሆኑን ስመለከት ትቼዉ መጣሁ።

ለዚህ ለተጋፈጡት ችግር የበኩሌን ለመርዳት ወስኜ እዚህ በበጎ ፈቃደኝነት ለመሥራት መጣሁ።»

በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘዉ ድርቅ፤ የሰዎችንም ሕይወት እየቀማ ነዉ። የፑንት ላንድ ምክትል ፕሬዝደንት አብዲሃኪም አብዱላሂ ሃጂ ኦማር ሀገሪቱ ከዚህ ቀደምም ድርቅ አጋጥሟት እንደነበር ቢገልፁልም የአሁኑ ግን እጅግ የከፋ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህ ምክንያትም ሰዎች በገዛ እጃቸዉ ሕይወታቸዉን እያጠፉ መሆናቸዉ እየተነገረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምስል DW/A. Kiti

«እንደምታዉቁት ሶማሌያዉያን መቶ በመቶ የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸዉ። አብዛኛዉን ጊዜ ደግሞ ሰዎች ራሳቸዉን አይገድሉም። ነገር ግን በዚህ ጭንቀት ምክንያት ሕይወታቸዉን ማጥፋት ጀምረዋል።»

ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነዉ የሶማሊያ ዜጋ ሕይወት በግዛቱ ከሚንቀሳቀሱት የሰብዓዊ ድርጅቶች በሚገኝ የእርዳታ እህል ላይ ጥገኛ ነዉ። በአካባቢዉ ለሚንቀሳቀሱት የእርዳታ ድርጅቶች ደግሞ ዋነኛዉ ሥጋት የፀጥታ ጉዳይ ነዉ። የሰብዓዊ ድርጅቶቹ  ዉጥረት በሰፈነበት አካባቢ መንቀሳቀሳቸዉ እርዳታ ማግኘት እንዲችሉ የተሻለ ፀጥታ ወዳለበት አካባቢ ብዙ ሰዎች እንዲፈልሱ አስገድዷል። ሶማሊያ ዉስጥ በወቅቱ ድርቅ ምክንያት ለከፋ ርሃብ የተጋለጠዉን ከስድስት ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ ለመመገብ ቢያንስ አንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል።  

ሸዋዬ ለገሠ/ አልፍሬድ ኪቲ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW