1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ትምህርትኢትዮጵያ

የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 8.4% ማለፋቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ

እሑድ፣ መስከረም 4 2018

በየዓመቱ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች መካከል ከ15-20% የሚልፉበት ደረጃ ለመድረስ እስከ ሁለት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ተናገሩ። ከ2017 ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተፈታኞች ያለፉት 8.4% ብቻ ናቸው። ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ መካከል 1,249 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ሳያሳልፉ ቀርተዋል

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ትምህርት ሚኒስቴር በፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገው ለውጥ “በገመትንው ልክ በተወሰነ ደረጃ ከገመትንው በላይ ውጤት እያመጣ” እንደሆነ ተናግረዋል። ምስል፦ Education Ministry of Ethiopia

በየዓመቱ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች መካከል ከ15 እስከ 20 በመቶው የሚልፉበት ደረጃ ለመድረስ እስከ ሁለት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ተናገሩ። በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መካከል 8.4 በመቶው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ማግኘታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 28.9%፣ ሐረሪ ክልል 21.8% እንዲሁም አማራ ክልል 12% ተማሪዎች በማሳለፍ የተሻለ ውጤት እንዳስመዘገቡ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ዛሬ እሁድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 14,620 ተማሪዎች፣ የኦሮሚያ ክልል 11,651 ተማሪዎች አሳልፈዋል።

ሀገሪቱ በምትከተለው የትምህርት ፖሊሲ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚችሉት ከ50% በላይ ዉጤት ያመጡ ተማሪዎች ናቸው። ባለፈው ዓመት 585 ሺሕ 882 ተማሪዎች በመላ ሀገሪቱ ፈተናውን ወስደዋል።

ፈተናውን የወሰዱ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ ይዟል። ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ 297,528 ተማሪዎች የተፈጥሮ ሳይንስ 288, 352 ተማሪዎች የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተና እንደወሰዱ ተናግረዋል። ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 277 ሺሕ 816 ሴቶች ሲሆኑ 308 ሺሕ 66 ተማሪዎች ወንዶች ናቸው። 

ከእነዚህ ውስጥ 23% ፈተናውን የወሰዱት በኦንላይን ነው። በኦንላይን ከተፈተኑት መካከል 21.7% ወይም 29, 233 ተማሪዎች ማለፋቸውን የገለጹት የትምህርት ሚኒስትሩ ወደፊት በተመሳሳይ መንገድ የሚሰጠው ፈተና እየጨመረ እንደሚሔድ ጥቆማ ሰጥተዋል። 

ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት በማምጣት 48,929 ተማሪዎች ማለፋቸውን ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገልጸዋል። ፈተና ካለፉ ተማሪዎች ውስጥ 30,451 ወንዶች ሲሆኑ 18,478 ሴቶች ተማሪዎች ናቸው። 

ከተፈታኞቹ ውስጥ ከ91% በላይ የሚሆኑት ቢወድቁም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ትምህርት ሚኒስቴር በፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገው ለውጥ “በገመትንው ልክ በተወሰነ ደረጃ ከገመትንው በላይ ውጤት እያመጣ” እንደሆነ ተናግረዋል። 

የ12ኛ ክፍልፈተና በኦንላይን ከተፈተኑት መካከል 21.7% ወይም 29, 233 ተማሪዎች ማለፋቸውን የገለጹት የትምህርት ሚኒስትሩ ወደፊት በተመሳሳይ መንገድ የሚሰጠው ፈተና እየጨመረ እንደሚሔድ ጥቆማ ሰጥተዋል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

ለዚህም “ከምንም ዐይነት ኩረጃ በጸዳ መልክ ተምረው የሚያልፉ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ እየጨመረ” መሆኑን የጠቀሱት የትምህርት ሚኒስትሩ የተማሪዎች ብቃት ሲጨምር “የዩኒቨርሲቲዎችን ትምህርት ጥራት እያሻሻለ እየሔደ እንደሆነ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

“ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት የሚሰጡት ትኩረት እየጨመረ በሔደ ቁጥር የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሔድ” ትምህርት ሚኒስቴር መገንዘቡን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ለመምህራን የተሰጡ ሥልጠናዎች እና ተማሪዎች ከመደበኛው መንገድ በተጨማሪ በዲጂታል ስልቶች የሚሰጧቸው ትምህርቶች ለውጤቱ መሻሻል አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ መስከረም 4 ቀን 2018 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። 

በ2017 ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች መካከል 1,249 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ሳያሳልፉ ቀርተዋል። በዓመቱ 50 ትምህርት ቤቶች በአንጻሩ ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ አሳልፈዋል። ባለፈው ዓመት 1,363 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አላሳለፉም ነበር። 

ከ600 ከሚታረመው ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በወንዶች ከፍተኛውን 591 ውጤት ያመጣው በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ዶዶላ ኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው። በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ በሴቶች ከፍተኛው 579 ሲሆን ውጤቱን ያስመዘገበችው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ተማሪ ናት። 

በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከወንዶች ከፍተኛው 562 ውጤት ያመጣው የአምቦ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደሆነ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገልጸዋል። በሴቶች 548 ውጤት ያስመዘገበችው በአዲስ አበባ የሚገኘው የሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደሆነች ገልጸዋል። 

በ2016 ከተፈተኑት መካከል 1,221 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ሲያመጡ ዘንድሮ ወደ 2,384 ተማሪዎች ከፍ እንዳለ ፕሮፌሰር ብርሀኑ አስረድተዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ መካከል  ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው። የትምህርት ሚኒስትሩ እንዳሉት የአዳሪ ትምህርት ቤቶች አማካይ ውጤታቸው 71% ሆኗል።  የመንግሥት መደበኛ ትምህርት ቤቶችአማካይ ውጤት 30.6% ሲሆን የግል ትምህርት ቤቶች በአንጻሩ 51% ነው።  ዝቅተኛው ውጤት የተመዘገበው በማታ ትምህርት ተማሪዎች ነው። የማታ ትምህርት ተማሪዎች አማካይ ውጤታቸው 25.9% እንደሆነ የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

አርታዒ ታምራት ዲንሳ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW