1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

በ30 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የውሂብ ማዕከል በአዲስ አበባ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2016

ራክሲዮ ግሩፕ በተባለ የግል ድርጅት በአዲስ አበባ የተገነባው ይህ የውሂብ ማከማቻ ማዕከል፤ የመረጃ መጥፋትን፣ የአገልግሎት መቋረጥን እና ከመረጃ ቴክኖሎጅ መሠረተ ልማቶች ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችን በማስቀረት ቀልጣፋ እና አስተማማኝ የዲጅታል መረጃ አጠቃቀምን ለመፍጠር ያግዛል ተብሏል።

Äthiopien Raxio-Rechenzentrum
ምስል፦ Privat

ራክስዮ ኢትዮጵያ የመረጃ ማከማቻ ማዕከል

This browser does not support the audio element.


ባለንበት የዲጂታል ዘመን፣ የውሂብ ማዕከላት/Data Centers/ የዕለት ተዕለት የዲጅታል እንቅስቃሴዎቻችን ጋር በእጅጉ የተሳሰሩ ናቸው።  
እነኝህ ማዕከላት  የውሂብ መጥፋትን ፣ የአገልግሎት መቋረጥን እና ከመረጃ ቴክኖሎጅ መሠረተ ልማቶች ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችን በማስቀረት ቀልጣፋ እና  አስተማማኝ የዲጅታል መረጃ አጠቃቀምን በመፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። 

ከዚህ ጠቀሜታቸው አንፃር  መንግስታት እና  የግል ኩባንያዎች በየሀገራቱ በርካታ መዋዕለንዋይ በማፍሰስ  የውሂብ ማዕከላትን ይገነባሉ።
የሀገራትን መረጃ የሚተነትነው ስታስቲካ ባወጣው መረጃ መሰረት በጎርጎሪያኑ  2021 ዓ/ም ፣ ከመረጃ ማዕከላት  ሽያጭ  የተገኘው ዓለም አቀፍ ግምታዊ ገቢ  50.58 ቢሊዮን ዶላር ያህል ነበር። በጎርጎሪያኑ 2028 ደግሞ ከ136 ቢሊዮን ዶላር እንደሚበልጥ ይሄው  መረጃ  ያሳያል።
በተለያዩ ተቋማት በግላቸው የሚሰሩት የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እሸቴ እንደሚሉት በኢትዮጵያም በተለያዩ ተቋማት የውሂብ ማዕከላት አሉ። ነገር ግን  ያልተቀናጁ እና ለደህንነት ችግር የተጋለጡ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን ችግር የሚያቃልሉ አንዳንድ የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ አቅም ያላቸው የውሂብ ማዕከሎችን እየገነቡ ነው።ያለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይም ራክሲዮ  የተባለ የግል ኩባንያ አቅም ያለው የውሂብ ማዕከል ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ በውቀቱ ታፈረ እንደሚሉት አይሲቲ ፓርክ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው ይህ ማዕከል በ10,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ  ሲሆን፤ ግንባታው ሦስት ዓመታትን ወስዷል።

አዲስ አበባ ከተማ የተገነባው ራክሲዮ የውሂብ ማዕከል በ30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ የተደረገበት ሲሆን፤ 5 ነጥብ 5 ሜጋዋት አቅም አለው።ምስል፦ Privat

እንደ ስራ አስኪያጁ  ራክሲዮ የውሂብ ማዕከል በ30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገነባ ሲሆን፤ 5.5 ሜጋዋት አቅም አለው።ይህም በዲጅታል መረጃ ላይ ለተመሰረቱ ባንክን ለመሳሰሉ ተቋማት ያለችግር  አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል። በኢሜይል የሚመጡ የመረጃ ስርቆቶችን እንዴት እንከላከል?
አስተማማኝ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የበይነመረብ ግንኙነት፣ የኤለክትሪክ ሀይል እንዲሁም አመቺ የሙቀት እና ቅዝቃዜ ባለበት ቦታ መረጃዎችን በማከማቸት፤ የውሂብ ማዕከሉ ለተቋማት ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በተለይ በኢትዮጵያ ፤አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎችን ለሚሰሩ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማሳደግም አስተዋፅኦ እንዳለው ያብራራሉ። 

አዲስ አበባ ከተማ የተገነባው ራክሲዮ የውሂብ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ ምስል፦ Privat

ለሀገር ውስጥ የንግድ ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማትን በመደገፍ፣ለዲጅታል ኢኮኖሚው ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር፤የራክሲዮ የውሂብ ማከማቻ ማዕከል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአገልግሎት እና የይዘት አቅራቢዎችን ለመሳብ ማዕከሉ አጋዥ እንደሚሆን ገልፀዋል። እንደ ክላውድ ያሉ የውሂብ ማከማቻዎችን ለመጠቀም የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬም ያስቀራል።ክላውድ፤መረጃን ከመጥፋት የሚታደገው ቴክኖሎጂ
በጎርጎሪያኑ መስከረም  2023 ዓ/ም  ክላውድሲን /Cloudscene/ ባወጣው  መረጃ መሠረት፣ በዓለም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ በንቃት  ስራቸውን የሚከውኑ  የውሂብ ማዕከሎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 5,375 በዩኤስኤ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ጀርመን 522፣ እንግሊዝ በ517 የውሂብ ማዕከላትን በመገንባት  አሜሪካን ይከተላሉ። ቻይና በ448 የውሂብ ማዕከላት በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሩሲያ እና ጃፓን እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይይዛሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ  ሀገራት ግን መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው በግል ኩባንያዎች የሚገነቡ ታላላቅ የመረጃ ማከማቻ ማዕከላት በጣም ጥቂት ናቸው።
ለዚህም የገንዘብ እጥረት፣የሀገራት አለመረጋጋት እና በቂ የኤለክትሪክ ሀይል አለመኖር እንደ ችግር ይጠቀሳሉ።ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች በዘርፉ አለመኖራቸው ለአዳጊ ሀገራት የመረጃ ማዕከላት ሌላው ፈተና ነው።

ለዲጅታል ኢኮኖሚው ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር፤የራክሲዮ የውሂብ ማከማቻ ማዕከል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የአገልግሎት እና የይዘት አቅራቢዎችን ለመሳብ አጋዥ እንደሚሆን ተገልጿል,ምስል፦ Privat

ኢትዮጵያን ጨምሮ በ7 የአፍሪቃ ሀገራት ተመሳሳይ ማዕከላትን በመገንባት ላይ የሚገኘው የራክሲዮ ኩባንያ እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ለመስራት ምን ምን ስራዎችን አከናወነ? አቶ በውቀቱ እንደሚሉት«በኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ተስፋዎችም አሉ።»ከነዚህም ውስጥ የኤለክትሪክ ዋጋ ርካሽ መሆን አንዱ ሲሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብም በሀይል አቅርቦት ረገድ ሌላው ተስፋ ነው። በሌላ በኩል የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረትን በተመለከተ ስልጠና በመስጠት ሰዎችን ለስራው ብቁ እንዲሆኑ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ ድርጅታቸው እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 

የውሂብ ማዕከላት አንድ ድርጅት ፣  የንግድ ተቋም  ወይም ግለሰብ  ብዙ መረጃዎችን የሚያከማችበት፣ እና  የሚያስተዳድርበት አካላዊ ወይም ምናባዊ /Virtual / መዋቅር ነው። የመረጃዎቹ ለድርጅቱ ትክክለኛ ተግባር አስፈላጊ የሆኑ የንግድ ፋይሎችን፣ የውሂብ ቋቶችን፣መተግበሪያዎችን  እና ሌሎች የዲጂታል መረጃዎችን ሊያካትቱ ይችላሉ።

ራክሲዮ የውሂብ ማዕከል ለተቋማት ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በተለይ በኢትዮጵያ ፤አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎችን ለሚሰሩ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማሳደግም አስተዋፅኦ አለውምስል፦ Privat

በአጠቃላይ እነዚህ የውሂብ ማከማቻ ማዕከላት  ሰርቨሮችን፣ የማከማቻ መሳሪያዎችን እና የኔትወርክ ማሰራጫዎችን  ከሌሎች የመረጃ ቴክኖሎጅ  መሠረተ ልማት ክፍሎች ጋር ያስቀምጣሉ። መጠናቸውም ሆነ ውስብስብነታቸው ከትናንሽ የአካባቢ የመረጃ ማዕከላት  ግዙፍ መዋቅር ፈጥረው  በዓለም አቀፍ ደረጃ  እስከ ሚያገለግሉት  ሊደርስ  ይችላል። ዋናው ግባቸው ግን የመረጃ ደህንነትን በመጠበቅ አስተማማኝ  የዲጅታል አገልግሎት እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህንንም በተጓዳኝ ከሚሰራ ይልቅ ከፍ ያለ የመፈፀም ብቃት ያላቸው እና ስራዬ ብለው በዘርፉ ላይ ያተኮሩ እንደ ራክሲዮ ያሉ የውሂብ ማዕከላት ቢሰሩት በብዙ መንገድ ውጤታማ መሆኑን የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው እሸቴ ከነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት ያስረዳሉ። 

አቶ በውቀቱ እንደገለፁት በጎርጎሪያኑ በ2018 የተቋቋመው ራክሲዮ ግሩፕ፤ ቲር III  የተባለውን ለቴክኖሎጅ ተቋማት የሚሰጠውን ከፍተኛ የቴክኒክ አቅም እና የብቃት  ደረጃ ሰርተፍኬት አለው።ኩባንያው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ7 የአፍሪቃ ሀገራት ማለትም  በኡጋንዳ፣ ሞዛምቢክ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አንጎላ እና ታንዛኒያ ተመሳሳይ  የመረጃ ቋቶችን  በመገንባት ላይ ሲሆን፤በጎርጎሪያኑ 2031 ዓ/ም ደግሞ ከስሃራ በታች ላሉ የአፍሪቃ ሀገራት  ወደ 25 የውሂብ ማዕከላትን ለመገንባት ማቀዱን  ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
 
ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW