1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡርኪናፋሶ የውጭ ሚዲያዎችን ለምን ዘጋች

ቅዳሜ፣ ግንቦት 3 2016

የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አመራር ፍራንስ 24፣ ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል እና ጄዩን አፍሪኬን ጨምሮ በርካታ የውጭ የሚዲያ አዉታሮችን አግዷል። ይህ ርምጃ የመጣዉ የዜና ማሰራጫዎቹ የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች፣ ወታደሮች በሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል ብሎ ያወጣዉን መግለጫ ከዘገቡ በኋላ ነው።

Burkina Faso
ምስል AP/picture alliance

ቡርኪናፋሶ ለምን የውጭ ሚዲያዎችን ዘጋች

This browser does not support the audio element.

የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ ጁንታ የዶቼ ቬሌ ራድዮን DW ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎችን እና ጋዜጦችን አግዷል። ይህ የፕሬስ አፈና ወታደራዊዉ ጁንታ በሲቪል ዜጎች ላይ ያሳለፈዉ ፀረ ሽብር ርምጃ ስርዓት አንዱ አካል ነዉ። ይህ በቦርኪናፋሶ ሲቪል ነዋሪ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰም ነዉ። ይህ የቡርኪናፋሶዉ ወታደራዊ አገዛዝ ርምጃ የመጣዉ የዜና ማሰራጫዎቹ የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች ፤ በሃገሪቱ ዉስጥ ጽንፈኛን ለመከላከል በሚወሰድ ርምጃ ወታደሮች በሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል ብሎ ያወጣዉን መግለጫ ከዘገቡ በኋላ ነው።  በቅርቡ ከታገዱ ሚዲያዎች መካከል DW፣ TV5 የዜና ማሰራጫዎች እንዲሁም ላልተወሰነ ጊዜ ከታገዱት የዓለም አቀፍ ጋዜጦች መካከል የፈረንሳዩ ለ ሞንዴ ፣ እንዲሁም የብሪታኒያዉ - ዘ ጋርዲያን ይገኙበታል። እነዚህ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከመዘጋታቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ የብሪታንያዉ የቢቢሲ እና የአሜሪካ ድምጽ የ VOA ስርጭት በቡርኪናፋሶ ለጊዜው  መታገዳቸዉ የተሰማዉ በመጀመርያ ነበር።  

የምዕራብ አፍሪቃ የሚዲያ ፋውንዴሽን (MFWA) ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ሙሂብ ሰኢድ ፤ ጉዳዩ የሚጠበቅ ነበር ይላሉ። «በአጠቃላይ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በውጪ ሚዲያዎች ላይ የሚታየዉ ጭቆና እና ጥላቻ እየተባባሰ መምጣቱ አላስደነቀንም።»  

በመብት ጥሰት የተከሰሰዉ የመከላከያ ሰራዊት

ቡርኪናፋሶምስል Philippe De Poulpiquet/MAXPPP/dpa/picture alliance

በጎርጎረሳዉያኑ 2022 የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አመራር በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ ፤  አገዛዙ ፍራንስ 24፣ ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል እና ጄዩን አፍሪኬን ጨምሮ በርካታ የሚዲያ አዉታሮችን  አግዷል። የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ አገዛዝ ባለፈዉ 2023 ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ የመጨረሻዎቹን ሁለት የፈረንሣይ ጋዜጠኞችን ከሃገር አባሮ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ፤ አንድም የውጭ ጋዜጠኛ አይገኝም።

በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን የመጣዉ እና በትራኦሬየሚመራዉ የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ ሃገሪቱ በዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት መረጃ ጠቋሚ መዘርዝር ላይ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በመረጃዉ መሰረት በምዕራብ አፍሪቃ ባጠቃላላይ በጎርጎረሳዉያኑ 2023 በአሸባሪዎች የተገደሉ ሰዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በቡርኪናፋሶ ብቻ ከሁለት ሦስተኛ በላይ ጨምረዋል፤ ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።   

ቡርኪናፋሶ

«በቡርኪናፋሶ ከአማፂያኑ ጋር የሚደረገዉ ፍልምያ  በጦር ሜዳም ሆነ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ እየተካሄደ ነው። በርዕዮተ ዓለሙ መስመር ሁሉንም ዜጎች በወረፋ ለመግረፍ ያለመ ፕሮፓጋንዳ እቅድ ተዘርግቷል። ስለዚህ በአስተዳደሩ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ትችት በተወሰነ መልኩ ጭቆና እና ግፊት ደርሶበታል።» 

በቢርኪናፋሶ የቅርብ ጊዜው የሚዲያ አዉታሮች እገዳ ምክንያት የሆነዉ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ የቡርኪናፋሶ ጦር በአንድ የነዋሪዎች መንደር በየካቲት 2024 በትንሹ 223 ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል ሲል የከሰሰበት መግለጫ ነበር። 

በተመሳሳይ በዩናይትድ ስቴትስ መቀመጫዉን ያደረገዉ ያለትርፍ የሚንቀሳቀሰዉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባወጣዉ መረጃ መሰረት በትራኦሬ የሚመራዉ ወታደራዊ  የጸጥታ ሃይላት በሲቪሎች ላይ የፈፀሙት ግድያ  በ2022 430 ሰዎች ተቆጥረዉ ነበር። ከዓመት በኋላ በ2023 ዓመት ብቻ 735 ሰዎች መገደላቸዉን አጋልጧል።

የሀገር ውስጥ ሚዲያ መዘጋት

በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የበለጠ ከባድ ያደርገዋል ሲሉ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እና የምዕራብ አፍሪቃ የሚዲያ ፋውንዴሽን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ሙሂብ ሰኢድ ገልፀዋል።

ቡርኪናፋሶምስል Vincent Bado/REUTERS

«የዓለም አቀፉ የሚዲያ ድርጅቶች በአጠቃላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና የተወሰነ የዲፕሎማሲ ጡንቻ አላቸው። እናም የዓለምአቀፉ ሚዲያ ከተጠቃ፣ ከተባረረ እና ከታገደ፣ እርምጃዉ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በቀጣይ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንዲገጥማቸው በግልፅ መልክት ያስተላለፈ ነዉ።»

የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች እና የተለያዩ የሚዲያ አዉታሮች ወታደራዊዉን አስተዳደር የማያስቀይም ዘገባ ለመስራት እጅግ በጣም ተጠንቅቀዉ፤ራሳቸዉን ከእዉነታ በማገድ እና ቅድመ ምርመራ በማድረግ መሆኑም ተመልክቷል። በሃገሪቱ የሚታየዉ ፖለቲካዊ ቀዉስን በተመለከተ የሃገር ዉስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ የቡርኪናፋሶዉ ወታደራዊዉ ጁንታ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን የምዕራብ አፍሪቃ የሚዲያ ፋውንዴሽን እና ድንበር አያግዴዉ የጋዜጠኞች ድርጅት  ገልፀዋል።  

 

ኬት ሄርሰን / አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረእግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW