ቡንደስታግ፤ የጀርመን አዲሱ የአፍሪቃ ግንኙነት መርህ እና የጀርመን እሴቶች
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2018
በጀርመን ፌዴራል ፓርላማ - ቡንዴስታግ የጀርመን አዲስ የአፍሪቃ ስትራቴጂን በሚመለከት ባለፈዉ ሳምንት መጠናቀቅያ በጀርመን ፓርላማ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ የውጭ ፖሊሲ ግልጽነት አስተማማኝነት ያለው መሆኑ ተገልጿል። ስብሰባዉ ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እሴቶችን የዘረዘረ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት አምባሳደሮች እና የተለያዩ የአፍሪቃ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል። ከዚህ ሌላ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ አባላት፣ የጀርመን ተቋማት ተወካዮች፣ የኬንያ እና ሌሎች ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል። በውይይቱ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት የምታጠናክርበት ጉዳዮች ተነስተዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በተለይ በአየር ንብረት፣ በኃይል ምንጭ እና በሞያ ስልጠና ዘርፍ የጋራ ትብብርን በተመለከተ በውይይቱ የተነሱ ነጥቦች ነበሩ። የኬንያ አምባሳደር አገራቸዉ ኬንያ የጀርመን አፍሪቃ ጉባዔን ማስተናገድዋን አንስተዋል። አምባሳደርዋ በኬንያ ከ120 በላይ የጀርመን ኩባንያዎች እንደሚገኙም ተናግረዋል። የጀርመን ንግድ ምክር ቤት በግብፅ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ናይጄሪያን ጨምሮ በ12 የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ቢሮዎች አሉት። ይህ ቢሮ በኢትዮጵያ የለም። በዚሁ ጉባኤ ላይ ትናንት ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ሪም አላባሊ ራዶቫን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ በይፋ ተነግሮም ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ በበርሊን ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ተገኝተዋል። ዶክተር ፀጋዬን በጀርመን ፓርላማ ዉሎ ምን ይመስላል ስንል ጠይቀናቸዋል።
«ስብሰባዉ አዲሱን የጀርመን ፖለቲካ፤ በጀርመንኛዉ (interessengeleitete Außenpolitik mit Transparenz und Verlässlichkeit) ማለትም የጀርመንን ፖለቲካ ያማከለ፤ የትብብር እና የእድገት ፖለቲካ እንደማለት ነዉ። ዝግጅቱ የነበረዉ ይህን አዲስ የፖለቲካ መርህን ለማስተዋወቅ ነበር። ይህን ስብሰባ በጀርመን ፓርላማ ይመሩ የነበሩት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ በዚህ ስብሰባ ላይ እሳቸዉን ጨምሮ የጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ አባላት፣ የጀርመን ተቋማት ተወካዮች፣ የኬንያ እና ሌሎች ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል። በጀርመን የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ነበሩ፤ የክርስትያን ዲሞክራቶች ፤ ሶሻል ዲሞክራቶች፤ አማራጭ ለጀርመን እንዲሁም አረንጓዴዎቹ እና ግራዎቹም ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ እንደኔ የተጠሩ ሰዎችም ነበሩ። እነዚህ ሁሉ በተገኙበት ነበር የጀርመን ፍላጎት ተኮር የሆነዉ አዲሱ የፖለቲካ መርህ የቀረበዉ።»
ዶ/ር ፀጋዬ እንደዉ ቀደም ብለዉ እንደገለፁልኝ በፓርላማዉ የአፍሪቃ ሃገራት ተወካዮች ፤ የተለያዩ ተቋማት ተጋብዘዋል። የስብሰባዉ ዋና ማጠንጠኛም ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር በአዲስ የያዘችዉ ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እሴቶች መሆናቸዉን ጠቅሰዋል ይህ በዝርዝር ምን ይሆን?
«ዋናዉ ፍላጎት ተኮር የሆነዉ የጀርመን ፖለቲካ፤ ቋሚ ያደረጋቸዉ ነጥቦች፤ ለምሳሌ ሌሎች ሃገራት ሄደዉ እርዳታ ሲሰጡ ከዚ ህስ ጀርመን ምን ልትጠቀም ትችላለች የሚለዉን ይመለከታል። አንደኛ ኤኮኖሚዉን ይመለከታል። ጀርመን ያላት የኤኮኖሚ ፍላጎት ላይ ነዉ፤ ይኸዉም እርዳታ በሚሰጡበት ሃገራት፤ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ አገሩን እየጠቀሙ ጀርመንም ልትጠቀም የምትችልበት ነዉ።
ሁለተኛዉ ደግሞ የጀርመን እሴቶችን ይመለከታል። ዲሞክራሲን፤ ብዛሃነት - ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጥምረት መስራት፤ ከዚህ ሌላ ፀጥታ ደህንነትን፤ የአካባቢዉንእና የቀጠናዉን፤ መረጋጋት በተመለከተ፤ በዝያ ዉስጥ ያሉትን የጀርመን ዜጎችን፤ እንዲሁም ድርጅቶችን/ካንፓኒዎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነዉ። ሌላዉ ጀርመን ጥሬ ማዕድንን ልትጠቀም የምትችልበትን ያካትታል። ይህ ማለት ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እሴቶች የተባሉትን ሦስቱን ምሶሶዎች ይዞ ነዉ የሚሄደዉ። በጀርመን ፓርላማ ቡድደስታግ የጀርመን አዲስ የአፍሪቃ ስትራቴጂ በሚል በተካሄደ ስብሰባ ላይ በፓርላማ የተገኙት ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ጋር ያደረግነዉን ቃለ ምልልስ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን። ጀርመን የሥራ ባህል ያለዉ ሃገር ነዉ፤ ጥራት ተኮት ትጋት ተኮር ፤ ያለዉ ባህል አላቸዉ። የጀርመናዉያን መዋዕለ ንዋይ «ኤንቬስት» ጠንካራ ነዉ። ወዳጅነትም ከጀመሩ ዘላቂነት ያለዉ ነዉ።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ