ቢል ጌትስ ሐብታቸውን ለበጎ አድራጎት ሊያውሉ ነው
ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017
ቢል ጌትስ ሐብታቸውን ለማከፋፈል መዘጋጀታቸውን በገለጡበት ንግግር፦ በአፍሪቃ በርካታ አገራት የጤና በጀት ማሽቆልቆሉን አጥብቀው ተችተዋል ። ባለሐብቱ ትችቱን የሰነዘሩት 25ኛ ዓመት የቢል ጌትስ በጎ አድራጎት ተቋም ወይንም ፋውንዴሽን ምሥረታን በማስመልከት በአፍሪቃ ኅብረት የኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ባሰሙት ንግግር ነው ። የገንዘብ ድጋፎቹ በድንገት መቋረጥ በአፍሪቃ የጤናው ዘርፍ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ባለሐብቱ አሳስበዋል ።
«አንዳንዶቹ የገንዘብ ድጋፎች ሙሉ በሙሉ የተቋረጡት እጅግ በድንገት ነው ። እናም የእነዚህ ድጋፎች መቋረጥ ብርቱ ስህተት ነው ብዬ ነው የማስበው ። በእርግጥ በተቻለኝ መጠን ወደ ቀድሞ ይዞታቸው እንዲመለሱ ጥረት ማድረጌን እቀጥላለሁ ። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ከ25 ዓመታ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕጻናት ሞት ከመቀነስ ይልቅ ከፍ ይላል ።»
በአፍሪቃ ለጤናው ዘርፍ በጀት ማሽቆልቆል እንደ ዋና ምክንያትነትም የአገራት በእዳ መዘፈቅ እና ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊዎች እጅ ማጠር መሆናቸው ተጠቅሷል ። በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ ከዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ተግባሯ ማፈግፈጓ በአዳጊ አገራት ላይ ብርቱ ጫና አሳርፏል ። የአሜሪካ በጎ አድራጎት (USAID) በዓለማችን የተለያዩ አገራት በዓመት የ50 ቢሊዮን ድጋፍ ነበር የሚያደርገው ። ይህ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ በመታጠፉም የመርኃ ግብሩ 83 በመቶ ያህሉ ላይ ብርቱ ተጽእኖ አሳርፏል ። በአፍሪቃ የጤና እና የግብርናው ዘርፍ ላይ ተጽእኖው እጅግ የጎላ ነው ።
ከዓለማችን ቁጥር አንድ ባለሐብቶች መካከል አንዱ የሆኑት ቢል ጌትስ ከአጠቃላይ ሐብታቸው አንድ በመቶ ውጪ ለበጎ አድራጎት በተለይም በአፍሪቃ የጤና ዘርፍ ላይ ለማፍሰስ መዘጋጀታቸውን ገልጠዋል ። ባለሐብቱ ለበጎ አድራጎት ለመስጠት የወሰኑት ወደ 200 ቢሊዮን ዶላር ግድም የሚጠጋ ነው ። ሐብቱ የሚፈስሰውም በቢል ጌትስ በጎ አድራጎት ተቋም መሆኑ ተጠቅሷል ።
«ሐብቴ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት እንዲከፋፈል ቁርጠኛ ውሳኔ አሳልፈናል ። እንደምታውቁት ከመጠን በላይ እጅግ በጣም ዕድለኛ ነኝ፤ ሐብቴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ እናም ሥጦታዬን በማፋጠን የቢል ጌትስ ፋውንዴሽን ይህን ሐብት በሙሉ እንዲወስድ እፈልጋለሁ ። እናም ከዚህ ቀደም በሕዝብ ፊት ያላልኩት ነገር፤ አብዛኛው ገንዘብ እዚህ አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ጥቅም ላይ ይውላል ። »
ምንም እንኳን ቢል ጌትስ ሐብታቸውን ለበጎ አድራጎት ለማዋል መወሰናቸው ቢሰማም ተቃውሞ እና ትችትም አላጣቸውም ። በቢል እና ሜሊንዳ የበጎ አድራጎት ተቋም በኩል አፍሪቃ ውስጥ የዘረ መል ምርምር እንዲደረግ ከፍተኛ ድጋፍ ተደርጓል የሚል ትችት ይስተጋባል ። ይህ ድጋፍም በአፍሪቃ ሰፋፊ የግብርና መስኮችን ለመቆጣጠር ያለመ ነውም የሚሉ አሉ ። ዶክተር ዶሚንጎስ ክሪስቶቫኦ፦ በአንጎላ ሐኪም እና የጤና አስተዳደር ብሎም የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሞያ ናቸው ። የአፍሪቃ አገራት ከጥገኝነት መውጣቱ ላይ ቢያተኩሩ እንደሚያሻም አጥብቀው መክረዋል ።
«የአፍሪቃ አገራት ፍጹም እጅ ጠባቂ መሆንን ማስወገድ አለባቸው ። የሕዝብ የጤና ስርዓትን ዘላቂ ማድረጉ እጅግ ወሳኝ ነው ። ለሕዝብ ጤና ሥርዓቶች ዘላቂነት እያንዳንዱ አገር የራሱን የጤና አጠባበቅ ሥርዓት በገንዘብ ለመደገፍ የራሱን ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ ነው ።»
የቢል ጌትስ ተቋም አፍሪቃ ውስጥ የጤው ዘርፍ ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ወደፊት ዓለም ላይ ብርቱ ተጽእኖ የሚያሳርፈው የሰው ሠራሽ አስተውሎትምስር እንዲሰድድ ይሻል ። በእርግጥ አፍሪቃ በዚህ ረገድ ገና ዳዴ በማለት ላይ ናት ። እናም አፍሪቃ የሚያስፈልጋትን ራሷ መወሰን ይገባታል ሲሉም ዶክተር ዶሚንጎስ አክለዋል ። ዐይኖች ሁሉ በተለያዩ ዘርፎች አፍሪቃ ላይ ማተኮራቸውን ቀጥለዋል ። አፍሪቃ ምን ያህል ተጠቃሚ ትሆን ይሆን?
ማንተጋፍቶት ስለሺ/አንቶኒዮ ካሽካሽ
ሸዋዬ ለገሠ