1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አዉሮፕላን የምርመራ ዉጤት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2015

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሲበር ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጨረሻ የምርመራ ውጤት ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ይፋ ተደረገ።

Äthiopien Mehr als 150 Tote bei Flugzeugabsturz
ምስል Reuters/T. Negeri

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሲበር ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጨረሻ የምርመራ ውጤት ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ይፋ ተደረገ።

ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ እንዳስታወቀው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ከስድስት ደቂቃ በላይ አየር ላይ መቆየት ሳይችል የተከሰከሰው እና ከ35 ሀገራት ለጉዞ ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎችን እንደጫነ ቱሉ ፈራ የተባለችው አካባቢ የወደቀው ግዙፍ አውሮፕላን የመከስከሱ ምክንያትና አውሮፕላኑን ከቁጥጥር ውጪ ያደረገው "ኤም ካስ" የተባለው መቆጣጠሪያ  ንደነበር ታውቋል ብለዋል። የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር "የተጎጅዎችን እንባ ሊያብስ የሚችል እና በዘላቂነት የበረራ ዘርፉ ላይ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርግ ነፃ ፣ ግልጽ እና አለም አቀፍ አሰራሮችን የጠበቀ ምርመራ ለማድረግ ችለናል" ብላል።

157 ሰዎችን አሳፍሮ ቢሾፍቱ አካባቢ የተከሰከሰዉ የኢትዮጵያ አዉሮፕላንምስል Reuters/T. Negeri

አራት አመታት ሊሆነው ጥቂት ወራት የቀሩትና ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከ ስድስት ደቂቃ በኋላ ከራዳር እይታ የጠፋው ቦይንግ 737 ማክስ 8 የመንገደኞች አውሮፕላን ከአየር ትራፊክ ግንኙነት መቋረጡን ተከትሎ የመከስከስ አደጋ ደርሶበት የበረራ ሰራተኞቹን ጨምሮ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ጠፍቷል።

ይህንን ክስተት ተከትሎ  "የፈልጎ ማዳን" የተባለ ቡድን ፍለጋ በማድረግ ቦሾፍቱ አቅራቢያ ጉዳቱ የደረሰበትን ቦታ ማግኘቱ ይታወሳል። አደጋው ከተከሰተ ከ 30 ቀናት በኋላ የመጀመርያ ደረጃ የምርመራ ግኝት ይፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የኮሮና ተህዋሲ በመዛመቱ እና የአደጋውን መንስኤ በጥልቀት ለመመርመር አስቸጋሪ በመሆኑ የመጨረሻው ሪፖርት በአስገዳጅ ሁኔታ ዘግይቷል ብለዋል የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ።

ቢሾፍቱ አካባቢ የተከሰከሰዉ የኢትዮጵያ አዉሮፕላን የመረጃ ቋት «ብላክ ቦልስ»ምስል picture-alliance/Photoshot

አራት ዋና ዋና የምርመራ ግኝቶችን የዘረዘሩት ዳግማዊት ሞገስ የአደጋው መነሻ ዋነኛ ችግር የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ መሆኑን ገልፀዋል። "አንደኛ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን የበረራ ባለሙያዎች በሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ደንብ መሰረት ሕጋዊ እና የታደሰ የበረራ ፈቃድ ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ያላቸው መሆኑ ተረጋግጧል። ሁለተኛ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን ከሲቪል አቬሽን ባለ ስልጣን የተፈቀደና የታደሰ የበረራ ፈቃድ ያለው እንደነበር በተደረገው የማህደር ፍተሻ ታይቷል። ሦስተኛ የአውሮፕላኑ የጭነት ክብደት እና ሚዛን በሚፈቀደው መጠን መሆኑ ታይታል። አራተኛ አውሮፕላኑን ከቁጥጥር ውጪ ያደረገው ዋናው ምክንያት ኤም ካስ የተባለው መቆጣጠሪያ እንደነበር ታውቃል" ብለዋል።

ምስል Solomon Muchie/DW

በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሥር ያለው የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ የምርመራ ሥራው ሲያከናውን ቆይቷል። የመጨረሻው የምርመራ ውጤቱ አደጋው በደረሰ በ 30 ቀናት ውስጥ ይፋ ከተደረገው  እውነታዎች ጋር የሚጣጣም እና እውነታው ይበልጥ የተረጋገጠበት ብሎም ያንን ግኝት ያፀና ያለውን የመጨረሻ የምርመራ ግኝት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የአሜሪካ እና የፈረንሳይ ድርጅቶች እንዲሁም የፈረንሳይ መንግሥት እና ባለሙያዎች በምርመራው ሂደት በመረጃ ትንተና ሥራ ላይ በስፋት መሳተፋቸውም ተገልጻል። የምርመራ ሥራው ሲከናወን ከፍተኛና ብዙ ጫና እና ፍላጎቶች እንደነበሩም ተነግሯል። "ብዙ ጫናዎች ነበሩ። ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈናል። ነገር ግን እንደ ሀገር በአለም አቀፍ ሕግ አደጋው የተከሰተበት ሀገር ስለሆንን ምርመራውን የምንመራው እኛ ስለነበርን የተጎጅዎችን እንባ ሊያብስ የሚችል እና በዘላቂነት የበረራ ዘርፉ ላይ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርግ ነፃ ፣ ግልጽ እና አለም አቀፍ አሰራሮችን የጠበቀ ምርመራ ለማድረግ ችለናል"

ቢሾፍቱ አካባቢ የተከሰከሰዉ የኢትዮጵያ አዉሮፕላን ምስል picture-alliance/dpa/M. Ayene

የተሳፋሪዎች እና የአውሮፕላኑን ካሳ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የአደጋው መርማሪ አካል "የአደጋ መርማሪው ቡድን ይህንን አይመለከተውም" ብሏል። ይልቁንም የምርመራው ዋና አላማ ተመሳሳይ ስህተቶች እንዳይደገሙ ትምህርት እንዲወሰድበት እና ወደፊት የተሻለ ሥራ መሰራት እንዲችል መሰረት ለመጣል ያለመ ነው ተብሏል።

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በወጣት አብራሪዎች ሲበር በደረሰበት የመከስከስ አደጋ የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ የ157 መንገደኞች ሕይወት መቅጠፉ ይታወሳል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW