1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ዲጂታል ዓለምኢትዮጵያ

በየል ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነው ቢኒያም ሎሊሶ

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ጥር 29 2018

“በ15 ዓመቴ የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነፃ የትምህርት ቱቶሪያል የሚሰጥ ፕሮጀክት ጀምሬ ነበር። “ ይላል ቢኒያም ሎሊሶ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው የል ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ነው። በኢትዮጵያ የክረምት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሰ አዲስኮደር (AddisCoder) በተባለው ተቋም በበጎ ፍቃደኝነት ስልጠናም ይሰጣል።

ቢኒያም ሎሊሶ
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው የል ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ቢኒያም ሎሊሶ በክረምት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሰ አዲስኮደር (AddisCoder) በተባለው ተቋም በበጎ ፍቃደኝነት ስልጠናም ይሰጣል።ምስል፦ Privat/DW

በየል ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነው ቢኒያም ሎሊሶ

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ዱራሜ ከተማ የተወለደው ቢኒያም ሎሊሶ ሎምቤ ያደገው ወይም የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እስኪያጠናቅቅ ድረስ አብዛኛው ጊዜውን ያሳለፈው በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ነው። ወጣቱ ሁሉም ተማሪዎች እኩል የትምህርት እድል ማግኘት ቢችሉ ምኞቱ ነው። ይህ ደግሞ ምኞት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ወደ ስራ የገባው ገና በ15 ዓመቱ ነው ።  

“በ15 ዓመቴ የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነፃ የትምህርት ቱቶሪያል የሚሰጥ ፕሮጀክት ጀምሬ ነበር። ይህ በፈረንጆቹ ዓመት 2012 ነው። ብቻዬን ነበር የጀመርኩት፤ በሁለት ተማሪዎች ተጀምሮ በትንሽዬ ወራት ጊዜ ወደ 10 እና 12 ተማሪዎች አድጎ ነበር። ይህም በቀድሞ ትምህርት ቤቴ የአዳማ ቁጥር 2 የሚባል ትምህርት ቤት ቱቶሪያል በነፃ እሰጥ ነበር።“

ቢንያም የመሰረተው ይህ የአልበርት ቱቶሪያል ማዕከል እስካሁን ድረስ ወጣቱ በሀገር በሌለበትም ስራውን ቀጥሏል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከ3000 በላይ ተማሪዎች በበጎ ፍቃደኞች አማካኝነት የማጠናከሪያ ትምህርት ማግኘታቸውን ቢንያም ከዶይቸ ቬለ ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ ገልጿል። ስልጠናው የሂሳብ፤ የፊዚክስ፣  የኬሚስትሪ ፣ የባዮሎጂ ፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚያግዙ ስልጠናዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።  

 „በተጨማሪ ደግሞ ከትምህርት እገዛው ባሻገር መስከረም በሚመጣበት ጊዜ የትምህርት መገልገያዎች ለማያገኙ ሰዎች ከረጂ አካላት የምናሰባስባቸውን ማቴሪያሎች በዚህ ፕሮጀክት እንለግሳለን።“ ይላል ቢንያም።


የመጀመሪያ ዲግሪውን በታላቋ ብሪታንያ የተከታተለው ቢንያም ከተለያዩ ተቋማት በርካታ የእውቅና ማስረጃዎችን አግኝቷል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ለድህረ ምረቃ ትምህርት በ ዩናይትድ ስቴትስ ይገኛል። ይህም ነፃ የትምህርት እድል ያለውን እውቀት ይበልጥ እንዲያዳብር እንዳገዘው ይናገራል።    

„ በአሁኑ ሰዓት የል ዩኒቨርሲቲ ነው ያለሁት። አሜሪካ ውስጥ ካሉ Ivy League ዩንቨርስቲዎች መካከል ትልቁ የሚባል ነው። የኮምፒውተር ሳይንስ እየተማርኩ ነው። የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት በአሁኑ በ AI ዘመን በጣም አስደናቂ ነው። እኔ እዚህ መምጣቴ የሪሰርች እውቀቴን እንዳዳብር ረድቶኛል። ማስተማር በጣም ነው የምወደው። ውስጤ PHD ሰርተህ በዩንቨርስቲ ደረጃ አስተማሪህ ሆነህ ቀጥል ነው የሚለኝ። እና ያለሁበት ቦታ የማስተማር እድሌን እንዳመቻች እድል ፈጥሮልኛል ።“ ይላል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ በበጋ የእረፍት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለስክ አዲስኮደር (AddisCoder) በተባለው ተቋም ውስጥ በበጎ ፍቃደኝነት ስልጠና ትሰጣለህ። ተቋሙ ከኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በትብብር ይሰራል። ከ700 በላይ ተማሪዎችንም እስካሁን አሰልጥኗል።  ከሰለጠኑ ተማሪዎች መካከል በርካታ ስመ ጥር ወደ ሆኑ የውጭ ሀገር ዩንቨርስቲዎች ትምህርታቸውን ቀጥለው ለመከታተል የሄዱ ተማሪዎች አሉ።  

(AddisCoder) የተባለው ተቋም እስካሁን ከ700 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኗል።  ምስል፦ Privat/DW

አዲስኮደር (AddisCoder) ስልጠና ለማን ነው የሚሰጠው?  

„አዲስኮደር በጣም የምወደው ፕሮጀክት ነው። ፕሮፌሰር ጄላኒ ኔልሰን በሚባል በእናቱ ኢትዮጵያዊ በአባቱ አሜሪካዊ በሆነ የኮምፒውተር ሳይንስ ፕሮፌሰር ነው የተጀመረው። በዚህ ፕሮጀክት ላይ የሚሳተፉት ተማሪዎች በትምህርታቸው የተካለ ውጤት የሚያመጡ ከመላው ኢትዮጵያ የተመረጡ ተማሪዎች ናቸው። ይላል ቢኒያም ቀጥሎም ሲያብራራ

"ግማሹ  የሚመጣው በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ነው ግማሹ ደግሞ በአዲስኮደር አማካኝነት አመልክቶ ነው። የማመልከቻ ጊዜ አብዛኛውን ጊዜ በፈረንጆቹ ታህሳስ 31 ይጠናቀቃል። ትምህርቱ የሚሰጠው በኢትዮጵያ ክረምት  በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ  ነው። በነፃ ነው ተማሪዎቹ የሚማሩት። እኔ በዚህ ፕሮጀክት ላለፉት ሶስት ዓመታት ረዳት መምህር ሆኜ  ሳግዝ ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ 30 ረዳት መምህርቶችን እየመራሁ አብሬ ስሰራ ነበር“

"በዚህ ፕሮጀክት ላይ የሚሳተፉት ተማሪዎች በትምህርታቸው የተካለ ውጤት የሚያመጡ ከመላው ኢትዮጵያ የተመረጡ ተማሪዎች ናቸው ይላል"ቢኒያም ምስል፦ Privat/DW


አመልካቾች ምን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል? 

„ውጤታቸው ጥሩ መሆን አለበት። የትምህርት ደረጃቸው ከአንድ እስከ አምስት ቢሆን፤ አማካይ ውጤታቸው ከ90 በላይ የሆኑ ለዚህ ፕሮግራም ቢያመለክቱ የመመረጥ እድላቸው ሰፊ ነው። ፕሮግራም ፕሮግራሚንግ ግዴታ ማወቅ አይጠበቅባቸውም። ከዜሮ ነው የሚጀምሩት።”

ቢንያም  ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ሁሉም ነገሮች የተሟሉ ባይሆንም ይህ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ UK እና  ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመሄድ እና  የከፍተኛ ትምህርቱን ከ  ከመከታተል ወደ ኃላ አላስባለውም።  ሌሎች ወጣቶች እንደሱ በትምህርት ስኬታማ እንዲሆኑ ከግል ተሞክሮው ተነስቶ ማወቅ አለባቸው የሚለው በርካታ የትምህርት እድሎች እንዳሉ ማወቅ እንዳለባቸው ነው። 


“ኢንተርኔት ላይ ጊዜዬን ብዙ አጠፋ ነበር። ትንሽ ገንዘብ ሳገኝ ኢንተርኔት ቤት ነበር ሮጬ እሄድ የነበረው። የትምህርት እድሎችን ለመሞከር ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ እሞክር ነበር። ሜንተር የሚያደርጉ ግሩፖችን መቀላቀል። ከትምህርት ውጪ የሚሰሩ ስራዎችን ኮሚኒቲ ሰርቪስ ቢያደርጉ የትምህርት እድሎችን ለማመልከት ሊረዱ ይችላሉ። ”

ምስል፦ Privat/DW

በተለያዩ ተቋማት እና ዮንቨርስቲዎች ነፃ የትምህርት እድል የማግኘት እድል አግኝተኃል። ላንተ ማን መንገዱን አሳየህ? 

„ሚዲያ እከታተል ስለነበር ትላልቅ ቦታ ላይ የደረሱ ሰዎችን አይ ነበር።  የኢንጂነር ቅጣው እጅጉን መፅሀፍ ያነበብኩት በልጅነቴ ነው። እዛ ላይ ውጪ ሀገር እንደተማረ አይቻለሁ። እና ከዛን ጊዜ ጀምሮ ውጭ ሀገር ሄዶ የመማር ፍላጎቴ የጨመረው ያኔ ነው። አርዓያ የሚሆኑ ሰዎችን ማየት ጥሩ ነው። …በዛ ምክንያት ነው የተነሳሳሁት። “

ነፃ የዉጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ለሚፈልጉ ተማሪዎች መረጃ የሚያገኙበት የቴሌግራም ቻናል አለህ። ቻናሉን 12500 የሚሆኑ አባላት አሉት።  ይህም ቻናል ከተከፈተ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንደው በዚህ መንገድ ምንያህል ወጣቶች ነፃ የዉጭ ሀገር የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማገዝ ችለህ ይሆን?

„ቁጥሩን በትክክል አላውቀውም። ግን የትምህርት እድል አገኘው፤ የቪዛ ቀጠሮ አገኘሁ ብለው ይፅፉልኛል። በትንሹ ከ20 በላይ ሰዎች የትምህርት እድል አግኝተው የሄዱ ይመስለኛል። የራሴን ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ ጊዜ ስለሚኖረኝ ይህንን ትራክ የማድረግ ፍላጎት አለኝ“። 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW