1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ባለሙያዎች ከዓመታት በኋላ ወደ ነጠላ አሐዝ ስለወረደው የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ምን ይላሉ?

እሑድ፣ ጥር 17 2018

የዋጋ ግሽበት ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ነጠላ አሐዝ ዝቅ እንዳለ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል። የዋጋ ግሽበት በታኅሳስ ወደ 9.7% ዝቅ እንዳለ የተገለጸው ሸማቾች በኑሮ ውድነት በሚፈተኑበት ወቅት ነው። ለመሆኑ የብሔራዊ ባንክ ገዥ “እጅግ የሚያስደምም” ያሉት ነጠላ አሐዝ የዋጋ ግሽበት በባለሙያዎች እንዴት ይታያል?

በያይነቱ የኢትዮጵያ ተወዳጅ ምግብ
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የዋጋ ግሽበት የከዓመት ዓመት ዕድገት በህዳር ወር ከነበረበት 10.9 በመቶ በታኅሳስ ወደ 9.7 በመቶ ዝቅ እንዳለ አስታውቋል።ምስል፦ DW

ባለሙያዎች ከዓመታት በኋላ ወደ ነጠላ አሐዝ ስለወረደው የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ምን ይላሉ?

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የዋጋ ግሽበት የከዓመት ዓመት ዕድገት በህዳር ወር ከነበረበት 10.9 በመቶ በታኅሳስ ወደ 9.7 በመቶ ዝቅ እንዳለ አስታውቋል። በድርጅቱ ሪፖርት መሠረት የምግብ ዋጋ ግሽበት በህዳር ከነበረበት 10.6 በመቶ ወደ 9.8 በመቶ ዝቅ ብሏል። ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ግሽበት በአንጻሩ ከ11.4 በመቶ ወደ 9.6 በመቶ እንደወረደ ሪፖርቱ ይጠቁማል።

የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያ ወደ ነጠላ አሐዝ ዝቅ ያለው ከአስር ዓመታት ገደማ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ለምሳሌ ያክል በጥር 2014 ገደማ የዋጋ ግሽበት 33.6 በመቶ ደርሶ ነበር። ባለፉት ዓመታት ዋጋ በፍጥነት እያሻቀበ ኢትዮጵያውያንን በኃይል ሲፈታተን ቆይቷል። 

“የአቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻ ወጪ መናር እና ልል የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲዎች” የዋጋ ግሽበት መንስዔዎች እንደሆኑ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር። “የምግብ ትራንስፖርት እና ሥርጭትን ሒደት ያስተጓጎሉ የሀገር ውስጥ ግጭቶች እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የቁልፍ ሸቀጦች ወጪ መጨመር” ለዋጋ ንረት ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ መዋቅራዊ የዋጋ ንረትን ለማቃለል የታቀዱ መመሪያዎች እና የፖሊሲ እርምጃዎች ይፋ ያደረገው በነሐሴ 2015 ነበር። በወቅቱ የማዕከላዊው ባንክ ገዥ የነበሩት ማሞ ምህረቱ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ ከ20 በመቶ በታች፤ በ2017 ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ” ማቀዱን አስታውቀው ነበር።

“የዋጋ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የገንዘብ ፖሊሲን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ” ሥልጣን የተሰጠው ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል። ማዕከላዊው ባንክ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ ብድር ማቆም እና ባንኮች የሚያቀርቡት ብድር ከዓመት ዓመት የሚያሳየውን ዕድገት መገደብ ይገኙበታል። 

አቶ ማሞን የተኩት የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” በተባለ ስብሰባ ላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 9.7 በመቶ መድረሱን ገልጸው “ይኼ ድል ልቡን የማያሞቀው ኢትዮጵያዊ ካለ የዚህን ሥራ ጥልቀት እና ክብደት በአግባቡ ያልተረዳ ነው” ሲሉ ጉዳዩ ለመንግሥታቸው ከፍ ያለ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። “የማክሮ [ኢኮኖሚ] ማሻሻያው በአግባቡ ተናቦ ተቋማት አንድ ላይ ሆነው ስለሰሩ ዛሬ እጅግ የሚያስደምም ውጤት ማግኘት ችለናል” ብለዋል። 

ዶይቼ ቬለ የፋይናንስ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ እና በኔዘርላንድስ በሚገኘው ክሊንገንዴል ኢንስቲትዩት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪው አማኑኤል ደሳለኝን በመጋበዝ በጉዳዩ ላይ ውይይት አካሒዷል።

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW