1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባሕርዳር-ግጭት፣ዉጥረትና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል

ዓርብ፣ ሐምሌ 28 2015

የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግሥት የሚንስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል «የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ» ያለዉን ግጭት ለመግታት በመላዉ የአማራ ክልል የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ ጠዋት ደንግጓል

በኢትዮጵያ የሐገር መከላከያ ሠራዊትና «ፋኖ» በተባለዉ ታጣቂ ቡድን መካከል አማራ ክልል ውስጥ የሚደረገዉ ግጭት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ። የየአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት፣ ማዕከላዊ ጎንደር-ጎንደር፤ ደቡብ ጎንደር-ደብረ ታቦር፤ ምሥራቅ ጎጃም-ደብረ ማርቆስ ከተሞች ዉስጥ ዛሬ እስከማርፈጃዉ ድረስ የተኩስ ልዉዉጥ ሲደረግ ነበር። ዛሬ ከቀትር በኋላ ባህርዳር ዉስጥ በሁለት አካባቢዎች ቦምቦች ፈንድተዋል። የፍንዳታዉ ምክንያትም ሆነ ያደረሰዉ ጉዳት ሥለመኖር አለመኖሩ የተዘገበ ነገር የለም።ሰሞኑን ዉጊያ ሲደረግባቸዉ የነበሩት የቆቦ፣ የወልዲያና የላሊበላ ከተሞች ከፍተኛ ዉጥረት ከመስፈኑ ባለፍ ዛሬ እስከማርፈጃዉ ተኩስ አልነበረም። የተለያዩ የአማራ ክልል ከተማና ቀበሌዎችን የሚያገናኙ መንገዶች በመዘጋታቸዉ የሰዎች ጉዞና እንቅስቃሴ ታጉሏል። የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን እንደዘገበዉ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን ለመዉሰድ ባሕርዳር ዩኒቨርስቲ ዘንዘልማ ካምፓስ የገቡ ተማሪዎች ወደየመኖሪያ አካባቢዎቻቸዉ መመለስ አልቻሉም። የኢንተርኔት አገልግሎትም ከትናንት በስቲያ ማታ ጀምሮ በአብዛኛዉ የአማራ ክልል ተቋርጧል።የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግሥት የሚንስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል «የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ» ያለዉን ግጭት ለመግታት በመላዉ የአማራ ክልል የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ ጠዋት ደንግጓል።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ-ደሴ ከተሞች የሚያደርገዉን በረራ ማቋረጡን ትናንት አስታዉቋል። የአማራ ክልል በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዉ ትልቅ ክልል ነዉ። 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW