1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባሕር እና ውቅያኖስ ላይ የተከሰው ሙቀት የጋበዘው ድርቅ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 2015

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያስከተለው ድርቅ በርካታ አካባቢዎች ላይ የውኃ እጥረት ማስከተሉ እየተነገረ ነው። የባሕር እና ውቅያኖሶች መሞቅ ድርቅ መጋበዙን ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት። በድርቅ ተጎድቶ በከረመው የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ደግሞ ከበድ ያለ ዝናብ በአንዳንድ ቦታዎች ጎርፍ ማስከተሉ ተነግሯል።

BG Tonga Vulkanausbruch | Vulkan Hunga Tonga-Hunga Ha'apai
ምስል Tonga Geological Services via REUTERS

ባሕር እና ውቅያኖስ ላይ የተከሰው ሙቀት የጋበዘው ድርቅ

This browser does not support the audio element.

በየሁለት ደቂቃው አንድ የእግር ኳስ ሜዳን የሚሸፍን የደን አካባቢ እንደሚወድም የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ተቋም መረጃ ያመለክታል። ዛፎች ዛፍ ብቻ አይደሉም የሚለው ይኽ መረጃ፣ ሙቀት አማቂ የሆነውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በመምጠጥ የዓለም የሙቀት መጠን እንዳይጨምር የሚከላከሉን አስፈላጊዎቻችን መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥቷል።

በምዕራብ ሜዲትራኒያን አካባቢ የተከሰተው ሙቀት ከባድ ድርቀት ሊያስከትል እንደሚችል ጥናቶች እያመለከቱ ነው። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ከወዲሁ ሙቀቱ ጠንከር ማለቱ እየታየ ነው። ለተከታታይ ዓመታት በድርቅ በተጎዱ የአፍሪቃው አንድ አካባቢዎችም ድርቀቱ ለከባድ ዝናብ እና ጥፋት ለሚያስከትል ጎርፍ ቦታውን ቢለቅም ከገቡበት ቀውስ ለማውጣት እንደሚያዳግት የዓለም የምግብ መርሃግብር ባለሙያዎች ጠቁመዋል።

«ለሦስት ዓመታት ገደማ የዘለቀው ድርቅ ለዝናብ እና ለአውዳሚ ጎርፎች መንገድ ከፍቷል። ከተገመተው በላይ ዝናብ የተገኘበትን የዝናብ ወቅት ብናጠናቅቅም፤ አንድ የተሻለ የዝናብ ወቅት ብቻውን ያለው ቀውስ እንዲያበቃ ሊያደርግ አይችልም።»

የሚሉት በናይሮቢ የዓለም የምግብ መርሃ ግብር በእንግሊዝኛውም ምህጻር የWFP ጽሕፈት ቤት የአቸኳይ ጉዳይ ከፍተኛ ተጠሪ ዶሜኒክ ፌሬቲ ናቸው። የእሳቸው ድርጅት WFP እንዲሁም የዓለም የእርሻ ድርጅት እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት በጋራ የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢን ወቅታዊ ይዞታ አስመልከተው ባለፈው ሳምንት በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ የተከሰተው ድርቅ ያስከተለው የምግብ እጥረት እንደሚባባስ እና የወረርሽኞች መከሰትም በተጠቀሰው አካባቢ ቀውሱን እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል።

ድርቅ ያጠቃው የፊንላንድ መሬት አውሮጳምስል Lehtikuva/AFP/Getty Images

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ አምስት ሚሊየን ገደማ ሕጻናት በተጠቀሰው አካባቢ ለከፋ የምግብ እጥረት እንደሚጋለጡም ነው የተነገረው። ከዚህም በላይ በግጭቶች፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ከኮሮና  ወረርሽኝ ማግስት በተከሰተው የኤኮኖሚ ድቀትእና በምግብ ዋጋ መናር ምክንያት 60 ሚሊየን የተገመተ ሕዝብም አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑንም የተመ የረድኤት ድርጅቶች ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ለረዥም ጊዜያት የተጠበቀው ዝናብ በመጋቢት ወር መምጣቱ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት አባል በሆኑት ሃገራት ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ መጠነኛ እፎይታ ያመጣል ተብሎ ቢታሰብም፤ በበርካታ ቦታዎች ጎርፍ ቤቶቻቸውን፣ የእርሻ ማሳቸውና ከብቶቻቸውን ሳይቀር ጠራርጎ መውሰዱን የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO አመልክቷል። ለምግብ ዋስትና የአየር ንብረት ስጋቶች ዋነኛ አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸውን ያመለከtg,ው FAO ለሚከሰተው ጉዳት አስቸኳይ ድጋፍ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሊመጣ ያለውን አስቀድሞ በመገመት መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ የተሻለ እንደሚሆን የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ የምግብ ደህንነት እና የኤኮኖሚ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ ብሬንዳ ላዛረስ ተናግረዋል። ባለሙያዋ አያይዘው ስለ አየር ጠባይ ለውጦች ሲናገሩም፤

የሜድትራኒያን ባሕርምስል Giacomo Zorzi/ Sea-Watch/REUTERS

«ኤሊንኞ ምናልባት እንደ ደቡብ ሱዳን ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍን ስጋት ሊቀንስ ይችል ይሆናል። ስጋቱን በተመለከተ፤ ከአማካኝ በታች የሆነ የዝናብ መጠን እና ድርቅ፣ ግጭት ባሚያስከትለው የምግብ ዋስትና እጦት ተደምሮበት የእርሻ ምርቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖረው፣ ያለውን የምግብ ዋስትና ስጋት ይጨምረዋል። ይኽ ደግሞ ደቡብ ሱዳን፤ ሱዳን፣ በከፊል ኢትዮጵያ እና በአፍሪቃ ምዕራብ ክፍል የሚታይ ነው።»

ይኽን መሰሉ የአየር ጠባይ ክስተት በአፍሪቃ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ ነው በቅርቡ የአውሮጳ ምርምር ማዕከል ይፋ ያደረገው ጥናት የሚያመለክተው። ጥናቱ ከባድ ድርቀት የሜዲትራኒያን ምዕራባዊ ክፍልን እያጠቃ መሆኑን ይገልጻል። በዚህም ምክንያት በአካባቢው ኃይለኛ የውኃ እጥረት መከሰቱን፣ አፈር ርጥበት ማጣቱን፣ የወንዞችም ፍሰት መቀነሱን፣ ይኽ ደግሞ በወሳኝ የዝናብ ወቅት ተክሎች እና የተዘራ እህልን እንደሚያጨናግፍ ጥናቱ ዘርዝሯል።

የሜትሪዎሎጂ ቅኝትምስል StockTrek Images/IMAGO

አብዛኞቹ የምዕራብ ሜዲትራኒያን አካባቢዎች ከዓመት በላይ እጅግ አነስተኛ የዝናብ መጠን እንዳገኙ ነው ጥናቱ የጠቆመው። ይኽ ካልተለመደው ድርቅ እና እጅግ ሞቃት የክረምት እንዲሁም የጸደይ ወራት የአየር ጠባይ ጋር ተዳምሮ ከባድ ድርቅ ያስከተለ ሲሆን በዚህ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወቅት የሙቀት መጠኑም በጣም ሊጨምር እንደሚችልም አመልክቷል። ለምሳሌ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር እስከ የዘንድሮው ሚያዝያ ወር በነበረው ጊዜ ሰሜናዊ ሞሮኮ፣ አልጀሪያ፤ ደቡባዊ ስፔን፣ ደቡብ ፈረንሳይ እና ሰሜናዊ ጣሊያን ከፍተኛ የሙቀት መጠን አስተናግደዋል። ባጠቃላይ አውሮጳ ውስጥም ለረዥም ቀናት የሙቀት ማዕበል በውኃ አካላት መጠናቸው እንዲቀንስ አድርጎ ታይቷል።   ይኽ ደግሞ በእርሻው ዘርፍም ሆነ ኃይል በማመንጨቱ ረገድ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ጥናቱ እንዳመለከተውም በሜዲትራኒያን አካባቢያ የተከሰተው ከባድ ሙቀትና ድርቅ በቀጣይ ከአማካኙ የሙቀት መጠን በላይ ከፍ ያለ ሙቀት ማስከተሉን ይቀጥላል።

ፓስፊክ ውቅያኖስምስል Mario Tama/Getty Images

በኢትዮጵያ የሜትሪዎሎጂ ተቋም ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አሳምነው ተሾመ መሥሪያ ቤታቸው በውኃ አካላት፤ በየብስና በከባቢ አየር ውስጥ የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት በዓመት ሦስት ጊዜ የየወቅቱን የአየር ሁኔታ ለባደ ድርሻ አካላት እንደሚገልጽ አስረድተውናል። እሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያን የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ሲዘጋጁ ከግምት ከሚገቡ ክስተቶች አንዱ የምሥራቅ እና የመካከለኛው የፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሙቀት ይዞታ ነው። የተጠቀሰው ውቅያኖስ የመሞቅ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን በማመልከትም የዝናቡ መጠን የሚቀንስባቸው አካባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የዓለም የምግብ መርሃግብርና የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት ለረዥም ጊዜያት የዘለቀው ድርቅ አሁን በዝናብ መተካቱን፤ ሆኖም ኃይለኛው ዝናብ ጎርፍ ያስከተለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ነው ያመለከቱት። ዶክተር አሳምነውም በሰኔ ወር በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዝናብ መዝነቡን ያረጋግጣሉ። አውሮጳ ውስጥ አራት የየራሳቸው መለያ በግልጽ የሚታይ ወቅቶች ሲኖሩ ኢትዮጵያ በአራት ወራት የተከፋፈሉ ሦስት ወቅቶች አሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW