1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባቡርና አገልግሎቱ

ዓርብ፣ ጥር 27 2014

የኢትዮ ጅቡቲ የመንገደኞች ባቡር ለተገልጋዮች ተደራሽ ባለመሆኑ መንገደኞችን እያጉላላ ነው ተባለ። አንድ የምጣኔሃብት ባለሙያ  በቅርቡ መንግስት ከ3 ሺ በላይ የደረቅ ጭነት መኪኖችን ለማስገባት ማቀዱን ለDW ገልጸው ከዚያ ይልቅ ያለውን የባቡር ኢንቨስትመንት ማጠናከር ይሻል ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

Äthiopien Addis Ababa - Neuer Zug verbindet Hafen und Stadtzentrum
ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር አገልግሎትና ችግሮቹ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮ ጅቡቲ የመንገደኞች ባቡር ለተገልጋዮች ተደራሽ ባለመሆኑ መንገደኞችን እያጉላላ ነው ተባለ።አንድ የምጣኔሃብት ባለሙያ  በቅርቡ መንግስት ከ3 ሺ በላይ የደረቅ ጭነት መኪኖችን ለማስገባት ማቀዱን ለDW ገልጸው ከዚያ ይልቅ ያለውን የባቡር ኢንቨስትመንት ማጠናከር ይሻል ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮ ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ግን የደረቅ ጭነት ማጓጓዝን በየአመቱ እያሻሻለ እንደመጣ በመግለጽ ስራ ያልጀመሩ 12 የመንገደኞች ጣቢያዎችንና ሌሎች አዳዲስ ጣቢያዎችን በመክፈት ችግሩ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚቀርፍ ተናግሯል። 

ከ5 አመታት ግንባታ በኋላ የዛሬ 4 አመት ወደ ስራ የገባው የኢትዮ ጅቡቲ የደረቅ ጭነትና የመንገደኞች ባቡር አዋሽ ክሚገኘው ከአገሪቱ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖና ሞጆ ደረቅ ወደብ ጋር ባለመተሳሰሩ እንዲሁም የመንገደኞች ባቡር ለተገልጋዮች ተደራሽ አለመሆኑ ወቀሳዎች ይሰነዘሩበታል። በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔሃብት  መምህርና በመስኩ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ፍሬዘር ጥላሁን የባቡር ሃዲዱ ከተሞቸን ከማስተሳሰር ባለፈ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው የአገሪቱ የነዳጀ ማጠራቀሚያ የሆነውን የአዋሽ ዲፖንና ሞጆ ደረቅ ወደብን አለማስተሳሰሩ ተገቢ አልነበረም ባይ ናቸው። በቅርቡ መንግሰት ከ3ሺ በላይ የጭነት መኪኖችን ለማስግባት ከማቀድ ይልቅ ባቡሩን ማጠናከር ይሻል ነበር ሲሉም ይከራከራሉ

ምስል Ethiopian railway corporation

የህዝብ ማመላለሻ ባቡር ትኬት መቁረጫ ስፍራዎች እንደ ልብና በቅርብ አለመገኘትንና፣ የባቡር ጣቢያዎቹ ከከተሞች የራቁ መሆናችውንም እንደ ችግር ያነሳሉ የምጣኔሃብት ባለሙያው አቶ ፍሬዘር። 

የኢትዮ ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ በበኩላቸው ኩባንያቸው  400 ኩንታል የሚጭኑ ከ60 እስከ 70 መኪኖች የሚጭኑትን በአንዴ በአንድ ባቡር  የማጓጓዝ አቅም እንዳለው ገልጸው በመኪኖች ከሚደረገውን ምልልስ  ከ30 እስከ 40 በመቶ መሸፈን ከተቻለ ትልቅ ስኬት እንደሆነ የአለም አቀፍ የባቡር ኩባንያዎችን ልምድ በመጥቀስ ያስረዳሉ። በዚህ መስክ ድርጅታቸው በየአመቱ የመጫን አቅሙ ሲጀምር ከነበረው 1 ሚልዮን ቶን አሁን ወደ 2 ሚልዮን ቶን ማደጉን  በመጥቀስ ይህ ማለት ግን  በመኪኖች የሚደረግ ምልልስን ያስቅራል ማለት አደለም ብለዋል።

የባቡር መስመሩ ከነዳጅ ማጠራቅሚያና ደረቅ ወደቦች ጋ አለመተሳሰሩ እንደችግር እንደሚወስዱት የገለጹት ኢንጅነር ጥላሁን ይህ የሆነውም በአገሪቱ የገንዘብ አቅም እጥረትና ከአበዳሪዎች ይገኛል የተባለው ገንዘብ በጊዜው አለመገኘት መሆኑን ይጠቅሳሉ። በአሁኑ ሰአት ግን ሁሉንም ለማስተሳሰር በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬን በኩል ጨረታ ወጥቶ ስራው በሁለት አመታት ይጠናቀቃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸውልናል።

 ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ የሚወስደው የመንገደኞች የባቡር አገልግሎት ለመንገደኞች ተደራሽ ያለመሆኑ በተለይም የባቡር ጣቢያዎች ከከተሞቸ ርቀው መገንባታቸው ተገልጋዮች ትኬት ለመቁረጥ ወደ ባቡር ጣቢያዎች እንዲሄዱ ስለሚገደዱ መጉላላታቸውን ተገልጋዮች ይገልጻሉ። ከተገነቡት 16 ጣቢያዎች አሁን ስራ ላይ ያሉት 4 ብቻ ናቸው። ጉዳዩን አስመልክተን ኢንጅነር ጥላሁንን ጠይቅናችው ባቡር ጣቢያዎቹ ስራ ያልጀሩት በገንዝብ እጥረት እንደነበር ከሪፖርቶች መረዳታቸውን ገልጸው አሁን ግን ከ12ቱ በተጨማሪ ጊዚያዊ ጣቢያዎችን በማቋቋም ጭምር በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስራ ለማስጀመር መታቀዱን ተናግሯል።

የትኬት አገልግሎትን ዲጂታል ለማድረግ 5 ሚልዮን ዶላር መጠየቃቸውን የገለጹት ኢንጅነር ጥላሁን አቅም በፈቀደ ያሉትን ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት ይደረጋል ብሏል። 

የኢትዮ ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማሀበር ኢትዮጵያ 75 በመቶ፣ ጅቡቲ 25 በመቶ ድርሻ በመያዝ ያቋቋሙት ድርጅት ነው።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW