1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ቤተ-እስራኤላዉያን እና ዘመቻ-ሙሴ 40ኛ ዓመት

Azeb Tadesse Hahn
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2017

እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ1984-1985 ከኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤሎች ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ተሰደው በስደተኞች ካምፖች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይህን ተከትሎ የእስራኤል መንግስት ከሱዳን ወደ 8,000 የሚጠጉ የኢትዮጵያ አይሁዶችን በድብቅ ከሱዳን ወደ እስራኤል ለበርካታ ሳምንታት አጓጉዟል።

Israel Jerusalem 2025 | Operation Moses | 40. Jahrestag
ምስል፦ Privat

ቤተ-እስራኤላዉያን እና ዘመቻ-ሙሴ 40ኛ ዓመት

This browser does not support the audio element.

ቤተ-እስራኤላዉያን እና ዘመቻ-ሙሴ 40ኛ ዓመት   

«በተለይ የኛ አብዛኛዉ ማኅበረሰባችን ከኢትዮጵያ በእግር ጉዞ ወደ ሱዳን የተመመዉ በበጋዉ ወቅት የሚፋጀዉ ሙቀት እና ወበቅ በነበረበት ወቅት ነዉ። ሱዳን ድንበር ላይ አምራኮቫ የሚባለዉ ቦታ ምንግዜም በታሪክ የማይረሳን፤ ብዙ ቤተ እስራኤላዉያን የረገፉበት፤ ለወጉ እንኳ አፈር ሳይለብሱ የቀሩበት አጥንታቸዉ እንኳ የት እንዳለ የማይታወቅበት ነዉ። ይህን ለማሰብ ነዉ ዘንድሮ (እ.አ.አ)የካቲት 26 ቀን 2025 ዓ.ም በመንግስታዊ ስርአት 40ኛዉ ዓመት የሙሴ ዘመቻ፤ የተከበረዉ እና የታወሰዉ።»  

ቤተ እስራኤላዉያን ከሱዳን በገፍ እስራኤል ስለገቡበት ስለ ዘመቻ ሙሴ የነገሩን በእስራኤል ሲኖሩ ከአርባ ዓመታት በላይ የሆናቸዉ ቤተ-እስራኤላዊ አቶ ሳሙኤል ምህረት ናቸዉ። በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ ቤተ- እስራኤላዉያን ወደ ተስፋይቱ ሃገር ወደ ሚልዋት እስራኤል በከፍተኛ ቁጥር የገቡበት ዘመቻ ሙሴ 40ኛ ዓመት መጋቢት ወር እየሩሳሌም ላይ በመንግስት ደረጃ ታስቦ ዉልዋል። እስራኤል ከተመሰረተችበት ከጎርጎረሳዉያኑ 1948 ዓመት ወዲህ በዓለም ላይ ተበትነዉ የሚገኙ እስራኤላዉያን ዛሬም ድረስ እስራኤል እየገቡ ነዉ። በኢትዮጵያ ፅዮናዊ አራማጅ እና የአፍሪቃ አይሁዳዉያን የምርምር ጥናት ማዕከል አባል አቶ መስፍን አሰፋ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የሚገኙት ቤተ-እስራኤላዉያን እዉቅና ያገኙት እና ወደ እስራኤል መጓዝ የጀመሩት ከሙሴ ዘመቻ ሁሉ ቀደም ብሎ ነዉ። ሃኑካ እና ቤተ-እስራኤላዉያን በኢትዮጵያ 

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የቤተ-እስራኤላዉያን የፀሎት ቤት - ክራብምስል፦ Privat

የእስራኤል ሊቀ ራባናት የነበሩት ራብ ኦባዲያ ዮሴፍ በ 1973 ዓ.ም ቤተ እስራኤሎች እውነተኛ ይሁዲዎች ናቸው የሚል ሃይማኖታዊ ውሳኔ ማስተላለፋቸዉ ይነገራል። ይህን ውሳኔ የእስራኤል መንግስት ወዲያውኑ ተግባራዊ ሳያደርግ ከቆየ በኋላ በ 1975 ዓ.ም ወደ እስራኤል የመመለስ መብት ያለው ማነው የሚልው አጠቃላይ ሕግ ለቤተ-እስራኤሎችም የሚያገለግል በመሆን ጸደቀ፡፡ እስከ 1977 ዓ.ም እስራኤል ዉስጥ ቁጥራቸው ወደ 200 የሚሆኑ ቤተ- እስራኤላዉያን ይኖሩ እንደነበር የኢትዮጵያ ይሁዲዎች ቅርስ ማዕከል መረጃ ያመለክታል፡፡ አቶ መስፍን አሰፋ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ይሁዲዎችን ጥያቄ ለመደገፍ በተመሠረተው የአሜሪካ ይሁዲወች ማህበር እርዳታ፤ የቤተ-እስራኤሎችን ወኪሎች ወደተለያዩ አገሮች እየወሰዱ በመላው ዓለም የሚገኙ መንግስታትና የይሁዳውያን ድርጅቶች በእስራኤል መንግስት ላይ ግፊት እንዲያደርጉ የተጠናከረ ሥራ አካሄዱ። ከዝያም ነዉ ምናሄም ቤጊን የእሥራኢል ጠቅላይ ሚኒስትር ሁነው ሲመረጡ የመጀመሪው ሙከራ በጎርጎረሳዉያኑ  1977 ዓ.ም ቁጥራቸው 200 የሚሆኑ ቤተ- እስራኤሎች፤ የቤተሰብ ዉህደት በሚል ዉል እስራኤል እንዲመጡ ከስምምነት ተደርሶ እስራኤል የገቡት። 

አቶ ሳሙኤል ምህረት ቤተ-እስራኤላዉያን በትልቁ የሙሴ ዘመቻ እስራኤል ከመግባታቸዉ በፊት ትምህርታቸዉን እንዳጠናቀቁ 32 ወጣቶች ሆነዉ በሱዳን በኩል እስራኤል የገቡት ናቸዉ።በሃማስ ጥቃት በርካታ ቤተ እስራኤላዉያን ተገድለዋል ተባለ  

አቶ ሳሙኤል እና ሌሎች 31 ጓደኞቻቸዉ ለመጀመርያ ጊዜ በሱዳን ድንበር በኩል በእግር ተጉዘዉ ከወጡ በኋላ ለሦስት ወራት መጠለያ ጣብያ ኖረዉ በእስራኤል መንግስት አጋዥነት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1972 ዓ.ም  እስራኤል ገብተዋል። «ሌሎች ሱዳን መጠለያ ጣብያ የነበሩ ቤተ እስራኤላዉያን በትልቁ  የሙሴ ዘመቻ በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1976 ዓ.ም እስራኤል ገብተዋል።»    

እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ1984-1985  በኢትዮጵያ ረሃብ በተከሰተበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤሎች ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ተሰደው በስደተኞች ካምፖች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ይህን ተከትሎ የእስራኤል መንግስት የኢትዮጵያ አይሁድ ስደተኞችን  ከሱዳን ለማስወጣት እና ወደ እስራኤል ለማምጣት ወሰነ። የእስራኤል መንግሥት ወደ 8,000 የሚጠጉ የኢትዮጵያ አይሁዶችን በድብቅ ከሱዳን ወደ እስራኤል ለበርካታ ሳምንታት አጓጉዟል። ቤተ-እስራኤላዉያኑ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ባደረጉት አስቸጋሪ የእግር ጉዞ በሃሩር በዉሃ ጥም በረሃብ በበሽታ እንዲሁም በሽፍቶች ወደ 4,000 ፈላሾች ህይወታቸዉን አጥተዋል። ዘንድሮ እየሩሳሌም ላይ በተካሄደዉ የሙሴ ዘመቻ 40ኛ ዓመት መታሰብያ ላይ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፤ የውህደት ሚኒስትሩ ኦፊር ሶፈር፤ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የማኅበረሰብ ተወካዮች እና የሞሳድ ባለስልጣናት ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይ ቤተ-እስራኤላዉያን ማኅበረሰቦች ለእስራኤል ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

ቤተ-እስራኤላዊት ወጣቶች በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ምስል፦ Privat

የእስራኤል የውህደት ሚኒስትር ኦፊር ሶፈር በሙሴ ዘመቻ ወደ እስራኤል የገቡ ቤተ-እስራኤላዉያን ለሃገሪቱ የማኅበረሰብ ዉህደት ያደረጉት አስተዋጾ እንደ ፅድቅ የሚታዩ ናቸዉ ሲሉ ገልፀዉታል። ቤተ-እስራኤላዉያን ዛሬ በእስራኤል የተለያዩ ኃላፊት ቦታዎች ላይ፤ በዉትድርና፤ በስለላዉ ድርጅት በሞሳድ በወኪልነት፤ በአይሁድ ጉዳይ ድርጅት ሰራተኝነት እና በሌሎች ተለያዩ የፈጠራ ስራዎቻቸዉ ለሃገሪቱ ትልቅ ሃብት ሆነዋል ብለዋል።ቤተ- እስራኤላዉያን ሻናቶቫ

እንደ እስራኤል የውህደት ሚኒስቴር ዘገባ በዘመቻ ሙዜ፤ እስራኤል ከገቡ ቤተ- እስራኤላዉያን መካከል 3,073 የሚሆኑ ሰዎች ዛሬም በህወት አሉ። በዘመቻዉ የገቡ ሰዎች 7,645 ልጆችን ወልደዋል። አብዛኞቹ ህጻናት የተሰጣቸዉ ስም ደሞ ሙሴ፤ አልያም እስራኤል የሚል መጠርያ ነዉ። በሙሴ ዘመቻ ወደ እስራኤል ከተጓዙ ቤተ እስራኤል መካከል አብዛኞቹ የሚኖሩት ኔታንያ ከተማ ላይ ነዉ ። ከዝያ ቀጥሎ ፔታህ ቲክቫ፣ አሽኬሎን እና ሃደራን ከተሞች ላይም የሙሴ ዘመቻ ተጓዥ ቤተ እስራኤላዉያን የሚኖሩባቸዉ ከተሞች ናቸዉ። 

ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ሲጓዙ አልያም ሱዳን መጠለያ ጣብያ በበሽታ፤ በረሃብ እንዲሁም በሽፍቶች እጅ ላለቁ ቤተ-እስራኤላዉያን የቆመ መታሰብያ በእየሩሳሌም ምስል፦ Privat

ከዘመቻ ሙሴ በኋላ በርካታ ቤተ- ኢትዮጵያዉያን እስራኤል ገብተዋል ያሉት በኢትዮጵያ የፅዮናዊ አራማጅ እና የአፍሪቃ አይሁዳዉያን የምርምር ጥናት ማዕከል አባል አቶ መስፍን አሰፋ፤ ከአዲስ አበባ በ 36 ሰዓታት በረራዎች ወደ 14 ሺህ ቤተ እስራኤላዉያን ከኢትዮጵያ የወጡበትን የሰለሞን ዘመቻንም አስታዉሰዋል።እስራኤል፤ ለቤተ-እስራኤላዉያን ደማቅ አቀባበል

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስራኤል ዉስጥ ወደ 160 ሺህ የሚሆኑ ቤተ- እስራኤሎች የኖራሉ፡፡ ከዚህ ቁጥር መካከል 89 ሺህ የሚሆኑት ኢትዮጵያ የተወለዱ ናቸዉ። ወደ 71 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ እስራኤል የተወለዱ ሁለተኛዉ ትዉልድ ቤተ-እስራኤላዉያን ናቸው፡፡

ቃለ ምልልስ የሰጡንን አቶ ሳሙኤል ምህረቱን እና አቶ መስፍን አሰፋን ሙሉ ጥንቅሩን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ  

Azeb Tadesse Hahn Azeb Tadesse
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW