ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ችግርና የተወሰደ ርምጃ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 20 2014
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ክፍል ፀረ ሠላም በሚል ከ130 በላይ ሰዎች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት ርምጃ መውሰዱን ዐስታወቀ። ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ እንደተገለጠው ርምጃው የተወሰደው በክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ድንገተኛ አሰሳ በማድረግ ነው። ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት የሕግ ማስከበር ሥራዎችን በማከናወን 137 ጸረ ሠላም የተባሉ ኃይሎች ላይ ርምጃ መውሰዱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በጉባኤው ተናግረዋል። 16 ያህል ታጣቂዎች ደግሞ መማረካቸውን አክለው ተናግረዋል። በድንገተኛው አሰሳ በርካታ የጦር መሣሪያዎች እና መሣሪያዎችን ክልሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ዐስታውቋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በክልሉ ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የ6 ወር ሥራ አፈጻጸም ዘገባ ባቀረበቡት ወቅት በክልሉ 287 ትምህርት ቤቶች በነበረው የጸጥታ ችግር ወድመት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በዚሁ ምክንያት 104ሺ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው ቆይተዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ሰላም ለማስፈን በተደረገው ጥረት በካማሺ ዞን የነበረው የጸጥታ ችግር በእርቅ መፈታቱ ለሎች አርአያ የሚሆን ነው ያሉ ሲሆን በመተከል ዞንም ተመሳሳይ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድለ ሐሰን በክልሉ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ባቀረቡት የክልሉ ስድት ወር ሪፖርት ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም 287 ትምህርት ቤቶች፣193 የጤና ተቋማት፣1400 በላይ ውሀ መሰረተ ልማቶች፣ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ተቋማት፣የእንስሳት ጤና ከላዎች እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሸከርካሪዎች ላይ ውድመት መድረሱን አብራርተዋል፡፡
በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ባልጀመረባቸው ከ200 በላይ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ለመጀመር ዝጅግት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡ በትምህርት ቤቶች መውደም ምክንያት ከትምህርት ውጪ የነበሩ 104ሺ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
በጤና ዘርፍም የጤና አገልግሎት ሽፋንን ለማሳደግ በመተከል እና ካማሺ ዞን በመገባንት ላይ የነበሩ የጤና ተቋማት በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ስራዎች ተቋርጡ እንደሚገኙ ለምክር ቤቱ ከቀረበው ዘገባ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በጸጥታ ችግሩም 12 ጤና ጣቢያዎች የወደሙ ሲሆን 30 በሚደርሱ አምቡላንሶች ላይም ባለፉት ስድስት ወራት ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ቁልፍ ችግር ተብሎ የተጠቀሰውን የውባ በሽታን ለመከላከልም ዘርፍ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንሚገኙ የገለጸ ሲሆን በተለይም የተፈናቀሉ ዜጎችን ባሉባቸው ወረዳዎች በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኙም አቶ አሻድሊ ሐሰን አብራርተዋል፡፡
የግብርና፣ የገጠር መሬትና ኢንቨስትመንት፣ንግድና ኢንዱስትርን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን ለጉባኤው በቀረበው ዘገባ የተካተቱ ሲሆን፤ በባህላዊ የወርቅ አምራቾች አማካኝነት ከ1ሺ በላይ ኪ.ግ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱም ተገልጿል፡፡
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ