ሳይንስእስያ
ቤንጋሉሩ-የሕንድ መንኮራኩር ጨረቃ ላይ አረፈች
ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 2015ማስታወቂያ
ሕንድ ያመጠቀቻት ሰዉ አልባ የጠፈር መንኮራኩር የጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ክበብ አጠገብ ዛሬ በሰላም አረፈች።በሳንስክሪት ቻንድራያን-3 (የጨረቃ በራሪ እንደማለት ነዉ) የተባለችዉ መንኮራኩር ያለምንም ችግር ጨረቃ ላይ ያረፈችዉ የሩሲያ መንኮራኩር ተመሳሳይ አካባቢ ለማረፍ ስትሞክር ከተከሰከሰች ከሦስት ቀናት በኋላ መሆኑ ነዉ።የሕንድ ሳይንቲስቶች ጨረቃ ላይ መንኮራክር ለማሳረፍ ከዚሕ ቀደም በተደጋጋሚ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም ነበር።አንድ መንኮራኩር በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ አጠገብ ስታርፍ ቻንድራያን-3 የመጀመሪያዋ ናት።መንኮራኩሯ በሳላም ማረፏና ባካባቢዉ ስታርፍ የመጀመሪያዋ መሆኗ በሕዝብ ብዛት ከዓለም የመጀመሪያዉን ደረጃ ለያዘችዉ ሕንድ ታላቅ ኩራት፣ ለሳይቲስቶቹ ከፍተኛ ደስታ ነዉ-የሆነዉ።
«ጌታዬ፣ ጨረቃ ላይ በሳላም አርፈናል።ሕንድ ጨረቃ ላይ ናት።ጌታዬ! የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትር ደስታችንን እንዲካፈሉና እንዲመርቁን እጠይቃለሁ። አመሰግናለሁ።»
ለብሪክስ ጉባኤ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ መንኮራኩሯ ስታርፍ በቀጥታ በቴሌቪዥን ሲከታተሉ ቆይተዉ ማረፏ ሲረጋገጥ የሐገራቸዉን ባንዲራ እያዉለበለቡ መቆጣጠሪያ ክፍል እንደነበሩት ባለሞያዎች ሁሉ በደስታ ፈንድቀዋል።