1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 10 2015

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥነ-ጥበባት ማዕከል ነዉ፤ ማዕከሉ በሥማቸዉ ነዉ የሚጠራዉ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በ 20ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን መግብያ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ታዋቂ የሆኑ ደራሲ እና ዲፕሎማት የነበሩ ሰዉ ናቸዉ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በዘመናቸዉ ከሃያ በላይ ድርሰቶችን ማሳተም የቻሉ ሰዉ ነበሩ።

Photo exhibition of Blata Geta Hiruy W/Selassie in the Ethiopian Academy of Sciences
ምስል፦ Ethiopian Academy of Sciences

የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን የ 84ኛ የዕረፍት መታሰቢያን ተከትሎ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እየታየ ነዉ

This browser does not support the audio element.

«የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በ 20ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን መግብያ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ታዋቂ የሆኑ ደራሲ እና ዲፕሎማት ነበሩ።»

የብላቴ ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ፎቶ አውደ ርዕይምስል፦ Ethiopian Academy of Sciences

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥነ-ጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት፤ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥር የሚገኘዉን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን ማዕከል ለመጎብኘት ወደ ስፍራዉ የመጡ እንግዶችን ተቀብለዉ ስለማዕከሉ ገለፃ ሲያደርጉ የተናገሩት ነዉ። ከወራቶች በፊት የዝግጅት ክፍላችን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥነ-ጥበባት ማዕከልን ሲጎበኝ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት በ 20ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን መግብያ ላይ ስለኖሩት እና ስለ እዉቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ፣ ዲፕሎማት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥራዎች  ፎቶግራፎች እና ታሪካቸዉን በዝርዝር ነበር ገለፃ ያደረጉልን።

የብላቴ ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ፎቶ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚምስል፦ Ethiopian Academy of Sciences

«ይህ ቤት የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ቤት የነበረ አሁን ፤የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥነ-ጥበባት ማዕከል ነዉ፤ ማዕከሉ በሥማቸዉ ነዉ የሚጠራዉ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በ 20ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን መግብያ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ታዋቂ የሆኑ ደራሲ እና ዲፕሎማት የነበሩ ሰዉ ናቸዉ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በዘመናቸዉ ከሃያ በላይ ድርሰቶችን ማሳተም የቻሉ ሰዉ ነበሩ። በዲፕሎማትነት ጃፓንን ጨምሮ በተለያዩ ሃገሮች የኢትዮጵያ ወኪል ሆነዉ ሰርተዋል። ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ አገልግለዋል። የታሪክ መዝገባት እንደሚያሳዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፤ የኖሩት እስከ 1930ዎቹ መጀመርያ ድረስ ነዉ። ከተለያዩ ሃገሮች ከፍተኛ እዉቅና የተቸሩ ዲፕሎማትም ነበሩ። በሚጽፏቸዉ ጽሁፎችም ሆነ በአስተሳሰባቸዉ ከዘመኑ ትንሽ ገፋ ብለዉ ዘመናዊ እና ጥበብ የገባቸዉ እንደነበሩ ይነገራል።»

ይህ አዲስ አበባ የሚገኘዉ ማዕከል በቅርቡ «የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሕይወትና ሥራዎች» በሚል ለአንድ ወር የከፈተዉ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ የፊታችን ጥቅምት 13 ይጠናቀቃል። የአውደ ርዕዩ ዓላማ የክቡር ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን የ 84ኛ የዕረፍት መታሰቢያን ማዕከል በማድረግ ሥራዎቻቸውን ለመዘከር፣ በስማቸው በሚጠራው ማዕከል ሥር የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠገን እንዲሁም ቋሚ ተጨማሪ ቅርስ የሚሆን አሻራን ለማኖር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር ታስቦ መሆኑ ተጠቅሷል። የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት በስልክ እንደነገሩን በአውደ ርዕዩ 40 የሚሆኑ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴን የሥራ እና የሕይወት ጉዞዎች የሚያሳዩ ታሪካዊ ፎቶዎች እንደተካተቱበት ተናግረዋል።  

የብላቴ ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ፎቶ አውደምስል፦ Ethiopian Academy of Sciences

የፎቶግራፍ አዉደ ርዕዩ ለህዝብ ክፍት ከሆነ በኋላ በተካሄደዉ ዉይይት ላይ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘዉዴ በሰጡት ማብራርያ ብላቴን ጌታ ኅሩይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ታዋቂ ዲፕሎማት፣ ደራሲና የግብረገብ መምህር የነበሩ መሆናቸውን፤ በጥንታዊ የሀገር በቀል ዕውቀቶችና  በዓለማቀፋዊ ጉዞና ንባብ የተቀረጹ እንደነበሩ መናገራቸዉ ተዘግቧል፡፡

ብላቴን ጌታ ኅሩይ የሰለጠኑ ሀገራትን ስልጣኔና መልካም ልምዶችን ለመቅሰም ካላቸው ጉጉት የተነሣ አዲስ አበባ  በሚገኘው የስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው የእንግሊዝኛ ቋንቋ መማራቸውን፤ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪም የዐረብኛ ቋንቋን ለማጥናት ሞክረው እንደነበርም አክለዋል፡፡

ኅሩይ በ1920ዎቹ ውስጥ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ከንቲባነት ቀጥሎም በዋና ከንቲባነት ለአራት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከ1903 ዓ.ም እስከ 1926 ዓ.ም ድረስ በአውሮጳ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ በሚገኙ ዘጠኝ ሀገራትን ጎብኝተዋል። የብላቴን ጌታ ኅሩይ ጉብኝቶቻቸውን ለየት የሚያደርገው ከዘጠኙ የጎበኟው ሀገራት መካከል ስለ አምስቱ ሰፋ ያለ ዘገባ መጻፋቸውና ከእነዚህም ውስጥ አራቱን ለህትመት ማብቃታቸውን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘዉዴ ተናግረዋል። 

ብላቴ ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ያስገነቡት ቤትምስል፦ Ethiopian Academy of Sciences

ብላቴን ጌታ ኅሩይ በተደጋጋሚ እንደ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ግብጽ፣ ጣሊያንን እና ፈረንሳይን ብሎም ጃፓንን የመሰሉ የውጭ ሀገራትን መጎብኘታቸውን፤ የሀገራቱንም የስልጣኔ ደረጃ እና የተጠቀሟቸውን አጋጣሚዎች ከሀገራቸው በሥልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት ጋር ባነጻጸሩ ቁጥር የሚሰማቸውን ቁጭት ባገኙት አጋጣሚ ይገልጹ እንደነበር  የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘዉዴ ጠቅሰዋል። ዋና መስርያ ቤቱን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴን መኖርያ ቤት ዋና መቀመጫዉ ካደረገ 10 ዓመት ስለሆነዉ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ እና ስለ ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ወልደሥላሴ  መኖርያ ቤት የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነት በስፋት አስጎብኝተዉናል።

የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ አዲስ አበባ የሚገኝና በባለሞያዎች የተቋቋመ ትልቅ ተቋም ነዉ። በብላቴን ጌታ ኅሩይ የተሰየመዉ የባህል እና የሥነጥበብ ማዕከል ዉስጥ የተለያዩ ህትመቶች ዉይይቶች እንዲሁም የሥነጥበብ እና የፎቶግራፍ አዉደር ርዕዮች ይካሄዳሉ።

ኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

የባህል መድረክ ተከታታዮቻችን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መታሰቢያ የፎቶ አውደ ርዕይ የፊታችን እሁድ ከመጠናቀቁ በፊት አዉደ ርዕዩን እንዲሁም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ስም የተሰየመውን የሥነ ጥበባት ማዕከልን እንድትጎበኙ ይጋብዛል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ጌትነትን እናመሰግናለን።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW