«ብሩኬጋ» ከምንም ተነስቶ የራሱን የንግድ መንደር የመሰረተው ወጣት
ዓርብ፣ መስከረም 16 2018
ከምንም ተነስቶ ራሱን በመቀየር መንደር የመሰረተው ወጣት
ብሩክ በቀለ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 216 ኪ.ሜ. ግድም ርቃ በምትገኘው የጅማ ዞን ሶኮሩ ከተማ ነው፡፡ ብሩክ ኑሮውን ለማሸነፍ በመነሻው እራሱን ያገኘው በአሽከርካሪነት ህይወት ነው፡፡ 200 ኪ.ሜ. ገደማ ርቀት ባለው ወልቂጤ እና ጅማ ከተሞች መካከል በየእለቱ መመላለስም የሰርክ ተግባሩ ነበር፡፡
ታዲያ በዚህን ወቅት ነው ብሩክን አንድ ሃሳብ የመጣለት፡፡ ከወልቂጤ ወደ ጅማ ተሳፋሪዎችን አሳፍሮ ሲመላለስ ሁል ጊዜም እኩሌታ ቦታ በሆነው አንድ ገደላማ ምድረበዳ ስፍራ ሰዎች ከጉዞው እረፍት ለመውሰድ እና ለመጸዳዳት የሚመርጡትን ቦታ ወደ ስራ ሃሳብ መቀየር የሚል፡፡ ጅማሮው ግን ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ ስፍራ ምንም ነዋሪ ያለበት አከባቢ አይደለም፡፡ ቦታው ገደላማ በመሆኑ ለኑሮም አይመረጥም፡፡ ጭው ያለ ሰው አልባ ቋጥኝ እና ጫካ ብቻ የሆነው ስፍራ ቁልቁል ይታያል፡፡
ወጣቱ ሾፌር ግን የማይፈለግ የሚመስለውን ይህን ቦታ ለዓመታት ሲመላለስበት እንዴት አድርጎ ወደ ስራ መቀየር እንደሚችል ብቻ ያወጣል ፣ያወርዳል ፡፡ በሃሳቡም ተገድቦ አልቀረም፡፡ ባለቤቱን ያወያያታል፡፡ ማወያየት ግን ማሳመን አይደለምና ሰው በሌለበት በዚህ ስፍራ የስራ ሃሳብ ማምጣት፤ እየሰሩም በዚያው መኖር በሚለው ለማሳመን ነገሮች ቀላል አልነበሩም፡ ይላል ወጣቱ ስራ ፈጣሪ የመነሻውን ክብደት ስያስረዳ፡፡ “መስመርተኛ ሾፌር ነበርኩኝ፡፡ ከወልቂጤ ጅማ ነበር የምሰራው፡፡ ከባለቤቴ ጋር መፀዳጃ ቤት ለመስራት ነበር ተማክረን ወደዚህ የገባነው” ይላል፡፡ ይህ ሃሳብ ስፈልቅ ግን አንድ ጽኑ እምነት አለ፡፡ ለመለወጥ ጠንክሮ መስራት የሚል የለውጥ መንገድ፡፡ በዚህ ቦታ መጸዳጃ በመስራት ሰዎችን ለማስጠቀም የታሰበው ደግሞ ቦታው በጅማ እና ወልቂጤ መሃል እኩሌታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ሰዎች ሁሌም ቢሆን በዚህ ስፍራ ያርፋሉ፡፡
የሃሳቡ ጥንስስ መነሻ
ኢትዮጵያ ውስጥ ያ ገደላማ፤ ተስፋም የማይታይበት ዓለታማ ስፍራ ለመንገደኞች መጸዳጃ ካልሆነ ለምን ይረባል የተባለለት ስፍራ አሁን ወደ ከተማነት ተቀይሯል፡፡ ከየትም አቅጣጫ ወደ ጅማ እና አዲስ አበባ መስመር የሚመላለሱ መንገደኞች ከትራንስፖርት ወርደው ሳይረግጡት የማያልፉት መብራትም ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሁሉ የሚገኝበት ትልቅ መንደር፡፡ ይህ ግን በዋዛ አልመጣም፡፡ “ጫካ ነበር በጣም፤ 12 ሰዓት ነበር ጅብም የሚወጣ ከዚህ፡፡ መብራትም የለው ተስፋ የሚስቆርጥ ጫካና በረሃማ ስፍራ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ከተማ ሆኗልና ወደዚህ የሚያመጣው ጠንክሮ መስራት ነው” ሲል ብቻውን ትልቅ መንደር የመሰረተ ወጣት ብሩክ በስራ አከባቢውን ለመቀየር ስላስፈለገው ጽናትና ብርታቱ አስረድቷል፡፡
ወደዚህ በመምጣት፤ አዲስ የስራ ሃሳብንም ለማመንጨት፤ እስኪያልፍ ያለፋልና ለዚም ለመዘጋጀት፤ ደግሞ ሰው በማይኖርበት፣ አውሬው በሚያስፈራበት አዲሱን የህይወት ፈተና ለመጋፈጥ ራስን እንኳ ማሳመን አይቀልምና እንዴት የህይወት አጋርህን ልታሳምን ቻልክ? ለብሩክ ያቀረብንለት ጥያቄ ነበር፡፡ “በእውነት አዎ፤ መጀመሪያም እሷን ማሳመን ግድ ነበር፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብምና እሷን በማሳመን እሷ ጠንካራ እንድትሆንልኝ ነበር ሃሳቤ፡፡ እንዴት ከሰው ተነጥለን በዚህ በጫካው እንኖራለን የሚል ሃሳብ ነበር የምታቀርብልኝ፡፡ አምና ከተቀበለችኝ በኋላ ግን እሷም ከኔ በላይ ጸንታ እየተበረታታን ለዚህ ደረጃ በቅተናል” ከራስ አልፎ አከባቢውን ስለቀየረው ስኬታማ መንገድ ለመምጣት መንገዱንም ለመጀመር ቀላል እንዳልነበር አስረዳ፡፡
መነሻ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት…
ብሩክ ከባለቤቱ ጋር ተያይዘው ወደዚህች በረሃማ ስፍራ ስመጡ ከጅማ ወልቅጤ ይመላለስባት ከነበረው 12 ሰዎችን የመጫን አቅም ካላት ሚኒባስ ተሽከርካሪ ውጪ ምንም አልነበራቸውም፡፡ ከሰው የተበደረውን ጨምሮ በአነስተኛ የመነሻ ካፒታል በመነሳት ግን አሁን ላይ ከራስም አልፎ መንደሩ ሁሉ ገቢያን በማግኘት የተቀየሩበት አነስተኛ ከተማ የምትመስል መንደር ተመስሪታ መንገደኞች ሁሉ የሚያርፉበት ስፍራን ፈጥሯልና በሂደቱ ውስጥ የርሱም ህይወት የገቢውም ምንጭ እንዲሁ በብዙ ተመንድጓል፡፡ “ወደዚህ ስገባ አንድ አሮጌ 5-ኤል ሚኒባስ ተሽሸከርካሪና 60 ሺህ ብር ብቻ ነበር ይዤ የገባሁት፡፡ 40 ሺውን ደግሞ ከሰው ነበር የተበደርኩት፡፡ አሁን ግን እግዚአብሔር ይመስገን ከምንም ከማንም በላይ ሰርተን የለፋንበትን ከሚገባንም በላይ አትርፈንበታል” በማለት ከገቢውም ማደግ በበለጠ የሰዎችን እርካታ እየተመለከቱ እንደሚደሰቱም ያስረዳል፡፡
በዚህ መስመር መንገደኞች ሁሉ ጊቤን ስሻገሩ ለሾፌር አንድ ነገር ያሳስባሉ፡፡ ብሩክ ጋር አሳርፈን የሚል፡፡ በዚያም ብሩክ የሚል መጠሪያም ያገኘው በዚያ ስፍራ የብሩክን ሽሮ ሳያጣጥም ማለፍ የሚፈልግ ማን አለ፤ ደግሞም በዚህ ማረፊያ አንድ ህግ አለ፡፡ ያልተጻፈ ህግ፡፡ በዚህ ብሩክ ማረፊያ የሚዘጋጀው ምግብ ሁሉ የመንገደኞችን የሃይማኖት ስብጥር ከግንዛቤ ያስገባ የሚል ነው፡፡ “ምግባችን ሙስሊም ክርስቲያንን ያማከለ ነው፡፡ አትክት፣ ሽሮ እና አሳ ነገር ካልሆነ በዚህ ቤት ስጋ አይገባም” ይላል፡፡ እናም ከማለዳ 12 እስከ ምሽት 4 ሰኣት ደንበኞች በሚፈሱባት በዚህች የቀድሞ በረሃማ የአሁኑ ደግሞ ሞቅ ባለች መንደር አገልግሎት ለመስጠት የምንደፋደፉ ከ35 በላይ ሰራተኞች በዚህ በብሩክ ቤት ብቻ አሉ፡፡
የአከባቢው ነዋሪዎች አስተያየት
በጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ በአከባቢው የምትገኘው የናትሪ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሱልጣን አባቡልጉ የ60 ዓመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት በኖሩበት በዚህ ስፍራ ያላዩት ያላሳለፉትም የለም፡፡ ወጣት ብሩክ ወደ አከባቢያቸው መጥቶ መንደሩን በሙሉ ስለቀየረበት ብርቱ ስራው የሚያስታውሱትንም አጋሩን፡፡ “ያቺ ብሩክ ያለባት ቦታ በጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ ደደርከታ ቀበሌ ልዩ ቦታዋ ደሚሲ ትባላለች፡፡ ቦታው መጀመሪያ በጣም ከባድ በረሃማና ዋሻ ሁሉ ያለበት ከባድ ስፍራ ነበር፡፡ የሌባና አውሬ ማከማቻ ቦታም የነበረ ነው፡፡ ብሩክ የሚባለው ልጅ መጥቶ ግን በዚያሻይ ቡና ጀመረ፡፡ በጣም ሰው የሚወድ ሰውም የሚወደው ልጅ ነው፡፡ የአከባቢውን ልጆች በማደራጀት ሁሉም የሚጠቀምበት ስራ ፈጥሮ ወደ ስራ ገባ” ሲሉ የስኬቱን የጅማሮ ዓመታት አስታወሱ፡፡
የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ቅድሚያ መስጠት
በአከባቢው ተደማጭነት ያላቸው አባገዳና የአገር ሽማግሌ የሆኑት ሱልታን አባቡልጉ ወጣቱ የስራ ፈጣራ ባለቤት አከባቢውን የቀየረበትና በአከባቢው ላይ ስለፈጠረው ተጽእኖም ስያብራሩ፤ “በአከባቢው ላይ ተወዳጅነት ያለው ሰው ነው፤ በተለይም ምስትየው ብርቱ ትባላለች፤ ሁለቱም ጠንክረው ስሰሩ ሰራተኛ እንጂ ምናቸውም ያን ሁሉ ያፈሩ ባለሃብት አይመስሉም” ይላሉ፡፡ በራሱ ትራንስፎርመር በማቆም ለአከባቢው ማህበረሰብ በነጻ ማብራት ከማከፋፈል ጀምሮ የበርካታ ማህበራዊ ችግሮች ዘብ ነው የሚሉትን ብሩክን ማህበረሰቡ ስቸከር እንደባንክ እንደ ዋስም በወጣቱ የስራ ፈጠራ ባለቤትን መከታው እንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡ ከመንገድ እስከ ልዩ ልዩ የማህበረሰቡ የጋራ መጠቀሚያ ልማቶችም ላይ ወጣቱ ብሩክ ተሳትፎ በማድረግ ከራሱም አልፎ አከባቢውን የቀየረበትን መንገድም አቶ ሱልጣን አውርተው አይጠግቡም፡፡
የሃይማኖትን እኩልነትና ማህበረሰቡን ከነማንነቱ መቀበልና ማክበር ሌላው የስራ ፈጠራ ባለቤት ወጣቱ መገለጫ ነው ይላሉ አስተያየት ሰጪው የአከባቢው ሽማግሌ፡፡ ብሩክም ይላል፤ “ሁሉም ደስተኛ ነው ለሙስሊሙ መስጂድ፤ ለክርስቲያኑም ቤተክርስቲያን አብሬን ቆመን እናሰራለን፡፡ ለእምነት ተቋማቱም በግል ማብራት አስገብተናል”፡፡
ከራስ አልፎ ለሌሎችም ስራ መፍጥር
ወጣት ዑስማን አሊ፤ የወጣቱ ስራ ፈጠራ ባለሙያ የብሩክ ጓደኛም፤ የስራ እድሉ ተቋዳሽም የአከባቢው ነዋሪ ነው፡፡ “እሱ ሾፌር በነበረበት ወቅት እኔ ከሱ ጋር በረዳትነት ነበር ምሰራው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሄን ቦታ ሁሌም ማልማት እንደምፈልግ ይናገር ነበር፡፡ እንደውም ሁሌም የምላት አባባል ነበረችው፤ ይህ ቦታ ነዳጅ ነዳጅ ይሸተኛልና ነዳጅ እናወጣበታለን፤ ከዚያን መኪናውን ሽጦ ከትንሽ ነገር በመጀመር በዚህ ስፍራ ይህን ትልቅ ከተማ መስርቷል፡፡ የብዙዎቻችንም ህይወት ቀይሯል፡፡ እሱን ለመግለጽም ቃላት የለኝም” ሲል ስለጓደኛውና አለቃው ስላለው አክብሮት ዘርዝሯል፡፡
ወጣት ኤርሚያስ አስመላሽ ደግሞ በተፈጠረለት የጎሚስታ ስራ ተጠቃሚ ነው፡፡ “እኔ ሱስ ተጠቂ ነበርኩ፤ ከከተማው ነበር የሚውለው ሶኮሩ ከተማ፡፡ እሱ ነው አምጥቶ ጎሚስታ ከፍቶ እንዲህ የሚያሰራኝ፡፡ ምግብም ከዚሁ በከራሱ ቤት ነው የምጠቀመው፤ ብዙዎቻችንን ቀይሯል” ሲል አስተያየቱን አጋራን፡፡
ቁርጠኝነት ካለ ለውጥ አይቀረ ነው…
የብዙዎች ምሳሌ፤ ደግሞም ማህበረሰብን የቀየረና በመቀየርም ላይ ያለ፤ ማህበረሰቡም ምስክርነት የሚወጣለት ወጣቱ እራሱንእና ሌሎችንም የቀየረበትን በመነሻው ከባድም ይመስል የነበረውን የስራ ዘርፍ ደግሞ በሚከብድ ስፍራ ለመጀመሩ ምክንያት የሆነውን ስገልጽ፤ “እኔ ልጅ እያለሁ ነበር ወላጆቼ የሞቱት፡፡ ድህነት አስከፊ መሆኑን በሚገባው አውቀዋለሁ፤ እናም ጠንክሬ መስራት እንዳለብኝ ስላወቅኩ ነው ወደዚህ መጥቼ ስራ የጀመርኩ” ይላል፡፡ በስራው ውጤታማ መሆኑን የገለጸው ብሩክ ከሚያገኘው በቂ ገቢያ ገቢውም እያደገ መሄዱን ያስረዳል፡፡ እናም የትኛውም ወጣት ከሰራ መቀየሩ ለጥርጣሬም የማይቀርብ ሃቅ እንደሆነ ከራሱ ልምድ ያጋራል፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ