ብሪታንያ ፣ ሕገ ወጥ ተገን ጠያቂዎችን ለመከላከል ያወጣችው እቅድ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2017
የብሪታንያ መንግስት በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ብሪታንያ የሚሰደዱ ሕገ-ወጥ የሚላቸው ተገን ጠያቂዎችን የሚያስተናግድበት መንገድ ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ መሰንዘር ከጀመረ ሰነበተ። በተለይ ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያለ ተገን ጠያቂዎችን በሌበር ፓርቲ የሚመራው አዲሱ መንግሥት በሆቴሎች ማስቀመጡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ከቀሰቀሰ ከረመ ። መውደቂያ ያጡ የብሪታንያ ዜጎች እያሉ መንግስት ተገን ጠያቂዎችን እንዴት በሆቴሎች አንፈላሶ ያስቀምጣል፣ የሚሉ ዜጎች ለበርካታ ሳምንታት በተከታታይ በተለያዩ ከተሞች አደባባይ እየወጡ ፣ንዴት ምሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። የፍልሰተኞችን ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ስደተኛ-ጠል የሚባሉ ቀኝ አክራሪ ፖርቲዎችም ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት ነው።
ይህ እየተባባሰ የሄደው ደግሞ አንድ ኢትዮጵያዊ ተገን ጠያቂ በአንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድና በምትረዳው ሌላ አዋቂ ሴት ላይ ወሲባዊ ጥቃትና ትንኮሳ በመፈጸም ከተጠረጠረ በኋላ ነበር። ተገን ጠያቂ ባለፈው ሳምንት በቀረበበት የለንደን ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል። ፍርድቤቱ በመስከረም በተከሳሹ ላይ ብይን እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የብሪታንያ መንግሥትም ተገን ጠያቂዎችን በሆቴሎች ማስቀመጥን ለማስቆም ያወጣውን እቅድ እንደሚያፋጥን አስታውቋል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ስለዚሁ ጉዳይ በሰጡት መልስ መንግስታቸው ያቀደውን ተናግረዋል።
«ተገን ጠያቂዎች የሚያርፉባቸውን ሆቴሎች በተመለከተ ከነርሱ ነጻ እንዲሆኑ ነው የምፈልገው። ይህን ጉዳይ በእውነት ግልጽ አድርጌያለሁ። ህዝቡ ለምን እንደሚሰጋ ሙሉ በሙሉ እረዳለሁ። ሆቴሎቹን ከተገን ጠያቂዎች ነጻ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ ስርዓት በያዘ ስልታዊ አሰራር የተገን ጠያቂዎቹን ጉዳዮች በተቻለ መጠን በፍጥነት መመልከት እና ከዚያም እዚህ መቆየት የማይገባቸውን መመለስ ነው።»
በብሪታንያ ፍልሰት አሁን ዋነኛ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኗል። ካለፈው ጥር ወር ወዲህ 28 ሺህ ተገን ጠያቂዎች በትናንሽ ጀልባዎች ብሪታንያ ገብተዋል። ስደተኞች ወደ ብሪታንያ መፍለሳቸው አዲስ ባይሆንም ከቀድሞው በላቀ በአሁኑ ጊዜ በብሪታንያ የስደተኞች ጉዳይ ለምን ይበልጥ ትኩረት ሊስብ ቻለ? የለንደኑ ዘጋቢያችን ድልነሳው ጌታነህ ለዚህ ምክንያት የሚባሉትን ዘርዝሯል።
ተገን ጠያቂዎች በሆቴሎች መቀመጣቸውን የሚተቹ ወገኖች ወጪን የሚያበዛ አሰራርና ኅብረተሰቡንም ለአደጋ የሚያጋልጥ በማለት በአንዳንድ ስደተኞች የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃትን የመሳሰሉ ከባድ ወንጀሎችን ይጠቅሳሉ ይሁንና ስደተኞችን የሚደግፉት ወገኖች ደግሞ፣ ከዚህ አትራፊ መሆን የሚፈልጉ የሚሏቸውን ፖለቲከኞችና ቀኝ ጽንፈኛ ቡድኖችን አጋጣሚውን በመጠቀም ሆነ ብለው ውጥረቱን በማባባስ ይከሷቸዋል። በዚህ እንቅስቃሴ ከሚተቹት አንዱ ሪፎርም የተባለ ፓርቲ የመሰረቱት ናይጅል ፋራጅ የተባሉት ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ ናቸው። ድልነሳው እንደገለጸው በቅርቡ የተመሰረተው ይህ የፋራጅ ፓርቲ አሁን በተፈጠረው ግርግር ብዙ ደጋፊዎች ለማግኘት በቅቷል። በመጪው ምርጫም አሸናፊ እንደሚሆን ከወዲሁ በልበ ሙሉነት እየተናገረ ነው።
በዚህ መሀል መንግስት ለህዝቡ ተቃውሞ መልስ ለመስጠት ወደፊት ተገን ጠያቂዎችን በወታደራዊ ተቋማት አካባቢ ለማስፈር እያሰበ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከዚህ ሌላ በቅርቡ በተደረገው ሹም ሽር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሻባና መሐመድ ብሪታንያ ስደተኞችን አንወስድም በሚሉ ሀገራት ዜጎች ላይ የቪዛ ገደብ ልትጥል እንደምትችልም ጠቁመዋል። ሚኒስትሯ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ብሪታንያ የሚካሄድን ስደት ለማስቆም የማይቆፍሩት ድንጋይ እንደሌለም ነው የተናገሩት።
ሚኒስትሯ መንግስታቸው ወደፊት ሊወስዳቸው ያሰባቸውን እርምጃዎች የተናገሩት ፣የናጃል ፋራጅ ሪፎርም ፓርቲ በአምስት ዓመታት ከ600 መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን ከብሪታንያ ለመጠረዝ የገንዘብ ማበረታቻ እና የቪዛ ገደቦችን ጨምሮ ስደተኞች ለመመለስ የሚያስችሉ አስተማማኝ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ቃል ከገባ በኋላ ነው። እርሳቸው ግን ፣ይህ የሌበር መንግሥት ከዚህ ቀደምም ሲያስብበት የቆየ ጉዳይ ነው በማለት ሀሳቡ የፓርቲያችን ነው ብለዋል።
ባለፈው ቅዳሜ ብቻ በዚህ መስመር 1097 ሰዎች ብሪታንያ ገብተዋል ።ይህም በብሪታንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. ብሪታንያ የገቡት ሕገ ወጥ የሚባሉ ተገን ጠያቂዎችን ቁጥር ወደ 30,100 ከፍ አድርጓል። ምንም እንኳን የሪፎርም ዓይነት አቋም የሚያራምዱ ፓርቲዎችና ቡድኖች ጥያቄ በተገን ጠያቂዎች ደረሱ በሚሏቸው ችግሮች ላይ ያተኮሩ ቢሆንም መረጃዎቻቸውና ጥያቄዎቻቸው ሲመረመሩ ግን ከእውነት የራቁ መሆናቸውን አንድ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት አመልክቷል።
የፊታችን ቅዳሜ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር መስከረም 13 ቁጥሩ ከሚሊዮኖች በላይ የሆነ ህዝብ ይሳተፍበታል የተባለ ስደተኞች እንዲባረሩ የሚጠይቅ ቀኝ አክራሪዎች የጠሩት ሰልፍ በብሪታንያ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።በዚህ ወቅት የውጭ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እና አላስፈላጊ የሆኑ ቦታዎች ላይ እንዳይገኙ ማሳሰቢያዎች እየተሰጡ መሆኑንም ድልነሳው ገልጿል።
ኂሩት መለሰ
ምንተጋፍቶት ስለሺ