1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ብሪታንያ የጀልባ ስደተኞች እንዳይመጡባት ያወጣችው እቅድና ትችቱ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12 2015

ብሪታንያ ያረቀቀችው አዲስ ሕግ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ከብሪታንያ አባሮ ወደ ሩዋንዳ ወይም ወደ ሌላ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሦስተኛ ሀገር እንዲላኩ የሚያደርግ ነው።ብሪታንያ በተለይ በጀልባ የሚመጡ ስደተኞችን አስገድዳ ከሀገርዋ ለማባረር የምታደርገው ዝግጅት በስደተኞችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በእጅጉ መተቸቱ ቀጥሏል።

Flucht über den Ärmelkanal
ምስል፦ Dan Kitwood/Getty Images

ብሪታንያ የጀልባ ስደተኞች እንዳይመጡባት ያወጣችው እቅድና ትችቱ

This browser does not support the audio element.

በጀልባ ወደ ብሪታንያ የሚመጡ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ለማስቆም መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ አቅዷል። መንግሥት ስደተኞቹን ወደመጡበት ወይም ወደ ሌላ ሦስተኛ ሀገር ለመመለስ ያስችላል የተባለ አዲስ ሕግ አርቅቋል። ረቂቁ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን በመጣስ ተተችቷል። ደቡብ ብሪታንያንና ሰሜን ፈረንሳይን በሚለየው «ኢንግሊሽ ቻናል» ተብሎ በሚጠራው በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኘው መተላለፊያ በኩል በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ብሪታንያ የሚደረግ ስደትን ለማስቆም የብሪታንያ መንግሥት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ከአምስት ወራት በፊት ስልጣን ሲይዙ ቃል ከገቡዋቸው ጉዳዮች ውስጥ እነዚህን የጀልባ ስደተኞች ማስቆም አንዱ ነበር። በዚሁ መሠረት ብሪታንያ እነዚህ ስደተኞች ወደ ሀገርዋ ዝር እንዳይሉ አዳዲስ እቅዶችን አውጥታለች። ከመካከላቸው በዚህ መስመር በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ብሪታንያ የሚገቡ መንግሥት ሕገ ወጥ የሚላቸው ስደተኞችን የማስቆም ዓላማ ያለው ረቂቅ ሕግ አንዱ ነው። ከዚህ ሌላ መንግሥት በዚህ መስመር የሚካሄድ ስደትን ለመከላከል የስደተኞቹ መሸጋገሪያ ከሆነችው ከፈረንሳይ ጋርም ስምምነት ላይ ደርሷል። ከአንድ ዓመት በፊት በጀልባ የሚመጡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ለንደን ከኪጋሊ ጋር የደረሰችበት ስምምነትም በቅርቡ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።  ባለፈው ቅዳሜ ኪጋሊ ውስጥ ከሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፓውል ካጋሜና ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቨንሰንት ቢሩታ ጋር በጉዳዩ ላይ የመከሩት የብሪታንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ስዌላ ብሬቨርማን ሩዋንዳ ስደተኞቹን ለመቀበል የሚያስችሏትን ዝግጅግቶች እያጠናቀቀች ነውብለዋል። 
«ሂደቱ እየፈጠነ ነው። እዚህ ኪጋሊ ተገኝቼ እንዳየሁት ከዓለም ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዘው ይህ ስምምነት በጣም በጣም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን በጣም እተማመናለሁ። ዛሬ እንዳየነው ደረጃቸው የላቀ ፣ደኅንነታቸው የተጠበቀ፣ ስደተኞች በዘላቂነት ሊኖሩባቸው የሚችሉ ቤቶች ተገንብተዋል፤»
ለስደተኞቹ ማኖሪያ የታሰበውን ስፍራ የጎበኙት ብሬቨርማን በሌላ ቦታም ለሚሰራ የስደተኞች ማቆያም የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል። በዚህ ፕሮጀክት በሩዋንዳ ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል። የብሪታንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚለው በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ማባረሩ ሊጀመር ይችላል። ብሪታንያ 170 ሚሊዮን ዩሮ የምታወጣበት ይህ እቅድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ግን የብሪታንያ ፍርድ ቤቶች አወዛጋቢው ፖሊሲ ሕጋዊ ነው ብለው ውሳኔ ካሳለፉ ብቻ ነው። ታዲያ ሩዋንዳ ሳይፈልጉ በግድ ብሪታንያ ያባረረቻቸው ስደተኞች ተቀባይ መሆኗ  የሀገሪቱን ፖለቲከኞች ማነጋገሩ አልቀረም። ከሩዋንዳ አረንጓዴ ፓርቲ ዶክተር ፍራንክ ሀቢኔዛ ጉዳዩ የሩዋንዳ ሃላፊነት አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ። 
«ይህን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። እንደ ፓርቲ ስደተኞቹ መምጣታቸውን አንቃወምም። ምክንያቱም እኛ ከኮንጎም ከብሩንዲም ይሁን ከሌላ ቦታ የሚሰደዱት ወደው ሩዋንዳ እስከመጡ ድረስ መምጣታቸውን እንደግፋለን። ከብሪታንያ የሚመጡት ግን ሩዋንዳ መሄድን አልመረጡም። የተሰደዱት ብሪታንያ ነው። ስለዚህ የነርሱ ጉዳይ የኛ ሃላፊነት አይደለም። »
የብሪታንያ መንግሥት እንደሚለው ባለፈው ጎሮጎሮሳዊው 2022 ዓም 45,755 ስደተኞች በእንግሊሽ ቻናል በኩል ብሪታንያ ገብተዋል። አብዛኛዎቹም በብሪታንያ ተገን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ባለፉት ሦስት ወራት ደግሞ ቁጥራቸው ወደ 3ሺህ የሚጠጋ ስደተኞች በተመሳሳይ መንገድ ብሪታንያ ደርሰዋል። በዚህ መስመር ወደ ሀገርዋ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል የሚል ስጋት አለኝ የምትለው ብሪታንያ ያረቀቀችው አዲስ ሕግ  በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ከብሪታንያ አባሮ ወደ ሩዋንዳ ወይም ወደ ሌላ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሦስተኛ ሀገር እንዲልክ ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሃላፊነቱን ሰጥቷል።ሕገ ወጥ የተባሉት ስደተኞች ተይዘው በሚቆዩባቸው የመጀመሪያዎቹ 28 ቀናት ዋስትና የማግኘትም ሆነ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የሚታይበት መብትም አይኖራቸውም። በዚህ ዓይነት መንገድ ከብሪታንያ የተባረሩ ስደተኞች ወደፊት ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ ወይም የብሪታንያ ዜግነት እንዳያገኙ አዲሱ ረቂቅ ሕግ ያግዳል። ሕጉ ከጸደቀም ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 7 ቀን ማለትም ከዛሬ 14 ቀናት ወዲህ በሕገ ወጥ መንገድ ብሪታንያ የገቡ ስደተኞች ላይ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።

ምስል፦ Stefan Rousseau/Getty Images
ምስል፦ Dan Kitwood/Getty Images

ብሪታንያ በተለይ በጀልባ የሚመጡ ስደተኞችን አስገድዳ ከሀገርዋ ለማባረር የምታደርገው ዝግጅት በስደተኞችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘንድ በእጅጉ መተቸቱ ቀጥሏል። ዴቪድ ኮንዶር የስደተኞች ሕግ አዋቂ ናቸው። ብሪታንያ ስደተኞችን በኃይል ከሀገርዋ ለማባረር የምትወስዳቸው እርምጃዎች በአውሮጳ ደረጃ ስደተኞችን በሚመለከት የተደረሰባቸውን ስምምነቶች የሚጻረር ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ኮንደር በተለይ ሰው ከሀገሩ መሰደድ ያለበት በዚህ ዓይነት መንገድ ነው የሚል ደንብ የለም ይላሉ።
«በስደተኛ ደንብ መሠረት በዚህ መንገድ የመጣ ስደተኛ ነው የምንቀበለው የሚል ደንብ የለም። ይልቁንም በሕገ ወጥ መንገድ የሚመጡ ስደተኞች በተለዩ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር መቀጣት እንደሌለባቸው በስደተኞች ጉዳይ ስምምነቶች ውስጥ በጣም ግልጽ ተደርጓል። ስለዚህ በእርግጠኝነት ይህ የአውሮጳ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን መንፈስ የሚጻረር ነው። »
በብሪታንያ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተጠሪ ቪኪ ቴናንትም አዲሱ የብሪታንያ የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ሕግ ስምምነቶችን የሚጥስ ነው ብለዋል።የብሪታንያ መንግሥት ግን ሕጉ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጻረር አይደለም ሲል ያስተባብላል።
«ይህ በትክክለኛነት በሕገ ወጥ መንገድ ብሪታንያ ለሚገቡ ስደተኞች ጥገኝነት እንዳይሰጥ ያለውን እድል በሙሉ መዝጋት ነው። በኛ እምነት ይህ የስደተኞች ጉዳይ ስምምነትን በግልጽ መጣስ ነው። 
የብሪታንያ መንግሥት ሕገ ወጥ የሚለውን ስደት ለማስቆም ያቀዳቸው እርምጃዎች በቢቢሲ ቴሌቪዥን የስፖርት ጋዜጠኛ ጋሪ ሊኒከር ሳይቀር ጠንካራ ትችት ተሰንዝሮበታል።የቀድሞው የቶንተምሀም የእግር ኳስ ቡድንና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሊኒከር በትዊተር ያሰፈረው ተቃውሞ ከስራው እስከ መታገድ አድርሶት እንደነበር የዶቼቬለ የለንደን ዘጋቢ ድልነሳው ጌታሁን ያስታውሳል።  ድልነሳው እንደሚለው የብሪታንያ ህዝብ ደግሞ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ለሁለት የተከፈለ አቋም ነው ያለው .

ምስል፦ Kin Cheung/AP/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW