ብሪክስ ለአፍሪካዉያን የሚገባቸውን ቦታ ይሰጣቸው ይሆን?
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 16 2017የደቡብ አፍሪቃን መንገድ የተከተሉት ኢትዮጵያ እና ግብጽ ሩስያ ባስተናገደችው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
በብራዚል ፣ ሩሲያ ፣ ህንድ ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት የተመሰረተው ብሪክስ አሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢራን ፣ ግብጽ ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ሳኡዲ አረቢያን በማካተት የአባላቱን ቁጥር 10 ሲያደርስ ቱርክ ፣ አዛርባጃን ማሌዢያ ቡድኑን ለመቀላቀል ማመልከቻቸውን አስገብተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ብሪክስ በተለያየ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዎ ፍላጎቶች ባላቸው ሃገራት ጥምረት መፍጠሩ እንደምን ወጥ የሆነ አቋም መያዝ ያስችለዋል የሚል ጥያቄ የማስተናገዱን ያህል አፍሪቃዉያንን ጨምሮ በርካታ በኤኮኖሚ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ሊቀላቀሉት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ሲታይ ቀስ በቀስ ምናልባትም ትልቅ ዓለማቀፍ ተቋም ወደ መሆን እየተንደረደረ መሆኑን ሳያሳይ አልቀረም ።
ሩስያ በደቡባዊ ከተማዋ ካዛን ባስተናገደችው የሶስት ቀናት የመሪዎች ጉባኤ አባል ሃገራት የፋይናንስ ትብብርን ለማጠናከር እና በምዕራባዉያን ቁጥጥር ስር ካሉት የክፍያ ስረዓቶች አማራጮችን ለማዘጋጀት የሚያስችል ዕቅድ ላይ እንዲመክሩበት መድረክ ፈጥሮላቸዋል።
ኢትዮጵያ በይፋ ብሪክስን ስትቀላቀል ባለሙያዎች ስለ ፋይዳው ጥርጣሬ ገብቷቸዋል
ቀስ በቀስ የአባላት ቁጥሩን እያሳደገ የሚገኘው ብሪክስ በተለይ ለአፍሪቃዉያኑ ሃገራት ዓለማቀፍ ሚናቸውን እንዲያሳድጉ ብሎም ራሳቸውን እንዲቀይሩ መልካም ዕድል ይዞላቸው እንደመጣ ጥምረቱን በቅርበት የሚከታተሉት ባለሞያዎች ይናገራሉ ።
በካሜሩን ዱአላ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ማይክል ንዲማንቾ እንደሚሉት በርካታ አፍሪቃዉያን ሃገራት ነባሩን ዓለማቀፍ ኃያል የሚገዳደር አዲስ የዓለም ኃያል መንግስት መሻታቸው ብሪክስን እንዲቀላቀሉ ምርጫቸው አድርጓል፤ ይላሉ ።
«ብሪክስ አፍሪካውያን ለተወሰነ ጊዜ ያላዩዋቸውን አዳዲስ ለውጦችን እያመጣ ነው። አስታውስ አፍሪካውያን አሮጌው እያልን ከምንጠራው ሥርዓት ከባርነት፣ በባሪያ ንግድ፣ በቅኝ ግዛት፣ በኢምፔሪያሊዝምና በመሳሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈዋል። ነገር ግን አሁን አፍሪካውያን፣ ብሪክስ ነባራዊውን ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ለመቋቋም ይረዳል ብለው ያስባሉ።»
እንደዚያም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ አፍሪቃዉያን ለራሳቸው ከሚሰጡት ግምት እና አመለካከት የተነሳ ገና በርካታ የቤት ስራ እንደሚጠብቃቸው የሚገልጹት ምሁሩ አፍሪቃዉያኑ በ,ተለዋዋጩ ዓለም የሚመጥናቸውን እና የሚጠቅማቸውን ስፍራ ለማግኘት በሚደርጉት ጥረት ልክ የቆየ የቤት ስራቸውን በፍጥነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ባይ ናቸው ።
«አፍሪካ እራሷን መመገብ አለባት፤ እና በአፍሪካ ውስጥ የንግድ ስራ መስራት ደግሞ በጣም በጣም ከባድ ነገር እንደሆነ ይገነዘባሉ። ሰዎች አፍሪካ ውስጥ ከመግዛት ከአውሮጳ እና አሜሪካ መግዛት ርካሽ እንደሆነ ነው የሚያስቡት ይህ ደግሞ መሆን የለበትም ። »
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን የጠየቀችዉ ጎራ ለማማረጥ አይደለም-ዉጉሚ
ሌላው የኮንጎ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ኤ ኤል ኪቴንጌ ሉባንዳ እንደሚሉት አፍሪቃዉያኑ ብሪክስን መቀላቀላቸው እንዳለ ሆኖ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት መበላሸት የለበትም ።
« BRICS ውስጥ ብንሆንም ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለን ጂኦፖለቲካዊ ግንኙነት ያለ ምንም ችግር መቀጠል ነው ያለበት ። እና ይህ ደግሞ ዛሬ ነው መሆን ያለበት። ከተወሰኑ አካላት ጋር የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የተወሰነ ነፃነት እንዲኖረንም ያስችለናል ፤ እናም ይህ ነፃነት ለሁሉም ሰው መከበር ያለበት ይመስለኛል።»
ምሁራኑ በተናጥል ለዶቼ ቬለ በሰጧቸው አስተያየቶች ብሪክስ ለአፍሪቃ ምናልባትም አዲስ ተስፋ ይዞ እንደመጣ ነው። ሩሲያ እና ቻይና በሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶች ላይ ያቀረቡት ማራኪ ቅናሾች ደግሞ ምናልባትም ም አዲስ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ለመፍጠር አፍሪቃ ራሷን እንድትቀይር አሳማኝ ጉዳይ ይዞ መምጣቱን መመልከታቸውን ይገልጻሉ።
ያለፉት አስርት አመታት በአፍሪካ ትልቁ የንግድ አጋሮች እና አዳዲስ ባለሀብቶች በሆኑት በአፍሪካ እና በ BRICS መንግስታት መካከል የንግድ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶች መጨመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጆሐንስበርግ-የብሪክስ ጉባኤተኞች አዳዲስ አባላት ይቀበሉ ይሆናል
እንደዚህም ሆኖ ግን ብሪክስን የሚቀላቀሉ የአፍሪቃ ሃገራት ተግዳሮት ሊገጥማቸው እንደሚችል ዶ/ር ማይክል ንዲማንቾ ስጋታቸውን ይገልጻሉ ለዚህኛው ሃሳባቸው መነሻ የሆነላቸው ደግሞ አፍሪቃዉያኑ በሚያገኟቸው ዕድሎች በአህጉሪቱ ውስጥ ምርት እና ምርታማነትን ሊገድሉ የሚችሉ ስምምነቶችን ጨምሮ ሌሎች አደጋዎችን በራሳቸው ላይ ሊጋብዙ የሚችሉበት ዕድል አለ ባይ ናቸው ።
«ስለገቢ ሸቀጦች ካነሳን ቻይና ለምትልካቸው ምርቶች አነስተኛ ቀረጥ የምትከፍልበት ሁኔታ ይፈጥራል ። ይህ ደግሞ ምርቶቿን ወደ አጠ,ቃላይ የአፍሪቃ ሃገራት መላክ የምትችልበት እና ከሞላ ጎደል ቀረጥ ነጻ የምታስገባበትን ዕድል ይፈጥርላታል ። ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የሚገድል ይሆናል »
የብሪክስ የሦስት ቀናት ጉባኤ ዛሬ ጆሃንስበርግ ላይ ጀመረ
በሌላ በኩል የብሪክስ መስፋፋት በዚህ ከቀጠለ አፍሪቃ ተግባራዊ ያደረገቻቸውን ቀጣናዊ ነጻ የንግድ ትስስሮች ሌላ ተግዳሮት እንዳይሆንም ያሰጋል ።
የማህበረ ኤኮኖሚ ተንታኞቹ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ሃሳባቸውን ሲቋጩ አፍሪቃ ያገኘቻቸውን ዕድሎች ማምከን የለባትም ። ቀጣናዊ ፣ አህጉራዊ ብሎም ዓለማቀፋዊ የንግድ ትስስሮች እና ጥምረቶች አንዱ ሌላኛውን ሳያፋልስ መጠቀም የሚችሉበትም ዕድል መታየት አለበት ። ሀገራቱ ብሪክስን ሲቀላቀሉ ከምዕራቡን ዓለም ጋር ያላቸውን ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ትብብር በማበላሸት መሆን አይገባዉም ባይም ናቸው ።
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ