1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሪክስ ጉባኤ፦ በአፍሪቃ እንዴት ይታያል?

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 2015

​​​​​​​አድማሱን ለማስፋት ያለመው ብሪክስ ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ውስጥ ይሰበሰባል ። ሆኖም ሩስያ በአኅጉሪቱ ላይ ካላት ተጽእኖ አንጻር የፕሬዚደንቷ ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ላይ በአካል አለመገኘት አፍሪቃ ውስጥ ያላት ተጽእኖ ላይ ምን ይፈጥር ይሆን?

ብሪክስ፦ የሩስያው ፕሬዚደንት ጉዳይ አወዛግቧል

This browser does not support the audio element.

ምስል Mikhail Tereshchenko/TASS/dpa/picture alliance

አድማሱን ለማስፋት ያለመው ብሪክስ ቡድን በሚቀጥለው ሳምንት ደቡብ አፍሪቃ ጆሐንስበርግ ውስጥ ይሰበሰባል ። ሆኖም ሩስያ በአኅጉሪቱ ላይ ካላት ተጽእኖ አንጻር የፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ላይ በአካል አለመገኘት አፍሪቃ ውስጥ ያላት ተጽእኖ ላይ ምን ይፈጥር ይሆን?

ሩስያ እና ቻይናን ጨምሮ አምስት ሃገራት ያቋቋሙት የብሪክስ (BRICS) ቀጣዩ ጉባኤ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ይቀሩታል ። ጉባኤው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚቀጥለው ሳምንት ከነሐሴ 16 እስከ 18 ድረስ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ዐስታውቀዋል ።

የብሪክስ ጉባኤና የሩስያ ፕሬዚደንት ማወዛገብ

የጉባኤው ዋነኛ ዓላማም፦ በዓለም ዙሪያ ፍትሐዊ አስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ብሎም በምዕራባውያን በኩል ያለውን የኤኮኖሚ የበላይነት መቀልበስ መሆኑ ይነገራል ።  

ቻይና ሻንጋይ የሚገኘው የብሪክስ (BRICS) ዋና መቀመጫ ። ምሥራቅ ሻንጋይ ውስጥ የሚታየው ይህ ሕንጻ የብሪክስ ባንክ ይሰኛል ። አዲሱ የልማት ባንክም በሚል የሚጠሩት አሉ ።ምስል Fang Zhe/Xinhua/IMAGO

ሆኖም የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ላይ በአካል አይገኙም መባሉ አፍሪቃ ውስጥ ባላቸው ተጽእኖ ላይ ጥላውን ማጥላቱ አይቀርም ሲሉ ተንታኞች ይገልጻሉ ።

የእንግሊዝኛው ብሪክስ ምሕጻር ከአምስቱ የቡድኑ አባል ሃገራት፦ ማለትም ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ ስያሜ የመጀመሪያዎቹን ፊደላት በማዳቀል የተፈጠረ ነው።  የቡድኑ አባላት በዓለማችን ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ግስጋሴ ላይ ባሉ ሃገራት የተመሠረተም ነው ።  

የሩስያ ፕሬዚደንት ከዩክሬን ወረራ ጋር በተገናኘ በአሁኑ ወቅት የእስር ማዘኛ በቆረጠባቸው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት(ICC) ዒላማ ውስጥ ናቸው ።  

በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ የሩስያ ልዑካን በውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው ሠርጌ ላብሮቭ በስተመጨረሻ ይመራሉ መባሉ አረገበው እንጂ፤ ጉዳዩ ደቡብ አፍሪቃን የዲፕሎማሲ እና ሕጋዊ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷት ሰንብቶ ነበር ። ፕሬዚደንት ፑቲን በጆሐንስበርግ ጉባኤ ላይ እንደማይገኙ ከሳምንታት በፊት ሲገልጡ ጉዳዩን ለማቃለል ሞክረዋል ።

የሩስያ ፕሬዚደንት ከዩክሬን ወረራ ጋር በተገናኘ በአሁኑ ወቅት የእስር ማዘኛ በቆረጠባቸው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት(ICC) ዒላማ ውስጥ ናቸው ምስል Alexander Kazakov/AP Photo/picture alliance

«ከባልደረቦቼ ጋር እንገናኛለን ። ከቻይና ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ሊቀመንበር፤ ከሕንድ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር፤ ከደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝተናል ። በቅርቡ ሰዎች ከብራዚል መጥተው ነበር ። ከፕሬዚደንት ሉላ ጋር ግንኙነት አለን ። ከእሳቸው ጋር በጣም ጥሩ ግኙነት ነው ያለኝ ። የእኔ በብሪክስ ጉባኤ ላይ መገኘት እዚህ ሩስያ ውስጥ ከመሆኔ ይበልጥ ጠቃሚ ነው ብዬ አላስብም ።»

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በደቡብ አፍሪቃ ግብዣ ሲደረግላቸው እና እሳቸውም በጉባኤው እንደሚሳተፉ ሲገልጹ ደቡብ አፍሪቃን በተለይ ከምእራባውያን ጋር አጣብቂን ውስጥ ከትቷት ነበር ።

ለመሆኑ የፕሬዚደንት ፑቲን መቅረት አንዳች ትርጉም ይኖረው ይሆን?

ፕሬዚደንት ፑቲን በጉባኤው ላይ አለመገኘታቸው ብርቱ ውዝግብን ማስቀረቱን ስብሰባው ይካሄድበታል በተባለው ከተማ ጆሐንስበርግ ውስጥ በዊትዋተርስታንድ ዩኒቨርሲቲ አጥኚ ጌዲዮን ቺታንጋ ይናገራሉ ።

«የፕሬዚደንት ፑቲን በስብሰባው አለመታደም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት እሳቸው ላይ የእስር ማዘዣ ከማውጣቱ ፤ ብሎም የምዕራቡ ዓለም በደቡብ አፍሪቃ ፖሊሲ እና ሩስያ ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ጭምር ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ስጋቱን ከመግለጹ አንጻር በጉባኤው አለመታደማቸው ለቡድኑ የሚበጅ ይመስለኛል ። በእሳቸው መገኘት እና ይታሰራሉ ወይንስ አይታሰሩም ጉዳይ መገናኛ አውታሩ መጠመዱ በራሱ የብሪክስ ጉባኤን መንፈስ የሚያደፈርስ ነበር ። ስለዚህ በስብሰባው አለመገኘታቸው ቢያንስ በአሁኑ ወቅት ትኩረቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንዲሆን ይረዳል ።»

የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን (በስተቀኝ) - እዚህ ፎቶ ላይ ከደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፖሳ (በስተግራ) ጋር ቆመው። የሩስያው ፕሬዚደንት በብሪክስ ጉባኤ በአካል አይገኙም ።ምስል Mikhail Metzel/ITAR-TASS/IMAGO

ደቡብ አፍሪቃዓለም አቀፍ ግንኙነት ተቋም የመንግሥታዊ አስተዳደር እና ዲፕሎማሲ ዋና ተመራማሪ ጉስታቮ ዴ ካርቫሎ ግን ሩስያ በአሁኑ ወቅት የኤኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ነው የምትገኘው ብለዋል ። ያም በመሆኑ ብላድሚር ፑቲን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ተጉዘው በስብሰባው ቢታደሙ ጥልቅ ለሆነ ድርድር ይጠቅማቸው ነበር፤ ያን አጥተዋል ብለዋል ።

«ሩስያ በአሁኑ ወቅት በኤኮኖሚ ተዳክማለች ። ለዚህ ትልቁን ድርሻ የሚወስደውም ጦርነቱ ነው። ስለዚህ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ቢታደሙ ኖሮ ምናልባት በከፍቴተኛ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶችን ሊያስፈችሙ ይችሉ ነበር ። ባይታደሙ ግን ስምምነቶቹ ሊፈጸሙም ላይፈጸሙም ይችላሉ ። በዚህም አለ በዚያ ግን ታላቅ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል ብዬ አላምንም ። »

በእሳቸው አባባል ሁሉም ይስማማል ማለት ግን አይደለም ። የብሪክስ ጉባኤ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪቃ እጅግ ግራ ዘመም የተቃውሞ ፖለቲካ አራማጁ የኤኮኖሚያዊ ነጻነት ታጋዮች ፓርቲ (EFF) መስራችና መሪ ጁሊየስ ማሌማ ለፕሬዚደንት ፑቲን የድጋፍ ሰልፍ አስተባብረዋል ። በሰልፉ ላይም ለሌሎቹ የብሪክስ አባላት ጥሪ አስተላልፈዋል ።

«የቻይና ሪፐብሊክ፤ የሕንድ እና የብራዚል ፕሬዚደንቶች ለፕሬዚደንት ፑቲን አጋርነታቸውን በማሳየት ወደ ብሪክስ ጉባኤ ለመታደም እንዳይመጡ ስንል ጥሪያችን እናስተላልፋለን ። `አንዳችን ስትነኩ ሁላችንንም እንደነችሁ ነው የሚቆጠረው` ሊሉም ይገባል ። »

በደቡብ አፍሪቃ እጅግ ግራ ዘመም የተቃውሞ ፖለቲካ አራማጁ የኤኮኖሚያዊ ነጻነት ታጋዮች ፓርቲ (EFF) መስራችና መሪ ጁሊየስ ማሌማ ለፕሬዚደንት ፑቲን የድጋፍ ሰልፍ አስተባብረዋል ። በሰልፉ ላይም ለሌሎቹ የብሪክስ አባላት «ለፕሬዚደንት ፑቲን አጋርነታቸውን በማሳየት ወደ ብሪክስ ጉባኤ ለመታደም እንዳይመጡ» ጥሪ አስተላልፈዋል ።ምስል Guillem Sartorio/AFP

የሩስያ በሣኅል ቀጣና ያላት ሚና

የሩስያው ፕሬዚደንትጉዳይ በደቡብ አፍሪቃ ብቻ አይደለም ትኩረት የሳበው ። በቅርቡ ኒጀር ውስጥ የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትም ሩስያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተከታታይ ሥዒረ መንግሥታት በተፈጸሙበት የሳኅል ቀጣና ውስጥ ተጽእኖዋ እየጎለበቱ መሄዱን አመላካች ሆኗል ።  

በቀጣናው ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ አምና እና ካቻምናም በተከታታይ መፈንቅለ መንግስት ተከናውኖባቸው ነበር ። ወታደራዊ ኹንታዎቹም በሃገራቱ የቀድሞ ቅኝ ገዢ የነበረችው ፈረንሣይ ወታደሮችን አባርረዋል ። በአንጻሩ ከሩስያ ጋር ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል ። ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር በመሆን ማናቸውንም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደማይታገሱ አስጠንቅቀዋል ። «ሰላማዊ መፍትኄ» እንዲኖር በሚል በጋር ጥሪያቸውን አስተጋብተዋል ።

በቅርቡ በወታደራዊ ኹንታ ከሥልጣናቸው የተሰናበቱት ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዞም መሪ በነበሩበት ወቅት ኒዠር የምዕራባውያን አጋር ተደርጋ ነበር የምትቆጠረው ። ተንታኞች ሩስያ አሁን አፍሪቃ ውስጥ የምታደርገውን ምዕራባውያንም ቀደም ሲል ያደርጉት ነበር በማለት ልእለ ኃያላኑ አፍሪቃ ውስጥ በእጅ አዙር ሽኩቻቸው መቀጠሉን ጠቁመዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW