ብሪታኒያ ቤልጅየም ዉስጥ የጸረ ድሮን መሳሪዎችና ባለሙያዎች አሠፈረች
ማክሰኞ፣ ኅዳር 2 2018
ባለፈው ሳምንት በቤልጅየም ያውሮፕላን ማረፊያዎችና የጦር ሰፈር ጭምር ድሮኖች በብዛት መታየታቸውንና በረራዎችን ማስተጓጎላቸውን ተክትሎ ብርታኒያ የጸረ ድሮን የያር ሀይል ባለሙያዎችንና መሳሪያዎችን ወደ ስፍራው የላከችና ያሰፈረች መሆኑ ተገልጿል።፡የብርታኒያ የጦር ሀይሎች አዣዥ ሰር ሪቻርድ ናይቶን ባለፈው ዕሁድ `ቤልጀየምን ለመርዳት ባለሙያዎችንና ጸረ ድሮን መሳሪያዎችን እንልካለን” በማለት ስጋቱ ከየትም ይምጣ ከየት፤ አገራቸው የኔቶ አባል ከሆነ አገር ጋር የሚቆም መሆኑን አረጋግጠዋል።
የጸረ ድሮን ወታደራዊ ድጋፍ ያስፍለገበት ምክንያት
ወታደራዊው እርዳታ የተሰጠው ባለፈው ሀሙስ ምንጫቸው ከየት እንደሆነ ያልታወቁ ድሮኖች የቤልጅየምን ያየር ትራስንስፖርት ካወኩና በጦር ሰፈሮች ላይም ማንዣበባችው ከተረጋገጠ በኋላ፤ የቤልጅየም መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መሆኑ ታውቋል።
ቀደም ብሎ ጀርመንም እንደዚሁ ወታደራዊ ባለሙያዎችን መሳሪያዎችን ወደ ቤልጅየም የላከች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ፈረንሳይም በተመሳሳይ ባለሙያዎችን በመላክ ለቤልጀይም ድጋፏን ያሳየች መሆኑ ተገልጿል።
ድሮኖችን ወደ ቤልጅየም የላከው አገር ማንነትና ጥርጣሬዉ
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ እንደ ሲዊድንና ፊንላንድ የመሳሰሉ የሰሜን አውሮፓና ኖርዲክ የኔቶ አባል አገሮች ያየር ክልል ላይ ድሮኖች ሲታዩ የነበር ሲሆን፤ ባለፈው ሀሙስ በበልጅየም ያየር ክልል የታዩት ድሮንቾ ግን ያገሪቱን ያውሮፕላን ጣቢያዎች ለተወሰነ ግዜም ቢሆን ያዘጉና ስጋትም የፈጠሩ ነበሩ። ድሮኖቹ ከየት እንደመጡ በትክክል አይታወቅም ቢባልም፤ ብዙዎች በዩክሬን ጦርነት ምክኒያት ከኔቶና ያውሮፓ ህብረት አባል አገሮች ጋር ፍጥጫ ላይ ያለችውን ሩሲያን ዋና ተጠያቂ ያደርጋሉ።።፡በተለይ በቤልጅየም ባንኮች ያለውንና በህብረቱ እንዳይንቀሳቀስ የተደረገውን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠረውን የሩሲያ ገንዘብ ለዩክሬን ለማስተላለፍ መታቀዱ አውሮፓን በተለይም ቤልጅየምን የድሮን ጥቃት ማስፈራርያ እንዲደርሳት ሳያደርግ እንዳልቀረ በብዛት ይነገራል።። የጀርመኑ የመከላከያ ሚኒስተር ቦሪይስ ፕሪስቶሪስም፤ እሳቸውም ቦልጅሞችም እርምጃውን ከዚህ ጋር የተያይዘ ነው ብለው እንደሚያምኑ ነው ሲናገሩ የተሰሙት፤ “ ሁላችንም በዚያ መልክ ነው የምንረዳው። በቤልጀየም ያለመረጋጋትና ፍርሀት ለመፍጠር ታስቦ በሩስያኖች የተደረገና ንብረታችንን ከነካችሁ ወዮላችሁ የሚል ማስፈራሪያ ለመላክ ነው” በማለት ሁኔታውን ከዚህ ውጭ መረዳት እንደማይቻል አስታውቀዋል።
የሩሲያ ማስተባባያና የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጥሪ
ሩሲያ፤ በአውሮፓ ባንኮች የሚገኘውን ንብረቷን ለዩክሬን ለማስተላለፍ የሚደረገው ጥረት ህገወጥና ተራ ዘረፋ ነው በማለት ያስጠነቀቀች ቢሆም በበልጀይምም ሆነ በሌሎች አገሮች ላይ ግን ምንም አይነት ድሮን እንዳላሰማራች ነው ስትገልጽ የምትሰማው። የስሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ ግን ሩሲያ ለአውሮፓም ለአለምም የደህንነት ስጋት ምንጭ መሆኗን ነው ደጋግመው የሚገልጹት፤ “ያጋጠመን ስጋት ተጨባጭ ነው። ሩሲያ ላውሮፓና ለአለም ሰላም ጭምር ስጋት ነች። ከቻይና ከኢራንና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ነው እየሰራች ያለችው። የዋሆች መሆን የለብንም መዘጋጀት አለብን” በማለት በተለይ ለኔቶ አባል አገራት ግልጽ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ገበያው ንጉሴ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ