ብዙዎችን ለስቃይ የዳርገው ምንነቱ ያልታወቀው የሰውነት መዛል
ማክሰኞ፣ ግንቦት 26 2017
መላ ሰውነትን ከመጠን በላይ ያዝላል። በዚህ ለጤና ችግር የተጋለጡ ወገኖች ሰውነታቸው እጅግ ይዝላል፤ ኃይለኛ የድካም ስሜት ይኖረዋል። እንዲህ ያለውን የመላ አካል ዝለት ስለሚያስከትለው የጤና ችግር ምንነት ከተደረሰበትና የህክምናው ዘርፍ ተመራማሪዎችም ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ብለው ከጠሩት ከ50 በላይ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህ የጤና ችግር የተጋለጡ ወገኖች ሁልጊዜም ከባድ ድካምና የሰውነት ዝለት ይሰማቸዋል። ሊያስወግዱት ግን አይችሉም። አንዴ ከተቀሰቀሰ ቢያንስ ለስድስት ወራት ጤናቸው አይመለስም። መድኃኒት አልተገኘለትም። የጤና ችግሩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት በቂ ምርምርም አልተካሄደበትም።
የዶቼ ቬለዋ አና ካርታውስ ካነጋገረቻቸው በዚህ የጤና ችግር ከሚሰቃዩ ወገኖች አንዷ ላሪሳ ናት። (የታማሚዋ ስም የግል መረጃዋን ለመጠበቅ ሲባል ተቀይሯል።) ህመሙ ሲነሳባት ምንም ለማድረግ አቅም ታጣለች። ሌላው ቀርቶ ከጓደኞቿ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ሲኖራት ከቤትዋ ለመውጣት ጊዜ ይፈጅባታል። ከቀጠሮ ሰዓቷ ቢያንስ ከ20 ደቂቃ በፊት የስልኳን ማንቂያ መሙላት ይኖርባታል። ድክም ይላታል፣ የመሞት ኃይል ይሰማኛል ትላለች።
ለዚህ የጤና ችግር የተጋለጡ ወገኖች በቋሚነት ኃይለኛ ድካም ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት የተለመደው ዓይነት የኑሮ ሂደት ለመምራት የሚችሉ አይመስላቸውም። በዚህ የጤና ችግር ውስጥ ካሉ ወገኖች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መሥራት አይችሉም። ላሪሳ አብዛኛውን ጊዜዋን በጭለማ ክፍል ውስጥ ጋደም ብላ ታሳልፋለች። ጆሮዋ የአካባቢውን ድምፅ እንዳይሰሙ ደፍና፤ ዓይኖቿን በጭንብል ሸፍና ትተኛለች። እሷ እንደምትለው ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ በኋላ የ30 ወይም የ40 ደቂቃ እረፍት ማድረግ ይኖርባታል።
ከመኝታዋ ስትነሳ ማረፍ አለባት፤ ወደመጸዳጃ ቤት ስትሄድም እረፍት ያስፈልጋታል። ጥርሷን ቦርሻ ስትጨርስም ማረፍ አለባት፤ ምግብ በልታም እንዲሁ ማረፍ ግድ ነው። ገላዋን ከታጠበች ደግሞ ለአምስት ቀናት ድቅቅ ብላ ትደክማለች።
ME/CFS ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ምንድነው?
ማይልጂክ ኢንሴፈሎሚየላይትስ ወይም ወይም ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል፤ ME/CFS የነርቭ-ኢሚውኖሎጂካል በሽታ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የጤና ችግር ብዙ ጊዜ ወደ ከባድ የአካል ጉዳት ይመራል። ለዚህ የጤና ችግር የተጋለጡ ብዙ ሰዎች ከባድ ህመም፤ የጡንቻ መኮማተር እና የልብና የደም ስር ችግር፤ የጉንፋን ምልክቶች ያጋጥማቸዋል፤ የመተኛትም ችግር አለባቸው።
ላሪሳ መቀመጥም ሆነ ቀጥ ብሎ መቆም ለእሷ እና እሷን ለመሰሉ ታማሚዎች ከባድ መሆኑን ትናገራለች። ጭጋጋማነት ያፈነው አንጎሏ ሃሳቦችን በወጉ አደራጅቶ መያዝ ተስኖታል።
«ሀሳቦች ከጭንቅላቴ ይጠፋሉ፤ አንዳንዶቻችን ሳንሞት ሕይወታችንን ያጣን ያህል ይሰማናል፣ ለመሆኑ የምለው ለሚሰማው ይገባው ይሆን?» በማለትም ትጠይቃለች።
በህክምናው ዘርፍ ከታወቀ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም እስካሁን ሰውነት ምን ሲሆን ሊከሰት እንደሚችል ግልጽ አይደለም። በበርሊን የሻሪቴ ፋቲግ ማዕከል የበላይ የሆኑት ካርመን ሻይበንቦገን፤
«ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ሲያጋጥም የአካል ውስጥ የደም ፍሰት ሊስተካከል አይችልም። ወደ አንጎል እና ጡንቻዎች የሚሄደው የደም ፍሰት ይደናቀፋል። ሰውነት በአግባቡ የሚሠራው በቂ ኦክስጂን በደም ስሮች አማካኝነት ወደዚያ ውስጥ መግባት ችሎ ኃይል ማመንጨት ሲችል ነው።» ነው የሚሉት።
መንስኤው
ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ብዙዉን ጊዜ የሚጀምረው ከተላላፊ በሽታ በኋላ ነው፤ እጢን የሚያናጋ ትኩሳት ወይም ኢንፍሉዌንዛ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። ለምሳሌ ላሪሳ በኮቪድ 19 ተይዛ ነበር።
እሷ እንደምትለው ከሳምንታት በኋላ በውኃ ውስጥ የምትራመድ ይመስል ስትሄድ ይደክማታል፤ አየሩም ድንገት ከበዳት። መቆም ፈተና ሆነባት፤ ቴሌቪዥን መመልከት የአድካሚ ሥራ ያህል ያዝላት ጀመር። ከዚያም የጡንቻ ህመም ተከተለ፤ የመገጣጠሚያ እና የነርቭ ህመም እንዲሁም የራስ ምታት መጣ። እንቅልፏ ይረበሽ፤ ጆሮዋም የማያቋርጥ ድምጽ ያሰማታል፤ ማቅለሽለሽና መራመድ ችግር ጠናባት።
ከዶክተር ዶክተር እያማረጠች ችግሯን እየገለጸች ተመረመረች። አዎንታዊ ነገር እንድታስብ፣ አትክልት እንድትበላ እና ዮጋ እንድትሠራ መከሯት። ኃይለና የአካል ድካሟን በፊዚዮቴራፒ ለማዳን ሲሞክሩ፤ አኩፓንቸር ሲያደርጉላት፤ የጉልበት ህመሟን ለማስታገስ የተለያዩ ዘዴዎች ሲጠቀሙ ጭራሽ ሰውነቷ ሙሉ ለሙሉ አቅም አነሰውና በተሽከርካሪ ወንበር ተቀምጣ ለመንቀሳቀስ ተገደደች።
«የማደርገውን ሁሉ የማደርገው በትግል ነው። ሁልጊዜም ታዲያ ይህን ትግል ማሸነፍ አልችልም። ለምሳሌ የግል ንጽሕናየን የመጠበቁ ትግል አንዱ ነው።»
እንግዲህ ከጽዳቷና አካሏን ከሚያዝለው ህመም መምረጥ ይኖርታል። ለዚህ ህመም ተጠቂዎች መጠነኛ የጭንቀት ስሜት ያለባቸውን ችግር ሊያባብስ ይችላል። የሚሰማቸው የሰውነት የመዛል ሁኔታ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ ሕይወታቸው የትግል ነው። በእርግጥ የላሪሳ መጠኑ ከፍ ይላል። ከእሷ በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ሥራ ውለው የሚገቡ እና የራሳቸውን ኑሮ መምራት የሚችሉ ናቸው። በአንጻሩ ከእሷም በባሰ ደረጃ የሚገኙ ሌላው ቀርቶ እጃቸውን እንኳ ከፍ አድርጎ ለማንሳት ስቃይ የሚሆንባቸውም አሉ።
የሻይበንቦርገን የምርምር ቡድን ምናልባት ለልብ ድካም የሚሰጠው መድኃኒት ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ተጠቂዎች ይረዳ እንደሆነ እየተመራመረ ነው። መድኃኒቱ ምናልባት የደም ቧንቧዎች በአግባቡ እንዲሠሩ ሊረዳ ይችላል የሚል ተስፋ አለ።
ከድካምና የአካል ዝለት ጎንለጎን ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ተጠቂዎች መጠነኛ ብግነት ያጋጥማቸዋል። ምክንያቱም በሽታ የመቋቋም አቅማቸው በአንድ ተላላፊ በሽታ ተይዘው በሚያገግሙበት ሂደት ንቁ ሆኖ ይቆያል። ተላላፊ ህመሙን ለመዋጋት የተነቃቃው የበሽታ የመከላከል አቅም በዚሁ አቅሙ ሰውነት ውስጥ ስለሚቆይ እራሱን መልሶ ማጥቃት ይጀምራል እና ነው። ይህ ደግሞ በብዛት የሚከሰተው የልብ ምት እና የደም ግፊትን በሚቆጣጠረው የነርቭ ሥርዓት ውስጥ ነው።
ምን ሊደረግ ይቻል ይሆን?
እስካሁን ይህ በርካታ ሚሊየኖችን ለሚያሰቃየው የጤና ችግር መድኃኒት አልተገኘም። አብዛናውን ጊዜ ታማሚው እና ዶክተሩ የህመሙን ምልክቶች ተከትለው በጋራ አማራጮችን ለመፈለግ ይሞክራሉ። የተደረሰበት አንዱና ዋነኛው መፍትሄ ታማሚዎች እራሳቸው በየግል አቅማቸውን እንዲያውቁና ከልካቸው ባለፈ ሰውነታቸውን ለማዘዝ እንዳይሞክሩ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ለላሪሳ ይህ ማለት አብዛኛውን ጊዜ ጋደም ማለት ነው።
ብዙ የሚቀረው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ
ቀደም ሲል እንደተገለጸው ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ከጎርጎሪዮሳዊው 1969 ጀምሮ በይፋ የታወቀ ህመም ነው። በመላው ዓለም 17 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በዚህ የሚሰቃዩ ሲሆን፤ በጾታ ሲታይ ከወንዶች ይልቅ አብዛኞቹ ታማሚዎች ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ለረጅም ዓመታት ችግሩ የስነልቡና ወይም የአእምሮ ህመም ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ዛሬም እንደዚያ የሚመለከቱት አሉ። በበርሊን የሻሪቴ ፋቲግ ማዕከል ኃላፊ ካርመን ሻይበንቦገን፤ «እስካሁን ማንም ያልተረዳው ከባድ ህመም» ይሉታል።
ላሪሳ በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ እንዳለች ነበር የህክምና ምርመራ ውጤት ያመለከተው። በዩኒቨርሲቲም ደረጃ ስለህመሙ ምንነት የሚያስረዳ ትምህርት አይሰጥም፤ ከተሰጠም የተሳሳተ ነው የሚሆነው ይላሉ ሻይበንቦገን። የሰውነት ድካም ወደ ህመምነት ደረጃ ማደጉ፤ ለጤናው ችግር ተጠቂዎችም መልስ የሌለው እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው።
ከሳምንታት በፊት እዚህ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ የዚህ ህመም ተጠቂዎች አደባባይ በመውጣት ምርምር እንዲደረግበትና መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥሪ አቅርበዋል። በመላው ዓለም ደረጃም በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊው ግንቦት 12 ቀን ስለክሮኒክ ፋቲግ ሲንድሮም ግንዛቤ እንዲኖር እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ። በርሊን ከተማ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ ያስተባበረችው ላሪሳ ናት። ግን መሳተፍ አልቻለችም። በስፍራው ተገኝታ ለመተኛት እንኳን አቅም አልነበራትም።
ሸዋዬ ለገሠ/አና ካርታውስ