ቦይንግ አፍሪካ ውስጥ ሁለተኛው የሆነውን ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ውስጥ ከፈተ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16 2017
ግዙፉ የአሜሪካ የኤሮስፔስ ኩባንያ ቦይንግ በአፍሪካ ሁለተኛ ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ውስጥ ከፍቷል። ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ቁልፍ አጋርነት ያለው ይህ ኩባንያ አዲስ የከፈተው የአስተዳደር ማዕከል «የአየር መንገዱን ደንበኞች እና አጋሮች በመላው አፍሪካ ለማገልገል» አቅሙን እንደሚያሳድግለት ገልጿል።
በጉዳዩ ላይ አስትያየታቸውን ለዴቼ ቬለ ከሰጡ የበረራ ዘርፍ ባለሙያዎች አንደኛው ይህ ውሳኔ «በቦይንግ እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም በቦይንግ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነትም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል» ብለዋል።
ሌላኛው ባለሙያ በበኩላቸው «በአፍሪካ ውስጥ የቦይንግን ገበያ ለማስፋፋት እና ከሽያጭ በኋላ አየር መንገዶች የሚያስፈልጋቸውን ክትትል በቅርበት በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው» ሲሉ መልሰዋል።
ቦይንግደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ ከሚገኘው ቀጥሎ በአፍሪካ ውስጥ ሁለተኛውን ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ውስጥ ከፍቷል። ድርጅቱ ይህ «በቀጣናው እያደገ ላለው የኤሮስፔስ ኢንደስትሪ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክራል።» ብሏል። የአፍሪካን የአቪዬሽን ዘርፍ እድገት ለማበረታታት ፈጠራን እና ትብብርን ለመፍጠር በጋራ እንጠባበቃለን ያለው ቦይንግ፣ ይህ ርምጃው የኩባንያውን ደንበኞች እና አጋሮች በመላው አፍሪካ ለማገልገል አቅሙን እንደሚያሳድግለትም ገልጿል።የበረራ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ዳንኤል ኃይሉ «አፍሪካ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋነኛው የቦይንግ ደንበኛ» መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ ቢሮ እዚህ አዲስ አበባ መከፈቱ አንድም ኩባንያው ገበያውን የሚያስፋፋበት ስልት ነው። በሌላ በኩል ቦይንግ አውሮፕላኖቹን ለደንበኞቹ ከሸጠ በኋላ የሚኖረውን «ድጋፍ በቅርበት ሆኖ በተቀላጠፈ ኹኔታ ለመከታተል ያሳለፈው ውሳኔ ነው» ብለዋል።
«የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ አውሮፕላኖች ከቦይንግ ይወስዳል። ስለዚህ ይህ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ገበያን ለማሳለጥ የተቋቋመ ነው»የኢትዮጵያ ኢሮክለብ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት የአቬሽን ባለሙያ ዮናታን መንክርን እንደሚሉት ደግሞ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የቦይንግ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት በተለይ ከስድስት ዓመታት በፊትቢሾፍቱ አቅራቢያ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ምክንያት ፈተና ውስጥ ገብቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ የአሁኑን እርምጃ ግን ግንኙነቱ የመሻሻሉ ጉልህ ማሳያ አድርገውታል። ባለሙያው አቶ ዮናታን እንዳሉት ኢትዮጵያ ከመጀመርያው የጀት አውሮፕላን ቦይንግ 720 B እስከ ዘመነኞቹ ማክስ ድረስ የቦይንግ ምርቶች ገዢ ስትሆን ለኩባንያውም ግዙፍ ደንበኛነቷን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኢሮክለብ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት የአቬሽን ባለሙያ ዮናታን መንክርን ለቦይንግ 737 አውሮፕላን መሥሪያ የሚያገለግል ግብዓት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግቢ ውስጥ ተመርቶ መላክ መጀሩ የሁለቱ የንግድ ተሻራኪዎች የግንኙነት አድማስ የማደጉ ማሳያ ነው ብለዋል። አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ምርቶች የታወቀ የጥገና ማዕከል ያለው መሆኑ፣ በሰው ኃብት ልማት አብረው ስለሚሠሩ የኩባንያው ቢሮ መከፈት ይበልጥ ለዘርፉ ማደግ አጋዥ ርምጃ ነው ብለዋል። ቦይንግ ከ150 በላይ ሃገራት ላሉ ደንበኞች የንግድ አውሮፕላኖችን፣ የመከላከያ የአውሮፕላን ምርቶችን እና የጠፈር ንድፎችን የሚያቀርብ፣ የሚያመርት እና የሚያገለግል ኩባንያ መሆኑን ይታወቃል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ነጋሽ መሐመድ