1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተመላሽ የወለጋ ተፈናቃዮች ዳግም ወደ አማራ ክልል መመለስ

ዓርብ፣ ሰኔ 21 2016

ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ከነበሩትና ሁለቱ ክልልች በተስማሙት መሰረት ወደ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከተመለሱት ተፈናቃዮች መካከል “የተገባው ቃል ተግባራዊ አልሆነም” በሚል ወደ አማራ ክልል እንደገና የተመለሱ ተፈናቃዮች ተናገሩ።

ፎቶ ማህደር፤ ወደ ጊምቢ የተመለሱ ተፈናቃዮች
ፎቶ ማህደር፤ ወደ ጊምቢ የተመለሱ ተፈናቃዮች ምስል Negassa Desalegn/DW

ተመላሽ የወለጋ ተፈናቃዮች ዳግም ወደ አማራ ክልል መመለስ

This browser does not support the audio element.

ተመላሽ የወለጋ ተፈናቃዮች ዳግም ወደ አማራ ክልል መመለስ

 ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ከነበሩትና ሁለቱ ክልልች በተስማሙት መሰረት ወደ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን  ከተመለሱት ተፈናቃዮች መካከል “የተገባው ቃል ተግባራዊ አልሆነም” በሚል ወደ አማራ ክልል እንደገና የተመለሱ ተፈናቃዮች ተናገሩ፣ የምዕራብ ወለጋ ዞን ቡና ጎኖፋ (አደጋ መከላከል) ጽ/ቤት አንዳንድ ያልተሟሉ ነገሮች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡

በ2014 ዓ ም በአካባቢው በነበረው ግጭትና አለመረጋጋት  ከምዕራብ ወለጋ ዞን ተፈናቅለውበአማራ ክልል የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎችከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በደረሱበት ስምምነት መሰረት የተወሰኑት ከሚያዝያ 2016 ዓ ም ጀምሮ ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል፡፡ ሆኖም ወደ ቦታቸው ከደረሱ በኋላ “ያለው ነገር እንዳልጠበቅነው ነው” በሚል አንዳንዶቹ ወደ አማራ ክልል እንደገና እየተመለሱ እንደሆነ ነው የሚገልፁት፡፡ አንድ ተፈናቃይ በተለይ በስም የጠቀሱትና “የወረዳው አስተባባሪ” ያሉት ግለሰብ “አገር አለን ብላችሁ ስለሄዳችሁ እዚህ ምንም ነገር የላችሁም” እንዳላቸውና የተስተካከለ ነገር ባለመኖሩ፣ ከነቤተሰቦቻቸው ወደ አማራ ክልል መመለሳቸውንም ነግረውናል፡፡

“የአማራ ክልል መንግስት ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር ተስማምተዋል፣ መቋቋሚያም ሰጣችኋል ተመለሱ በቤታችሁና በቤታችሁ ላይ አገር ሰላም ሆኗል ተብለን ተመለስን እዚያ ስንደረስ ግን ተገላባጩን ነው ያገኘነው፣ የወጣሁት ከምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ነበር፣ እንኳን ቤታችን ልንገባ ቀርቶ መጠለያም በቅጡ አላገኘን፣ ... እናንተ አገር አለን ብላችሁ አይደለ ወደ አማራ ክልል ሄዳችሁ የነበረው ተመልሳችሁ ከመጣችሁ ደግሞ አደብ ገዝታችሁ ተቀመጡ ይህ ጎደለ  ሆነ የሚል ማስፈራሪያ የሚሰጥ አስተባባሪ አለ (ስሙን ጠቅሰዋል) ከመሞት መሰንበት ይሻላል ብለን ለቅቀን መጣን ምን እናደርጋለን፣ በፊትም 3 የቤተሰብ አባላት ሞተውብኛል፣ አሁንም ልጄ ሞቷል፣ የልጄን ልጆች ጨምሬ 13 ቤተሰብ ይዤ ሄጄ መልሸ ይዤ ተመልሻለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

ሌላ አስስተያት ሰጪ ተፈናቃይም መሬታቸው በሌሎች መታረሱንና ቀደም ሲል የተጠቀሰው አስተባባሪ አደብ ገዝታችሁ ተቀመጡ እንዳላቸው ነው የሚገልፁት፣ በመሆኑም ወደ አማራ ክልል እንደገና መምጣታቸውን አመልክተዋል፡፡

“ለምን መሬታችን ይታረስብናል ብለን ስናመለክት እንዴያውም ከወረዳ ተወክሎ የሚሰራ (በስም ጠቅሰውታል) ትናንት የሆናችሁትን ረሳችሁ እንዴ መሬታችን ታረሰብን፣ ማንጓችን ተቆረጠ፣ ትናንት ያላችሁትን አትርሱት፣ አርፋችሁ ተቀመጡ ቀድሞ ይዛችሁ የነበረውን መሬት አታገኙም፣ አገር አለን ብላችሁ ሄዳችሁ ነበር አሁንም መሄድ ትችላላችሁ ተባልን፣ እዛ ተቀምጠን መሬታችን ታርሶ እየለማ አየን መቆፈሪያ ዶማም የሚሰጠን የለም መጣን” ሚያዝያ 2016 ዓም ወደ ምዕራብ ወለጋ ተመልሰው የነበሩና አሁን ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው ወደ አማራ ክልል እንደገና የተመለሱ ሌላ ተፈናቃይም አስተያየታቸውን ተይቀናቸው ነበር፡፡

ፎቶ ማህደር፤ ወደ ጊምቢ የተመለሱ ተፈናቃዮች ምስል Negassa Desalegn/DW

እርሳቸውም መንግስት ቃል የገባልን ነገርተግባራዊ ባለመሆኑ፣ የእርሻቦታና ግብዓት መቅረብ ባለመቻሉ ወደ አማራ ክልል ተመልሻለሁ ነው ያሉት፡፡ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ወለጋ ቡና ጎኖፋ (አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና) ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነፃነት ዓለማየሁ ስለሁኔታው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የግብርና ግብዓት ማቅረብ የጽ/ቤታቸው ኃላፊነት ባይሆንም የክልሉ ግብርና ቢሮ ግብዓት እንዲያቀርብ እንደተገለፀለት አመልክተው ግን እስካሁን ተግባራዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ “ግብርና ግብዓቶችን እንዲያቀርብ ለግብርና ተገልጧል፣ እናቀርባለን ብሎ ነበር እስካሁን አልቀረበም፣ እኛ በራሳችን መንግስታዊ ከልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እየጠየቅን እንዲረዱ እያደረግን ነው፣ ሁሉም ነገር ተሟልቷል ማለት ግን አይቻልም፡፡” ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮች እንደገና ወደ አማራ ክልል እየተመለሱ ነው ስለተባለው መረጃ እንዳላቸው ጠይቀናቸው ነበር፣ “አንዳንዶቹ እየተመለሱ ነው የሚባል ነገር እንሰማለን፣ የተወሰኑ ሰዎች ስምም ደርሶኛል” የሚል ምላሽ ሰጠተዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በስም ጠቅሰው አቤቱታ ያቀረቡበትን ግለሰብ ስሙን እንደሚያውቁት ኃላፊዋ አመልክተው አድርሷል ስለተባለው ጉዳይም እንደሚያጣሩ ነው ያስረዱት፡፡

የተፈናቃዮችን አቤቱታ በተመለከተ ለአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ለገሰ ደውለን መረጃ እንደሌላቸው ጠቁመው፣ ስለጉዳዩ የክልሉን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባባሪያ ኮሚሽነር እንድጠይቅ መክረዋል፡፡ ለአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባባሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብልና ለኦሮሚያ ክልል ቡና ጎኖፋ (አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና) ኃላፊ አቶ ሞገስ እዳኤ ብንደውልም የሁለቱም ስልካቸው አይነሳም፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW