ተስፋ የተጣለባቸው የኮሮና ማከሚያ እንክብሎች
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20 2014ሊገባደድ ከሦስት ቀናት ያነሰ ጊዜ ብቻ የቀረው ጎርጎርዮሳዊው 2021 ዓ.ም ዓለም ባህሪውን እየቀያየረ ብርቱ የጤና ጠንቅ እያስከተለባት ከሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መላቀቅ አልተቻላትም። ተሐዋሲውን ለመከላከል የተዘጋጁ ክትባቶችም ፈተና ገጥሟቸዋል። ሃገራት በወረርሽኙ ምክንያት ከገጠማቸው ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ጥረትም በሌላ የወረርሽኝ ማዕበል በመናጣቸው ከአንዱ ፈተና ወደ ሌላ ብርቱ ፈተና መሸጋገር ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል። እርግጥ ነው በዚህ መሃልም ቢሆን ኮቪድ 19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ካስከተለው ብርቱ ማዕበል ውስጥ መውጫ መንገድ የሚመስሉ ተስፋ ሰጭ የምርምር ሥራዎች እና ግኝቶች መታየታቸው አልቀረም። ስለ ውጤታማነታቸው አፍ ሞልቶ ለመናገር ግን ጊዜው ገና ይመስላል። ጤና ይስጥልን አድማጮች የዕለቱ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መሰናዷችን በመጠናቀቅ ላይ ባለው ጎርጎርዮሳዊ ዓመት 2021 የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የተደረጉጉ ጥረቶችን በተለይም በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር ዕውቅና በተሰጠው እና የፋይዘር እና ሜርክ ኩባንያዎች ምርት በሆኑት የኮሮና በሽታ ማከሚያ እንክብሎች አገልግሎት እና የተጣለባቸውን ተስፋ እንመለከታለን አብራችሁን ቆዩ።
በጎርጎርዮሳዊው 2019 መገባደጃ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ማለት ነው ከቻይናዋ ሁዋን ከተማ በመነሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን ያዳረሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባለፉት 24 ወራት ባሕሪውን እየቀያየረ አሁን ላይ ደርሷል። ተሐዋሲው በዓለም የጤና ድርጅት ተመዝግቦ የሚታወቅ 5,4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሲሆን ፤ ወደ ሁለት መቶ ሰማንያ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በተሐዋሲው መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህ አሃዝ በውል ተረጋግጦ የተመዘገበ ቢሆንም፤ የመመርመር ዕድሉን ብሎም የልደት እና ሞት የምዝገባ ስረዓታቸው ደካማ በሆኑ ሃገራት ውስጥ ከኮሮና ጋር በተያያዘ የሞቱትም ሆነ በተሐዋሲው የተያዙ ቁጥር ቢገኝ እጅጉን ሊያሻቅብ እንደሚችል ይጠበቃል።
ዓለም በኮሮና ማዕበል እየተናጠች ቀጥላለች። ወረሽኙን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችም መልከ ብዙ ፈተና ተጋርጦበታል። በአንድ በኩል ተሐዋሲውን ለመከላከል እየተሰጡ ያሉ ክትባቶች ማጠናከርያ ተጨማሪ ክትባቶች መጠየቃቸው፤ በሌላ በኩል ተሐዋሲው በራሱ ባሕሪውን እየቀያየረ መከሰቱ ወረርሽኙን በዘላቂነት ለማቆም የሚደረጉ ጥረቶችን ውስብስብ እንዳደረገው ይነገራል።
የሆኖ ሆኖ ወረርሽኙ አሁን ከምንግዜውም ይልቅ ብርቱ ጉዳት እያደረሰ እና እንደ አዲስ የመሰራጨት አቅሙን አጠናክሮ በመጣበት በዚህ ወቅት ከወደ አሜሪካ የተሰማውና ከጥቂት ቀናት በፊት በዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር ፈቃድ ያገኙት የኮሮና ማከሚያ እንክብሎች ተስፋ ተጥሎባቸዋል። የሜርክ ኩባንያ ምርት የሆነው «ሞልኑፒራቪር» እና የፋይዘር ኩባንያ ምርት የሆነው ፓክስሎቪድ የተሰኙ አዳዲስ እንክብሎች በኮቪድ 19 ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ፈጣን ህክምና ካገኙ እስከ 90 በመቶ የመሞት ዕድል ሊያስቀር ያስችላል በሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩን እንደሚሉት ወረርሽኙን ለመግታት በዋናነት መደረግ ያለበት ክትባቱን መከተብ ነው። ነገር ግን በተሐዋሲው ከተያዙ በኋላ የተሻለ ህክምና እንዲኖር የእንክብሎቹ መገኘት በኮሮና ሳብያ ሕይወታቸው ያልፍ የነበረ ሰዎችን በማትረፍ ሂደት እጅጉን ጠቃሚ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
በሜርክ ኩባንያ የተመረተው የ«ሞልኑፒራቪር» እንክብል ባለፈባቸው የምርምር ሂደቶች ከቀላል እስከ መካከለኛው በአዋቂዎች ላይ የሚከሰት የኮቪድ 19 በሽታን ለማከም እንዲሁም በሳርስ ኮቪድ 2 የተሐዋሲ ዓይነት በተጠቁ ሰዎች ላይም በተመሳሳይ አዎንታዊ ውጤት ማስገኘቱ ተነግሯል። ነገርግ ን በጠና ታመው ሆስፒታል በገቡ ወይም በጽኑ ህሙማን መንከባከቢያ ውስጥ ያሉ አልያም በሽታው ጸንቶባቸው ከሞት አፋፍ ለደረሱ ሰዎች መድሃኒቱን መስጠት ለጊዜው ፈቃድ አለማግኘቱን የመድሃኒቱን ፈቃድ ማግኘት የሚያትተው መረጃ ያመለክታል።
«ፓክስሎቪድ » የተሰኘው እና የፋይዘር ኩባንያ ምርት የሆነው የኮሮና ማከምያ እንክብል በበኩሉ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ሆስፒታል ከሚያደርስ የህመም ምልክት በፊት ቤታቸው ውስጥ ሊወስዱ የሚችሉት አይነት መድኃኒት መሆኑ ተመልክቷል። ነገር ግን የተሐዋሲ የምርመራው አይነት የሳርስ ኮቪድ ሁለት የተሀዋሲ ዝርያ የተገኘባቸው እና ክብደታቸው ከ40 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ ሰዎች በሐኪም የታዘዘ መድሀኒት አልያም ህክምና ሊከታተሉ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
የሁለቱን መድሃኒቶች ውጤታማነት በተመለከተ ፕሮፌሰር ያሬድ ሲናገሩ እንክብሎቹ የተሐዋሲውን የፕሮቲን ውቅር በማዳከም ህመምተኛውን ከሕመሙ በፍጥነት እንዲያገግም አቅም ይፈጥራል። ምንም እንኳ መድሃኒቱ በስፋት ስራ ላይ ሲውል ወደ ፊት ሊጣሩ የሚኖርባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም። በመሆኑም ለእንክብሉ ውጤታመነት ታማሚዎች በተሐዋሲው በተያዙ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንክብሉን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
አሁን በመላው ዓለም በፍጥነት እየተሰራጨ ላለው ኦሚክሮን ለተሰኘው ልውጡ የተሕዋሲ አይነት ታማሚዎች ጭምር ውጤታማ እንደሆኑ የተነገረላቸው የእንክብል መድኃኒቶቹ ተሐዋሲውን በተለያየ መዋቅራዊ መንገድ እንደሚያዳክሙ ተመልክቷል። ነገር ግን ማንኛውም መድሃኒት የሚኖረው አይነት የጎንዮሽ ጉዳት ከአዲሶቹ የኮሮና ማከሚያ መድኃኒቶችም እንዳላቸው ፕሮፌሰር ያሬድ ይገልጻሉ።
መድሃኒቶቹ በዩናይትድ ስቴትስ ፈቃድ ማግኘታቸውን ተከትሎ የአውሮጳ ሕብረትም አባል ሃገራቱ መድሃኒቱን አገልግሎት ላይ ያውሉ ዘንድ ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል። የልውጡ የኮሮና ተሀዋሲ ኦሚክሮን ስርጭት አሁን ብርቱ ስጋት በመደቀኑ ጀርመንን የመሳሰሉ የአውሮጳ ሃገራት ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ወደ መጣሉ ተመልሰዋል። ይኽም በርካታ ሰው ከተከተበ በአዲሱ ጎርጎርዮሳዊ ዓመት 2022 ከተሐዋሲው ስጋት ነጻ እንደሚኮን የነበረውን ተስፋ አደብዝዞታል። ነገር ግን አሁንም የህክምና ባለሞያው አንድ ነገር ይመክራሉ፤ ተመራማሪዎች አዳዲስ የተሐዋሲ መከላከያ ክትባት እና ማከሚያ መድሃኒት ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ልክ ፤ ተጠቃሚው የተሐዋሲውን መከላከያ በመከተብ እራሱን መጠበቅ ቢችል ተሐዋሲውን ለመቆጣጠር ቀኑ ሩቅ አይሆንም። እንግዲህ አድማጮች እኛም ለዛሬ ያልነውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዝግጅታችን በዚሁ ቋጨን ። ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እንጠብቃችኋለን ።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሰ