ተሻሽሎ የቀረበው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ምንነት
ሐሙስ፣ ኅዳር 15 2015
ተሻሽሎ የቀረበው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ መከላከያ ሠራዊቱ የሚመራበትንና ከተቋሙ ወቅታዊ ግዳጅ ጋር የሚጣጣም ብሎም የወደፊቱን ግዳጅ ታሳቢ ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የቀረበ ነው ተብሏል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሚቋቋሙት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እና ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የተባሉ ሁለት ደረጃዎች ያሉት ነው።እነዚህ ፍርድ ቤቶች የዘር ማጥፋት ወንጅልን ጨምሮ የጦርነት ማቆም ወይም የሰላም ስምምነት ጉዳዮችን እንዲሁም በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ የጦርነት ወንጀሎችን እንዲዳኙ ሥልጣን የተሰጣቸው ናቸው። የእነዚህን ፍርድ ቤቶች ዳኞችን ሥነ ምግባር ፣ የሥራ አፈፃፀም ብቃት ፣ ተጠያቂነትና ነፃነት የሚከታተል ከወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለት ፣ ከመደበኛ ፍርድ ቤቴች ሁለት፣ እና ከወታደራዊ አዛዦች አንድ በድምሩ አምስት አባላት ያሉት የስነ ምግባር ኮሚቴ እንደሚቋቃም ረቂቁ አስፍሯል።
ቀጣዩ የሶሎሞን ሙጬ ዘገባ ለወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የተሰጠውን የአዋጁን ክፍል በዝርዝር ይመለከታል።
ተሻሽሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ የመከላከያ ሠራዊት በምድር ፣ በአየር ፣ በባሕር ፣ በሳይበር እና በጠፈር መዋጋት በሚችል መልኩ ይደራጃል ይላል።ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን የሚመለከተው የረቂቅ አዋጁ ክፍል አምስት በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የወታደራዊ ፍትሕ ሥራን የሚያከናውኑ 5 አካላት መቋቋማቸውን አስፍራል።እነዚህም ወታደራዊ ፖሊስ ፣ ወታደራዊ መርማሪ ፣ ወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ ፣ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እና ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ናቸው።
ወታደራዊ ፖሊስ በሠራዊቱ ውስጥ ወንጀልን እንዳይፈፀም ይከላከላል ፣ ተጠርጣሪን ይይዛል። ወታደራዊ መርማሪ ምርመራ የመጀመር ወይም የማስጀምር እና ሌሎች ኃላፊነቶች አሉት። የወታደራዊ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ሥር በሚወድቁ ማናቸውም የወንጀል ጉዳዮች ላይ ክስ ያቀርባል ፣ ይከራከራል። ወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ደግሞ ለተከሰሱ ወይም ምርመራ ለሚደረግባቸው ሰዎች የጥብቅና አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ በረቂቁ ሰፍሯል።
ከአምስቱ አካላት ውስጥ ወታደራዊ መርማሪ እና ወታደራዊ ዐቃቤ ሕግ የተባሉት ተጠሪነታቸው ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሲሆን የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እና ተከላካይ ጠበቃ ደግሞ ለመከላከያ ሚኒስትር ተጠሪ ይሆናሉ ብሏል ድንጋጌው።
በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሚቋቋሙት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ሁለት ደረጃዎች አሉት። ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እና ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ናቸው። የፍርድ ቤቶቹ ዳኞች የሥራ ዘመናቸው አምስት ዓመት ሲሆን የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች በመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ደግሞ በመከላከያ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ይሾማሉ ይላል ረቂቅ አዋጁ።እነዚህ ዳኞች ከማንኛውም የመንግሥት አካልም ሆነ ባለስልጣን ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትም ሆነ ከማንኛውም ሰው ተጽእኖ ነፃ ሆነው ሥራቸውን ያከናውናሉ በማለት በረቂቁ አንቀጽ 49 ሥር ተደንግጓል።ይህንን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ በቁጥር በዛ ያሉ የሕግ ባለሙያዎችን እና ዐዋቂዎችን፣ ጠበቆችን፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አስተማሪዎችን አስተያየት እንዲሰጡበት ጠይቀናል። አብዛኞቹ ግን መናገር አልፈለጉም።ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ ግን አጭር አስተያየት ሰጥተዋል።ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን በሚምለከተው አንቀጽ ሥር የዳኞችን ሥነ ምግባር ፣ የሥራ አፈፃፀም ብቃት ፣ ተጠያቂነትና ነፃነት የሚከታተል ከወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች ሁለት ፣ ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ሁለት፣ እና ከወታደራዊ አዛዦች አንድ በድምሩ አምስት አባላት ያሉት የሥነ ምግባር ኮሚቴ ይቋቋማል ተብሎ ተደንግጓል።
እነዚህ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ እና እንደአስፈላነቱ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ እንዲሁም የማስረጃ ሕጎችን መሰረት በማድረግ ያስችላሉ ተብሎ ተቀምጧል። በሌላ በኩል በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ዳኞች መካከል በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ልዩነት ሲኖር በድምፅ ብልጫ ይወሰናል የሚል የሕግ ጭብጥ ተቀምጧል። ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በወታደራዊ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎችን ፣ በሠራዊት አባላት መካከል በሚፈፀሙ የግድያና የእስገድዶ መድፈር እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንጀሎች እና የአካል ማገድል ወንጀሎችን ፣ በጦር ሜዳ ግዳጅ ወቅት ከሰራዊቱ ጋር የዘመቱ ሲቪሎች ፣ የመደበኛ ፖሊስ አባላትና ሚሊሺያዎች በሚፈጽሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች ላይ የዳኝነት ስልጣን አለው።
ይህ ድንጋጌ በእንዲህ ያለው የጦር ሜዳ ግዳጅ ወቅት አጥፊዎችን ለመጠየቅ በጎ ድንጋጌ ሆኖ ቢገኝም ፣ በወዶ ዘማችነት አገርን ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነው የታደጉ ዜጎችን አጃምሎ ተጠያቂ እንዳያደርግ በብዙዎች ዘንድ ሥጋት አጭሯል።
ሆኖም በረቂቁ የወታደራዊ ፍርድ ዳኞች ከዳኝነት ስልጣናቸው ጋር በተያያዘ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ፣ ትእዛዞች ፣ብይኖች በማንኛውም ሰው ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆኑና ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንደሚሰሩ ይደነግጋል።የኢትዮጵያ የቀድሞው ሠራዊት ማሕበር ፕሬዝዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ አጭር አስተያየት አጋርተውናል።
ተሻሽሎ የቀረበው የመከላከያ ሠራዊት ረቂቅ አዋጅ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የየደረጃውን ትምህርት ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃዳቸው የብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ፣ ለዚህም ቀደም ብሎ ወታደራዊ ስልጠና ሊወስዱ እንደሚገባ የሚያደርግ አንቀጽ ጭምር ደንግጓል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ