1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ስለ አማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ዓርብ፣ ሐምሌ 28 2015

«አሁን የትግራይ ግጭት ትንሽ መልክ የያዘ ቢመስልም ቀሪ የቤት ስራዎች ያሉበት ነው።የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ከዚህ የሚጠቀስ ነው።አገሪቱ ትልቁ ግዛት ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረው ግጭትን በሰላም እልባት ለመስጠት በታንዛኒያ የተጀመረው ድርድርም የሰመረ አይመስልም፡፡አሁን ደግሞ ሁለተኛው ሰፊ የአገሪቱ ግዛት አማራም ወደ ሰፋ ግጭት መግባቱ ያሰጋል።»

Pro Merera Gudina vorsitzender OFECO
ምስል DW/S. Wegayehu

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ስለ አማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ስለሀገሪቱ አለመረጋጋት

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ መልኩን ቀያይሮ እየቀጠለ ያለው አለመረጋጋት አገሪቱን በብዙ መልኩ የሚያዳክም እና አንድነቷንም የሚፈታተን መሆኑ ተገለጸ፡፡ፖለቲከኞች ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ከየትኛውም ግጭት መባባስ አስቀድሞ ቅድሚያውን ለሰላም በመስጠት መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ ያለፉትን ሶስት ዓመታት የጎላ የእርሰ በርስ ጦርነትና ሰፋፊ ግጭቶች ውስጥ ለነበረች ኢትዮጵያ ሰሞኑን በአገሪቱ ሁለተኛው ሰፊ ክልል በሆነው በአማራ ክልል ጎልቶ የተስተዋለው አለመረጋጋት በርግጥም ለበርካቶች በአሳሳቢነቱ ይጠቀሳል፡፡ በክልሉ የተንሰራፋውን ግጭት አለመረጋጋት ተከትሎ ከትናንት በስቲያ የአገር መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ስዝቱ፤ ትናንት ደግሞ የክልሉ መንግስት ግጭቱ ከአቅሜ በላይ በመሆኑ የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ በመግባት ያረጋጋ ሲል ጠይቋል፡፡ በዛሬው እለትም የክልሉን አለመረጋጋት እና የችግሩን ጥልቀት የሚያሳይ በሚመስል መልኩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው ክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ 
የአማራ ክልሉ አለመረጋጋት አሁን ላይ ጎልቶ ይነሳ እንጂ በተለይም በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎችም ተደጋግሞ በስፋት የሚነሱ ግጭቶች ዘላቂ እልባትን ያገኙ አይመስሉም፡፡ ይህ አሳሳቢ ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡን የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና፤ አሁናዊ ሁኔታው ኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ናት የሚል ምስልን ሚያጎላ ነው ይላሉ፡፡“አይናችን እያየ አገሪቱ ወደ ሰፋ ቀውስ እያመራች ነው፡፡ አሁን የትግራይ ግጭት ትንሽ መልክ የያዘ ብመስልም ቀሪ የቤት ስራዎች ያሉበት ነው፡፡ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ከዚህ የሚጠቀስ ነው፡፡ የአገሪቱ ትልቁ ግዛት ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረው ግጭትን በሰላም እልባት ለመስጠት በታንዛኒያ የተጀመረው ድርድርም የሰመረ አይመስልም፡፡ አሁን ደግሞ ሁለተኛው ሰፊ የአገሪቱ ግዛት አማራም ወደ ሰፋ ግጭት መግባቱ አይናችን እያየ አገሪቱነ  ወደ ከፋ ችግር እንዳይወስዳት ያሰጋል፡፡”
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፖለቲከኛ ራሔል ባፌ በፊናቸው አሁን ላይ በአገሪቱ መልኩን ቀያይሮ የሰፋ ግጭት አሳሳቢ ነው ለማንም እልባት የማይሆን ነው ይላሉ፡፡ “እንደ ፖለቲከኛ፣ እናትና ሴት የሚሰማን ትናንት ከህወሓት ጋር በገባንበት ጦርነት ስንት ሰው ነው ያለቀው፡፡ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የሚያስከብር ታደር ጭምር አላለቀም ወይ፡፡ ከዚያ በኋላ በሰላም አልጨረስንም ወይ፡፡ ታዲያ አሁን የሚከፈተው ሌላው ምእራፍ ጦርነት አግባብነት አለው ወይ ብለን ስናነሳ በጭራሽ ነው መልሱ፡፡” 
ፖለቲከኞቹ በየትኛውም የአገሪቱ አቅጣጫ የሚከሰትና እየተስተዋለ ያለው ዘለቄታዊ እልባቱ ሊገኝ የሚችለው በውይይት መግባባት ላይ በመድረስ ነው ይላሉ፡፡ ፖለቲከኛ መረራ እንደሚሉት “ትልቁ የአገሪቱ ችግር በፖሊካዊ ድርድር እና በሃሳብ የበላይነት በሚያምን አመራር እጦት መፈተኗ ነው፡፡ ለየትኛውም አከባቢ አለመረጋጋትም መፍትሄ ሰላም ነው” ብለዋል፡፡ ዶ/ር ራሔር በፊናቸው “ከእስካሁኑ ጦርነት ውጤት በመማር በተሌም መንግስት በሆዴ ሰፊነት ለሰላም እድል ብሰት፤ ሁሉም ተዋጊ ወገኖችም ህዝቡን ወርደው በማወያየት ለሰላም ቅድሚያ ብሰጡ መልካም ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡ኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ በቆየችባቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች መመዝገባቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW