ተቃውሞ እና እስር በወልቂጤ
ዓርብ፣ ነሐሴ 20 2014በደቡብ ክልል ስር በሚገኘው የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ፤ ለሁለተኛ ቀን የሥራ ማቆም እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን የከተማይቱ ነዋሪዎች ገለጹ። የአድማው መንስኤ ከጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት አድማውን የተጠራው በወጣቶች፣ ምሁራን እንዲሁም በአገር ሽማሌዎች በጋራ ነው። ረዕቡ ከሰአት በኋላ በከተማዋ የተበተነውን የ ሁለት ቀን የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማንም ማኅበረሰቡ ተቀብሎ ተግባራዊ አንዳደርገው ገልጸዋል። ዶቼ ቬሌ ያነጋገረው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ አብዱበከር ከማል ተቃውሞው በታቀደለት መልኩ እየሄደ ያለው ህዝቡ ጥያቄውን የራሱ ስላደረገው ነው ይላሉ።
«የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማው ትላንት ነው የጀመረው ለሁለት ቀን ነው የሚቆየው ። ተቃውሞውን የሚመራው በምሁራን በወጣቶች በአገር ሽማግሌዎች የተደራጁ ብዙ ንኡሳን ኮሚቴ ነው ያሉት ተጠሪነታቸው ግን ለአገር ሽማገሌዎች ነው ትግሉ በታቀደው መሰረት ነው እየሄደ ያለው ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ህዝቡ ጥያቄውን የራሱ ስላደረገው ጭምር ነው ።ወረቀቱ ሙሉ ለሙሉ ለህዝቡ አልተዳረሰም ነበር ኮማንድ ፖስቱ ግን በድምፅ ማጉያ ሠራተኛ ጭኖ ነገ በተጠራው አድማ ላይ ሱቃችሁን ብትዘጉ ለአንድ አመት የሥራ ቦታችሁ ይታሸጋል ሲሉ ማህበረሰቡ አድማ እንዳለ ተረዳ ትላንት አንድ ሁለት ቤት አሸጉ የሚሰማቸው ሲያጡ ተዉት» ብለዋል። ሌላኛው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋ ነዳ በበኩላቸው ማኅበረሰቡ የታሰሩ አመራሮችና ወጣቶች በመኖራቸው ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ እንዳለ ይገልጻሉ።
«አድማው ከትላንት ወዲያ ከሰአት በኃላ በተበተነ ወረቀት ነው ጥሪውን ያስተላለፈው ማን እንደሆነ አላውቅም በአሁኑ ሰአት ከተማዋ ጭር ብላለች የታሰሩ አመራሮች እና ወጣቶች በመኖራቸው ህብረተሰቡ ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ነው በዛ ላይ የዞኑ ምክር ቤት ያፀደቀው ውሳኔ ስላላ ውሳኔው ወደ ሪፈረንደም እንዲሄድ እና የታሰሩት ልጆች ይፈቱልን የሚል ጥያቀ ነው ያለን» ብለዋል።
ስለታሰሩ አመራሮች እና ወጣቶችን በተመለከተ እንዲሁም ከቤት ባለመውጣት አድማው ላይ አስተያየታቸን እንዲሰጡን ወደ ደቡብ ክልል የኮማንድ ፖስት ኮሚሽን በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ልናካትት አልቻልንም።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የጉራጌ ዞንን ጨምሮ ሌሎች አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል እንዲቀጥሉ መወሰኑ ይታወሳል።
ማህሌት ፋሲል
ሸዋዬ ለገሰ