1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተባብሶ የቀጠለው ፆታዊ ጥቃት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 1 2012

የሴቶች ቀን ተለይቶ ለምን ይታሰባል የሚሉ አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩም በተቃራኒው አንድ ቀን ያንሳል 365ቱም ቀን የሴቶች ጉዳይ ይወሳ የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ስለሴቶች መብት መከበር ብዙ በሚነገርበት በዚህ ዘመን ግን በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከዕለት ወደዕለት እየጨመሩ መሄዳቸውን  መረጃዎች ያመለክታሉ።

Äthiopien | Proteset | Entführte Studenten
ምስል privat

«ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን»

This browser does not support the audio element.

ከጎርጎሪዮሳዊው 1910 ጀርመናዊቷ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባል ክላራ ሴትኪን አሜሪካውያን ሴቶች የጀመሩት የሴቶችን ቀን የማክበር ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥያቄ አቀረቡ። 100 የሚሆኑ ከ17 ሃገራት የተውጣጡ ሴቶች በሃሳባቸው ተስማምተው በቀጣዩ ዓመት 1911 ማለት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የሴቶች ቀን በኦስትሪያ፤ ዴንማርክ፣ ጀርመን እና ስዊትዘርላንድ በዚሁ የዘመን ቀመር መጋቢት 19 ቀን ተከበረ። የሴቶችን ቀን ማክበሩ አንድ ነገር ሆኖ ዛሬም በሀገሪቱ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች መበራከታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በጥቂት ሴቶች አሳሳቢነት ተጠንስሶ ለመጀመሪያ ሁለት ዓመታት በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር መጋቢት 19 ቀን ይከበር የነበረው የዓለም የሴቶች ቀን ከ1913ዓ,ም ጀምሮ በመጋቢት 8 ላይ ሲከበር ቆይቷል። ዕለቱ በተመድ ዕውቅና ያገኘው ግን በ1975 ነው በዚሁ አቆጣጠር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ታዲያ በየዓመቱ መሪ ቃል እየተሰጠው ዓመታት አሳልፏል።  ዕለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታሰብ ለፆታ እኩልነት የሚቀርበው ጥሪ እና ቅስቀሳ እንዳለ ሆኖ ከፖለቲካው እስከማኅበራዊ ዘርፎ ሴቶች ያገኙትን ስኬት የሚያወሳ እንዲሆን የታለመ ነው። ስለሴቶች መብት ኢትዮጵያ ውስጥ በአደባባይ መሞገት ከተጀመረ ወዲህ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ላይ የተጫኑ ቀንበሮች በይፋ ኅብረተሰቡ እንዲነጋገርባቸው ማድረግ ቢቻልም መሠረታዊ የሆኑ ለውጦች ተደርገዋል ለማለት አያስደፍርም። ዛሬም በባሕል ስም የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አልቀሩም። በምሳሌነትም የሴት ልጅ ግርዛት እና ጠለፋን መጥቀስ ይቻላል።

የሴቶች ቀን ተለይቶ ለምን ይታሰባል የሚሉ አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩም በተቃራኒው አንድ ቀን ያንሳል 365ቱም ቀን የሴቶች ጉዳይ ይወሳ የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ስለሴቶች መብት መከበር ብዙ በሚነገርበት በዚህ ዘመን ግን በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከዕለት ወደዕለት እየጨመሩ መሄዳቸውን  መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደውም ከሦስት ዓመታት በፊት የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ እንደጠቆመው በፆታዎች መካከል ያለው ልዩነት እንዲወገድ ሌላ 100 ዓመታት መጠበቅ ግድ ነው። ለዚህም ነው በየዓመቱ በመላው ዓለም የሚገኙ ሴቶች በአድሎዋዊው ዓለም ውስጥ ታግለው ለስኬት የበቁትን ሴቶች እያደነቁ፣ በቀሪዎቹ ላይ አሁንም የሚታየው ተባለጥ ትኩረት እንዲያገኝ የጋራ ድምፃቸውን የሚያሰሙት። ከትናንት በስተያ በመላው ዓለም ዕለቱ ሲታሰብ በተለይ በላቲን አሜሪካ ሃገራት እና በቱርክ፤  ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በመቃወም እና ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ክፍያ የጠየቁ የሴቶች ሰልፎች ተካሂደዋል። ሜክሲኮ ውስጥ ደግሞ በማግሥቱ ሰኞ ዕለት በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትና ጥቃት አድርሶ ያለቅጣት መታለፍን ያወገዘ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል። በዕለቱም ሴቶች በሥራ ገበታቸው ባለመገኘት፤ ያለ ሴት ዕለቱ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ሞክረዋል። በቺሌ እና አርጀንቲናም ተመሳሳይ ርምጃ ሴቶቹ ወስደዋል። መብታቸው እንዲከበርላቸው  ለመጠየቅ አደባባይ የወጡ የቱርክ ሴቶችን ለመበተን ፖሊሶች እንባ አስመጪ ጋዝ መጠቀማቸው ተሰምቷል።

ምስል Getty Images/AFP/P. Ojisua

ኢትዮጵያ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሴቶች ቀን መታሰብ ከተጀመረ 44 ዓመታት እንደዋዛ አልፈዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ምንም እንኳን ጠንካራ ሴቶች የተለያዩ መሰናክሎችን አልፈው ለስኬት ቢበቁም በተለይ በጓዳ የሚፈፀመው ፆታዊ ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ ይነገራል። ሴታዊት የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ለሴቶች መብት መከበር የሚሟገት ድርጅት መሥራች እና አስተባባሪ  የሆኑትን ዶክተር ስህን ተፈራን በአሁኑ ጊዜ የሴቶች የመብት ይዞታ ኢትዮጵያ ውስጥ በምን ደረጃ ይገኛል ብለናቸው አዎንታዊ ያሉትን አስቀድመው ጥቃት ተባብሷል የሚለውን የሚያጠናክር ምላሽ ሰጡን።

ለጥቃቱ መበራከት አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እና እርምት እንዳያገኙ  ማመቻቸት ያልቻለው  ደካማ የፍትህ ሥርዓት ዋና ተጠያቂ ነው እንደመብት ተሟጋቿ። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዘገባዎችም ፆታዊ ጥቃት እያደረሱ ያለቅጣት የሚታየፉ በመበርከታቸው አዘውትሮ እና አብዝቶ ስለሴቶች መብት እና ፆታዊ እኩልነት ግንዛቤ ሊያስጨብጡ የሚያግዙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ  እንደሚበጅ ይመክራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሴቶች መብት በመቆርቆር የሚፈፀሙ ጥቃቶች አደባባይ እንዲወጡ ማድረግ የቻሉ ጥቂት የማይባሉ ድርጅቶችና ማሕበራት መኖራቸው ይታወቃል። በምዕራብ ኢትዮጵያ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ  ጥቂት የማይባሉ ሴት ተማሪዎች  የመታገታቸው ዜና ከተማ ከ90 ቀናት በላይ ሆኗል። በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩ ተደጋግሞ እየተነሳ  ለሴቶች መብት የሚሟገቱት የት አሉ የሚል ጥያቄ እየቀረበ ነው። የሴቶችን ቀን ስናስብ ነገ በየትኛውም መስክ ሊሰማሩ ይችሉ የነበሩት ወጣት ሴቶች ጉዳይ ማነጋገሩ ቀጥሏል እና ለሴታዊት ድርጅት መሥራች እና አስተባባሪ ዶክተር ስሂን ይህንኑ አነሳንላቸው።

እነዚህን የደረሱበት ያልተሰማ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ጉዳያችን ብለው ድምፃቸውን የሚያሰሙላቸው ጥቂትም ቢሆኑ ሴት ወንድ ሳይል እንቅስቃሴ የጀመሩ ወገኖች መኖራቸው በእርግጥ መዘንጋት የለበትም። መልስ የሚፈልጉ ዓይኖችም መንግሥት ላይ እንዳተኮሩ መሆኑ ይታወስ።

ምስል privat

ኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤቷን 50 በመቶ ሴቶች ካደረገች ዓመት አለፈው። ሀገሪቱ በፓርላማ ሥርዓት የምትመራ በመሆኗ መንግሥታዊው ሥልጣን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር ቢሆንም ከአፍሪቃ ሃገራት ላይቤሪያ፤ ማላዊ ሞሪሺየስ ቀጥላም ኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝደንትን ሰይማለች። በቀድሞ ታሪኳ ሴት ነገሥታት እንደነበሯት ሳይዘነጋ። ምንም እንኳን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እየጨመረ መሄዱ አዎንታዊ ቢሆንም፤ ዛሬም የገጠሯ ብቻ ሳትሆን በከተማም በትምህርቱም ሆነ በገንዘብ አቅሙ የሌላት ሴት መሠረታዊ መብቶቿ በተገቢው መልክ እንዲከበሩላት ብዙ መሥራት የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል። የዘንሮውን የዓለም የሴቶች ዕለት አስመልክተው ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ  ባስተላለፉት መልእክትም «ሴቶችን በማብቃትና እኩልነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ሥራው ተጠናቋል ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። ሥራው ገና ተጀመረ እንጂ።» ነው ያሉት። እኛም ይህንኑ  አፅንኦት በመስጠት ለቃለምልልሱ የተባበሩን ዶክተር ስሂንን በማመስገን ለዕለቱ ያልነውን በዚሁ እናብቃ። አድማጮች አስተያየት ጥቆማችሁ አይለየን።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW