1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተደራራቢ ቀውሶች በበረታባት ኢትዮጵያ ለሰብአዊ ርዳታ ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ የካቲት 20 2016

በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዐሥር ወራት ርዳታ ለማቅረብ 3.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መንግሥት እና አጋሮቹ ለለጋሾች ያዘጋጁት ዕቅድ አሳይቷል። ዕቅዱ ግጭት፣ የከባቢ አየር ለውጥ ዳፋ እና ወረርሽኞች በተደራረቡባት ኢትዮጵያ ርዳታ በአፋጣኝ እና በዘላቂነት ካልቀረበ ሰብአዊ ቀውስ ሊቀሰቀስ እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ ነው።

 Äthiopien humanitäre Hilfe
ምስል AP Photo/picture alliance

ተደራራቢ ቀውሶች በበረታባት ኢትዮጵያ ለሰብአዊ ርዳታ ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል

This browser does not support the audio element.

ድርቅ በበረታባቸው የአፋር፣ የአማራ እና የትግራይ አካባቢዎች የሚቀርበውን ሰብአዊ ርዳታ “በአፋጣኝ ለማሳደግ” የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እና የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ 17 ሚሊዮን ዶላር መድበዋል። ከተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ መልስ ማዕከላዊ ቋት (CERF) የተመደበው ገንዘብ በኤል ኒኞ የአየር ጠባይ ምክንያት የተከሰተ ድርቅ “የፈጠረውን ጥልቅ ሥጋት” የሚያሳይ ነው።

ግሪፊትዝ “በኤል ኒኞ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ እና እየተካሔዱ ያሉ ግጭቶች በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ጥለዋል” ብለዋል። ከግሪፊትዝ ቀደም ብሎ የአውሮፓ ኅብረት ለስድስት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት 171 ሚሊዮን ዩሮ ርዳታ ይፋ ሲያደርግ በኢትዮጵያ “ተጋላጭ ለሆኑ ማኅበረሰቦች የሕይወት አድን ርዳታ ለማቅረብ” 38 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ብርቱ ሰብአዊ እና ኤኮኖሚያዊ ኪሳራ ያደረሰባቸው የአፋርየአማራ እና የትግራይ ክልሎች የገጠማቸውን ድርቅ እና የምግብ ዋስትና እጦት ለመቋቋም የሚችሉበት አቋም ላይ አይደሉም። ማርቲን ግሪፊትዝ እና የአውሮፓ ኅብረት የመደቡት ገንዘብም ቢሆን በኢትዮጵያ ለተቸገሩ ሰብአዊ ርዳታ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው አኳያ እጅግ አነስተኛ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ፖል ሐንድሌይ “ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብአዊ ርዳታ ይፈልጋሉ። ከመንግሥት ጋር 15.5 ሚሊዮን ሰዎችን ለመርዳት የሰብአዊ ግብረ መልስ ዕቅድ ይፋ አድርገናል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሰብአዊ ርዳታ ለማቅረብ 3.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ይፋ ያደረገው ዕቅድ በመንግሥት እና አጋሮቹ ለለጋሾች የተዘጋጀ ነው።

በጎርጎሮሳዊው 2024 በኢትዮጵያ ሰብአዊ ርዳታ ለማቅረብ ያስፈልጋል ከተባለው 3.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለምግብ የተመደበው ነው። የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ 15.8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል 10.4 ሚሊዮን የሚሆኑትን ለማገዝ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እና የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ “በኤል ኒኞ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ እና እየተካሔዱ ያሉ ግጭቶች በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ጥለዋል” ብለዋል።ምስል Martial Trezzini/dpa/Keystone/picture alliance

በሠነዱ መግቢያ የአደጋ ሥጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሚታዩትን “አዳዲስ እና የተወሳሰቡ ቀውሶች ለመፍታት መንግሥታቸው አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ” መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ኮሚሽነሩ እንዳሉት “እየጨመረ ለመጣው ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እና የከፋ ጥፋትን ለመቀልበስ በባለ ድርሻ አካላት መካከል የተጠናከረ ትብብር” ያስፈልጋል።

የሰብአዊ ሁኔታው በደጋማው ሰሜን ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ለውጥ መባባሱን የሚናገሩት ፖል ሐንድሌይ “በኤል ኒኞ የአየር ሁኔታ ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት መጨረሻ መሰብሰብ የነበረበት ሰብል ከሽፏል። በዚህም ሳቢያ ብዙ ምግብ ሊኖራቸው ይገባ የነበረ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ረሐብ ገጥሟቸዋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኃላፊው እንዳሉት ቀውሱ እስከ መጪው መስከረም ሊከፋ ይችላል የሚል ሥጋት ጭምር አለ።  

ኮንሶደቡብ ኦሞ እና የቦረና ዞኖችን ጨምሮ በደቡባዊ ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተራዘመ ድርቅ ባስከተለው ተጽዕኖ የምግብ ዋስትና እጦት ተጋርጦባቸዋል። በአካባቢው ስድስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በመክሸፋቸው የተከሰተው ድርቅ ባለፉት 40 ዓመታት ከታየው ሁሉ የከፋ ነው።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የታየው የወባኮሌራ እና የኩፍኝ ወረርሽኝ ሊቀጥል እንደሚችል ይኸው የሰብአዊ ግብረ መልስ ዕቅድ ያሳያል። በዓለም የምግብ መርሐ-ግብር የብራስልስ ቢሮ ዳይሬክተር ፍሬድሪክ ሊ ኦልሰን እንደሚሉት ኢትዮጵያ እና ሰብዓዊ ርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የተጋፈጡት “አጣዳፊ እና እየተባባሰ የሚሔድ ሰብአዊ” ቀውስ ነው።

ኃላፊው የአውሮፓ ፓርላማ ሦስት ቋሚ ኮሚቴዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ሲወያዩ ተጋብዘው “አስከፊ መዘዝ ያስከተሉ የበርካታ ችግሮች መገጣጠም እና አንዱ በሌላው ላይ መደራረብ” የቀውሱ ሥረ-መሠረት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ 15.8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መካከል 10.4 ሚሊዮን የሚሆኑትን ለማገዝ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል።ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

ኢትዮጵያውያን የትጥቅ ግጭት፣ የከባቢ አየር ለውጥ ያስከተለው ዳፋ፣ ወርሽኞች እና የዋጋ ግሽበት አንዳቸው በሌላው ላይ እየተደራረቡ ይፈትኗቸው እንደያዙ ያስረዱት ኦልሰን “በርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች በግጭት ወድመዋል፤ ወይም አሁንም እየወደሙ ነው። በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት 4.5 ሚሊዮን ሰዎች በመፈናቀላቸው ከፍተኛ የሰብአዊ ርዳታ ፍላጎት ተፈጥሯል” ሲሉ የቀውሱን ብርታት ለአውሮፓ ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ይፈጸማል የተባለው የምግብ ርዳታ ከተመደበላቸው ተረጂዎች ወደ ሌላ የማዛወር ድርጊት “ቀድሞም የነበሩ ተጋላጭነቶችን በማባባስ” ለምግብ ዋስትና እጦት አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ኦልሰን ተናግረዋል። ይኸ ጉዳይ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት እና የዓለም የምግብ መርሐ ግብር ለተወሰኑ ወራት በኢትዮጵያ ለተቸገሩ የሚያቀርቡትን የምግብ ርዳታ እንዲያቋርጡ አድርጓቸው ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ብቻ በመንግሥት ስሌት 28.7 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሶበት የዕዳ ክፍያ፣ የበጀት ጉድለት እና የዋጋ ግሽበትን የመሳሰሉ ተግዳሮቶች የተጫኑት ኤኮኖሚ ሰብአዊ ቀውሱን መሸከም የሚችልበት ትከሻ የለውም። በተለይ የመከላከያ እና የዕዳ ክፍያ በጀት መጨመር መንግሥት ለማኅበራዊ ዘርፎች የሚመድበውን ወጪ እንዲቀንስ አድርጎታል።

ሀገሪቱ ከውጭ የምታገኘው ብድር እና ዕርዳታ በማሽቆልቆሉ ምክንያት ለድህነት ቅነሳ እና ለማኅበራዊ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም የሚመደበው በጀት ቀንሷል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ግምት መሠረት ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ ግንባታ፣ ውኃ፣ ኃይል እና ግብርናን ለመሳሰሉ ደሀ ተኮር ዘርፎች በዚህ ዓመት የተመደበው ገንዘብ ከፌድራል መንግሥቱ በጀት 33 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። እነዚህ ዘርፎች በጎርጎሮሳዊው 2020 ከፌድራል መንግሥት በጀት 59 በመቶ ድርሻ ነበራቸው።

በመጋቢት 2015 ወደ 34 በመቶ ገደማ አሻቅቦ የነበረው የዋጋ ግሽበት የተወሰነ ቅናሽ አሳይቶ ባለፈው ታኅሳስ ወደ 28 በመቶ ገደማ ዝቅ ብሏል። “በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ቀውሶች ምክንያት በኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ የደረሰው የዋጋ ግሽበት በመላው ዓለም ከፍተኛ ከሚባሉት መካከል ነው” ያሉት በዓለም የምግብ መርሐ-ግብር የብራስልስ ቢሮ ዳይሬክተር “በዚህም ሳቢያ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ሲያሻቅብ የኢትዮጵያውያን የመግዛት አቅም ተሸርሽሯል” ሲሉ ተናግረዋል።  

በዓለም የምግብ መርሐ-ግብር የብራስልስ ቢሮ ዳይሬክተር ፍሬድሪክ ሊ ኦልሰን በኢትዮጵያ አጣዳፊ እና እየተባባሰ የሚሔድ ሰብአዊ ቀውስ መፈጠሩን ተናግረዋል። ምስል Claire Nevill/AP Photo/picture alliance

በኢትዮጵያ “አፋጣኝ እና ዘላቂ ሰብአዊ ርዳታ” ለማቅረብ ብርቱ የገንዘብ እጥረት መኖሩን ፍሬድሪክ ሊ ኦልሰን ለአውሮፓ ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሸሹ አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች በዚሁ የገንዘብ እጥረት ምክንያት ከሚያስፈልጋቸው ዕለታዊ ምግብ 60 በመቶ ብቻ ይሰጣቸዋል።

ኦልሰን እንዳሉት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ከለጋሾች ገንዘብ ካላገኘ በመጪው ሚያዝያ ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ ርዳታ ሊያቋርጥ ይችላል። በጎርጎሮሳዊው 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ርዳታ በከፍተኛ መጠን ካልቀረበ ኦልሰን “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ” እንደሚጋፈጡ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ ያዘጋጁት የሰብአዊ ግብረ መልስ ዕቅድ ተመሳሳይ ሥጋት የተጫነው ነው። ለጎርጎሮሳዊው 2024 ያስፈልጋል የተባለ የገንዘብ መጠን ካለፉት ሁለት ዓመታት አኳያ አነስተኛ ቅናሽ ቢያሳይም የለጋሾችን ትኩረት የሚሹ አንገብጋቢ ቀውሶች በመበርከታቸው የተፈለገውን ያክል የመገኘቱ ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

በጎርጎሮሳዊው 2023 ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል ከተባለው 4 ቢሊዮን ዶላር የተገኘው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ወይም 34% በመቶ ብቻ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ፖል ሐንድሌይ የተጠቀሰውን ገንዘብ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ቢስማሙም “መልዕክታችን ሰሚ አግኝቶ ለጋሾች መልስ ለመስጠት እና ለማገዝ ከሚችሉበት አቋም ላይ ይሆናሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የተጠየቀው ገንዘብ ካልተገኘ ሊከሰት የሚችለው ቀውስ ብርቱ እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ ያዘጋጁት የሰብአዊ ግብረ መልስ ዕቅድ ያስጠነቅቃል። ፖል ሐንድሌይ “ገና ካሁኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ብርቱ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ይገጥማቸዋል ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ብርቱ የተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚገጥማቸው ሰዎች “የት እንደሚገኙ ለመለየት እና ለማከም የሚያስችለን ሥርዓት ሊኖረን ይገባል” ያሉት ሐንድሌይ የሚያስፈልገው ገንዘብ ካልተገኘ “ቁጥሩ ሊጨምር፤ በርካታ ሰዎችም ሊሞቱ ይችላሉ” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW