1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ተዳፍኖ የቆየው የሶርያ የርስ በርስ ጦርነት ዳግም እያገረሸ ይሆን?

ሰኞ፣ ኅዳር 23 2017

የሶርያ አማጽያን በፕሬዝደንት በሺር አል አሳድ መንግሥት ላይ የከፈቱት ጥቃት ተዳፍኖ የቆየውን የርስ በርስ ጦርነት ዳግም እየቆሰቆሰው ይገኛል። አማጽያኑ አሌፖን ተቆጣጥረው ሐማ ወደ ተባለች ከተማ ሲገሰግሱ ሶርያ እና ሩሲያ በአየር ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸሙ ነው። የአሳድ አጋር ሒዝቦላሕ አሁን ተዋጊዎች ወደ ሶርያ የመላክ ዕቅድ እንደሌለው አስታውቋል

በአሌፖ የተፈጸመ የአየር ጥቃት
በአሌፖ ዙሪያ በተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች 16 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለው ሌሎች 20 መቁሰላቸውን የሶርያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ መረጃ ይጠቁማል።ምስል፦ Rami Alsayed/NurPhoto/Imago

ተዳፍኖ የቆየው የሶርያ የርስ በርስ ጦርነት ዳግም እያገረሸ ይሆን?

This browser does not support the audio element.

የሶርያ ጦር እና የፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ መንግሥት አጋር የሆነችው ሩሲያ በኢስላማዊ ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር በሚገኙ አካባቢዎች ዛሬ ሰኞ ኃይለኛ የአየር ድብደባ ፈጽመዋል። የሁለቱ ሀገራት የጦር ኃይሎች በጥምረት የፈጸሙት የአየር ድብደባ በኢድሊብ ግዛት በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ ነው። የሶርያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ በጥቃቶቹ አምስት ሕጻናትን ጨምሮ 11 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

የሶርያ እና የሩሲያ የጦር ጀቶች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ድብደባ ማካሔድ የጀመሩት የሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ አሌፖ በአማጺያን ቁጥጥር ሥር ከወደቀች በኋላ ነው። በአሌፖ ዙሪያ በተፈጸሙ የአየር ድብደባዎች 16 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለው ሌሎች 20 መቁሰላቸውን የሶርያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ መረጃ ይጠቁማል።

የሶርያ ሲቪል መከላከያ በጎ ፈቃደኛ ኢስማይል አላብዱላሕ “ሰላማዊ ሰዎች ከ2011 ጀምሮ በእያንዳንዷ ሰከንድ፤ በእያንዳንዷ ደቂቃ ዋጋ እየከፈሉ ነው። አሁን አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል” ሲሉ ይናገራሉ። “ሰዎች ከቤታቸው እየሸሹ ነው። ሰዎች ጥቃት እየተፈጸመባቸው ይገኛል። የአሳድ መንግሥት በቀበራቸው ፈንጂ ቁሶች ሰዎች እየተገደሉ ነው” የሚሉት ኢስማይል “ሰቆቃው ዳግም ተመልሷል” ሲሉ አስረድተዋል።

በበሺር አል አሳድ መንግሥት ላይ አዲስ ጥቃት የጀመሩት ሐያት ታሕሪር አል-ሻም የተባለ ታጣቂ እና በሥሩ የተደራጁ አጋሮቹ ናቸው። ባለፈው ረቡዕ ጥቃት የጀመሩት አማጽያን ትላንት እሁድ በኩርድ ኃይሎች እጅ ከሚገኙ ሠፈሮች ውጪ አሌፖን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠሩ የሶርያ ሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ኃላፊ ራሚ አብደል ራሕማን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ከሚገኙ መካከል የአሌፖ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና እስር ቤቶች ጭምር ይገኙበታል። በማኅበራዊ ድረ ገጾች በተሠራጩ ምስሎች ታጣቂዎቹ በአሌፖ በሚገኝ የፕሬዝደንት በሺር አል አሳድ ቤተ መንግሥት ውስጥ ወዲህ ወዲያ ሲሉ ታይተዋል። 

ማሕደረ ዜና፣ መካከለኛዉ ምሥራቅ ደም ጠጥቶ ደም የሚጠማዉ ምድር

ሐያት ታሕሪር አል-ሻም በጎርጎሮሳዊው 2011 ጃብሓት አል-ኑስራ በሚል ስያሜ የተመሠረተ እና ከአልቃዒዳ ጋር ግንኙነት የነበረው ቡድን ነው።  ይሁንና በጎርጎሮሳዊው 2016 የቡድኑ መሪ አቡ ሞሐመድ አል-ጃውላኒ ከአልቃዒዳ ጋር የነበረው ትስስር መፍረሱን በይፋ አውጀው በአዲስ ስያሜ አቋቁመውታል።

የአሳድ ተቃዋሚዎች አብዛኛውን አሌፖ መቆጣጠራቸውን የሶርያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ አስታውቋል። ምስል፦ AAREF WATAD/AFP

በስኮትላንድ ሴይንት አንድሪው ዩኒቨርሲቲ የሶርያ ጥናት ማዕከል ተባባሪ መሥራች የሆኑት ኢብራሒም ሐሚዲ “ሒዝቦላሕ እና ኢራን በሊባኖስ እና በሶርያ ከገጠማቸው ትልቅ ሽንፈት በኋላ በምዕራባዊ አሌፖ ሰፍሮ ይገኝ የነበረው የኢራን ሚሊሺያ ተዳክሟል” ሲሉ ይናገራሉ።

“በቱርክ የሚደገፉ ኢስላማዊ ታጣቂዎች ይኸን ዕድል በመጠቀም የተወሰነ አካባቢ ተቆጣጥረዋል” የሚሉት ኢብራሒም ሐሚዲ “በዚህም ምክንያት በሶርያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ አሌፖ መቀመጫውን በደማስቆ ካደረገው መንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆናለች” ሲሉ አስረድተዋል።

ሶርያ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀችው በጎርጎሮሳዊው 2011 ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው። በጦርነቱ ግማሽ ሚሊዮን ሶርያውያን ቢገደሉም ዓለም ከቀውስ ወደ ቀውስ እየተሸጋገረ ዘነጋው እንጂ አልቆመም። የተባባሩት መንግሥታት የሶርያ ልዩ ልዑክ ጊዬር ፔደርሰን ”ባለፉት አራት ዓመታት ከስድት ወራት የሶርያ አውደ ግምባሮች በአንጻራዊነት የተረጋጉ” እንደነበሩ ይናገራሉ።

ማሕደረ ዜና፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ እልቂትና የአሜሪካኖች ተቃራኒ መርሕ

“ከሞላ ጎደል በየቀኑ ግጭቶች” ቢኖሩም ፔደርሰን እንደሚሉት እንደዚህ የከፋ አልነበረም። “በአሳሳቢ ኹኔታ ላይ እንገኛለን” የሚሉት ጊዬር ፔደርሰን “አማጺያኑ በጀመሩት ጥቃት የርስ በርስ ጦርነቱ እያገረሸ ነው” የሚል ሥጋት አላቸው። የጦርነቱ ማገርሸት በሰላማዊው ሕዝብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ያስጠነቀቁት ልዩ ልዑኩ “በሶርያ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች ለተጨማሪ መከራ እንዳይዳረጉ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግጋት ማክበር እንደሚገባ ሁሉንም ወገኖች ስማጸን ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።

የሶርያ ጦር ሐያት ታሕሪር አል-ሻም በተባለው ቡድን የሚመሩት ተቃዋሚዎች ወደ አሌፖ መግባታቸውን፣ በርካታ ወታደሮቹም መገደላቸውን አረጋግጧል። የጦሩ አዛዥ ጄኔራል አብደልከሪም ማሕሙድ ኢብራሒም ሐማ ከተባለች ከተማ አቅራቢያ የሰፈሩ ወታደሮችን ከጎበኙ በኋላ ኃይሎቻቸው ለ14 ዓመታት ሲመክቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በሶርያ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ትላንት እሁድ በተላለፈው ንግግራቸው ጄኔራል አብደልከሪም ወታደሮቻቸው በነፍስ እና በደማቸው ሶርያን ለማዳን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ይኸ መሬታችን እና ክብራችን ነው” ያሉት የጦር ጄኔራሉ “ማንኛውም ቅጥረኛ ወይም ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሶ ሊተኩስ የሚሞክር ወዲያውኑ እርምጃ ይወሰድበታል” ሲሉ ዝተዋል።

ኢራን ለሶርያ መንግሥት ድጋፏን ለመግለጽ የላከቻቸው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ ከፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ምስል፦ Sana via REUTERS

የሶርያ የርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የበሺር አል አሳድ መንግሥት በአማጽያኑ ከተነጠቀው የሀገሪቱ ግዛት ሁለት ሦስተኛውን መልሶ ከእጁ ማስገባት ችሎ ነበር። አል አሳድ በሩሲያ፣ ኢራን እና በሒዝቦላሕ ላይ ተመርኩዘው ከአባታቸው የወረሱትን መንበረ ሥልጣን እስካሁን ማስጠበቅ ችለዋል።

ፕሬዝደንቱ ዛሬ ሰኞ ባወጡት መግለጫ የግጭቱ መባባስ አሜሪካ እና ምዕራቡ ዓለም አላቸው ካሉት “ቀጠናውን በመከፋፈል እና በውስጡ የሚገኙ ሀገሮችን በመበታተን ካርታ አፍርሶ እንደገና የመሥራት ሰፊ ዕቅድ ጋር ይጣጣማል” ሲሉ ወንጅለዋል። 

ፕሬዝደንቱ ሶርያ “ሁሉንም ሽብርተኞች እና ደጋፊዎቻቸውን ማሸነፍ እንደምትችል” እምነታቸውን ባለፈው ቅዳሜ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር። አል አሳድ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬት አቻቸው ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ሶርያ አማጽያኑን ማሸነፍ ትችላለች ቢሉም የአጋር እና የወዳጅ ርዳታ እንደሚያስፈልጋት ግን ገልጸዋል።

ይሁንና ኢራን ከጋዛ እና ሊባኖስ ጦርነቶች በኋላ እንደ ቀድሞው አይደለችም። ሒዝቦላሕ በእስራኤል ኃይለኛ ጥቃት ተሽመድምዷል። ሩሲያ ግን የአማጽያኑን ግስጋሴ ለማቆም ከስምንት ዓመታት ገደማ በኋላ በሶርያ የአየር ድብደባ ጀምራለች። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት አሳድን ለመታደግ በፍጥነት የጦር ጀቶቹን ቢያዘምትም ዋንኛ ትኩረቱ ግን የዩክሬን ጦርነት መሆኑ አይጠረጠርም።

በስኮትላንድ ሴይንት አንድሪው ዩኒቨርሲቲ የሶርያ ጥናት ማዕከል ተባባሪ መሥራች የሆኑት ኢብራሒም ሐሚዲ “ሩሲያ ከጅማሮው በፍጥነት ጣልቃ ገብታ ቢሆን ኖሮ ታጣቂዎቹ ይኸን ሁሉ ቦታ መቆጣጠር ባልቻሉ ነበር” የሚል ዕምነት አላቸው።

ማሕደረ ዜና፣ የዩክሬን ጦርነት፣ የምዕራብ-ምሥራቆች ፍጥጫ አብነት

“የሩሲያ ጦር ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን ወደ ዩክሬን ስላዘዋወረ ወዲያውኑ ጣልቃ መግባት አልቻሉም” ያሉት የሶርያ ጉዳይ ተመራማሪው አማጽያኑ አሌፖን ከተቆጣጠሩ በኋላ የአየር ድብደባ ቢጀመርም “አምስት ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ባሏት ከተማ ላይ ኃይለኛ ጉዳት ሳያደርሱ ታጣቂዎቹን ገፍተው ማስወጣት ይችላሉ ብዬ አላስብም” ሲሉ ተናግረዋል።

የቀጠናው ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ ልዕለ ኃያላኑ እና አካባቢያዊ ሚሊሺያዎች ጭምር በሶርያ እያገረሸ ያለውን የርስ በርስ ጦርነት በእግር ጥፍራቸው ቆመው የሚከታተሉ ይመስላል። ባድር እና ኑጃባ የተባሉ ሁለት የኢራቅ ቡድኖች የበሽር አል አሳድን መንግሥት ለመደገፍ ቢያንስ 300 ተዋጊዎች ወደ ሶርያ መላካቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

የሶርያ አማጽያን በምሥራቃዊ አሌፖ የሚገኝ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ተቆጣጥረዋልምስል፦ AREF TAMMAWI/AFP

ሩሲያ የበሺር አል አሳድን መንግሥትን መርዳት እንደምትቀጥል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አረጋግጠዋል። የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መሪ ሼይክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናሕያን ጋር ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ መምከራቸው ተሰምቷል።

በወታደሮቿ እና በምትደግፋቸው ታጣቂዎች ሰፊ የሶርያ ግዛት ተቆጣጥራ የምትገኘው ቱርክ መቀመጫውን በደማስቆ ያደረገው የአል አሳድ መንግሥት ከተቃዋሚዎች እንዲታረቅ መክራለች። የቱርክ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ከኢራን አቻቸው ዛሬ ሰኞ ከተገናኙ በኋላ የሶርያ ቀውስ እንደገና ያገረሸው በውጪ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

 ኢራን ከዓመታት በፊት በፕሬዝደንት በሺር አል አሳድ መንግሥት ግብዣ ወደ ሶርያ የተላኩ ያለቻቸው ወታደራዊ አማካሪዎች በዚያው እንደሚቆዩ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች። አሌፖ በአማጽያኑ እጅ መውደቋ ከተሰማ በኋላ የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ ወደ ደማስቆ ተጉዘው የሀገራቸውን ድጋፍ ለማሳየት ከፕሬዝደንት አሳድ ጋር ተወያይተዋል።

ለሶርያ ስደተኞች መርጃ ዳጎስ ያለ ገንዘብ የተሰበሰበበት የለጋሾች ስብሰባ

አሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሺር አል አሳድ ራሳቸውን ከኢራን ካገለሉ እና ለሊባኖሱ ሒዝቦላሕ የጦር መሣሪያ የሚቀርብበትን መንገድ ከዘጉ በሶርያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ የማንሳትን ጉዳይ መነጋገራቸውን ሬውተርስ አምስት የመረጃ ምንጮች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ሮይተርስ ያነጋገራቸው የመረጃ ምንጮች አሜሪካ እና ሸሪኳ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አሳድን ከኢራን ለመለያየት አመቺ አጋጣሚ ተገኝቷል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሶርያ ልዩ ልዑክ ጊዬር ፔደርሰን ግን “ልዩነቶችን ለማቻቻል እና ለፖለቲካዊ መፍትሔ ቅድሚያ ለመስጠት ፈቃደኝነት የለም። በግጭቱ የሚሳተፉ በርካታ ተዋንያን ወታደራዊ ድል ይገኛል ብለው ያምናሉ” ሲሉ ተናግረዋል። “በሶርያ ለሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ ድል መጎናጸፍ አይችሉም” ያሉት ልዩ ልዑኩ “አሁን ማተኮር ያለብን ፖለቲካዊ የመውጫ መንገድ ማፈላለግ ላይ ነው” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ትላንት እሁድ በጋራ ባወጡት መግለጫ ተጨማሪ መፈናቀል እንዳይፈጠር እና የሰብአዊ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ሰላማዊ ሰዎች እና መሠረተ-ልማቶች እንዲጠበቁ ጥሪ አስተላልፈዋል። የውጊያው ማገርሸት የተባበሩት መንግሥታት በጎርጎሮሳዊው 2015 ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ለግጭቱ ሶርያ መር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ማረጋገጫ እንደሆነም አራቱ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (NATO) አባላት አሳስበዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW