1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአውሮጳ

ተግዳሮት የገጠመው የዩክሬን ሰላም አስከባሪ

ዓርብ፣ የካቲት 14 2017

በአንድ ወገን ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ለመቀነስ ወይም ጨርሳ ልታቆም እንደምትችል የምታስፈራራው፤ ዩናይትድ ስቴትስ ኪየቭ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ኔቶ አባል መሆን እንደማይፈቀድላት ይፋ አድርጋለች። በዚህም ምክንያት የአውሮጳ ሃገራት በጦርነት ለደቀቀችው ሀገር የጋራ የጸጥታ ኃይል ለማዋቀር እየተሯሯጡ ነው።

የአውሮጳ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፓሪስ
ዩክሬን ጉዳይ ላይ የመከረው የአውሮጳ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በፓሪስምስል፦ Christophe Petit-Tesson/dpa/EPA/AP/picture alliance

የዩክሬን ሰላም አስከባሪ

This browser does not support the audio element.

 

የአውሮጳ ሕብረት አባል ያልሆነችው ብሪታንያ ከትብብሩ ጋ በመሆን ዩክሬንን ከሩሲያ ለመከላከል ወታደሮቿን ለመላክ ፈቃደኝነቷን አሳውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ለዕለታዊ ዘ ቴሌግራፍ በጻፉት አስተያየት፤ የዩክሬንን ፀጥታ ለመከላከል ብሪታንያ ቀዳሚ ሚና እንደምትጫወት ገልጸዋል። 

የአውሮጳን ወታደሮች ወደ ዩክሬን የመላኩ ሃሳብ አመንጪ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ ናቸው። ማክሮን ባለፈው ዓመት ያቀረቡት ይህ ሃሳብ አሁን ፍሬ የሚያሳይበት ጊዜ የደረሰ ቢመስልም ተግባራዊነቱ ግን ግልፅ አይደለም።

እነማን ሰላም አስከባሪ ኃይል ሊልኩ ይችላሉ?

በርካታ የአውሮጳ መሪዎች የአውሮጳ ወታደሮችበዩክሬን መሬት የመገኘታቸው ነገር እውን መሆን የሚችለው በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ብቻ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል። ፈረንሳይ እና ብሪታንያ እንዲሁም ስዊድን ሃሳቡን ደግፈዋል። ሰላም ከሰፈነን ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን ለመላክ ፈቃደኛነታቸውንም አሳውቀዋል። 

ባለሙያዎች እንደሚሉት የአውሮጳ ሃገራት ወደ ዩክሬን ወታደሮች ለመላክ ከኔቶ ጥላ ውጪ የተለየ ትብብር ያዋቅሩ ይሆናል። እንዲያ ቢሆንም ግን ዋነኞቹ የአውሮጳ ሃገራት እርግጠኞች አይደሉም። የጀርመን መርኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ እሑድ ዕለት ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድመው በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

በተቃራኒው ተቀናቃኛቸው የወግ አጥባቂው ክርስቲያን ዴሞክራት እጩ ለሃሳቡ ግልፅ እንደሚሆኑ አመላክተዋል። ፖላንድ ሃሳቡን ብትደግፍም የራሷን ወታደሮች ወደ ዩክሬን ስለመላክ ግን ፈቃደኛ አይደለችም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ፤

«ወደ ዩክሬን ግዛት የፖላንድ ወታደሮችን የመላክ እቅድ የለንም። ሆኖም ግን በአቅርቦት እና በፖለቲካው በኩል ይህን ለማረጋገጥ ላሰቡ ሃገራት ድጋፍ እንሰጣለን፤ ለዩክሬንም እንዲሁ በአካል ድጋፋችንን እናረጋግጣለን። ለረዥም ዓመታት፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት ለአውሮጳ እና ፖላንድ መረጋጋት እና ደኅንነት፤ በዩክሬን ድንበር ፀጥታው ዘላቂነት እንዲኖረው የሁሉም አውሮጳ ሃገራት፤ የዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም የኔቶ መዋቅር ትብብርን  ፖላንድ በአስተማማኝነት መመልከቷ ጥርጥር የለውም።  »

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክምስል፦ Aleksander Kalka/NurPhoto/picture alliance

ስንት ወታደር ይፈለጋል

ምንም እንኳን የፖለቲካ ፈቃደኝነቱ ቢኖርም ዋናው ጥያቄ የሚሆነው፤ ተባባሪዎቹ የዩክሬንን ድንበሮች ለመከላከል ስንት ወታደሮች የመላክ አቅም አላቸው የሚለው ነው። የቀድሞው የኔቶ ዋና ጸሐፊ አንደርስ ፎግ ራስሙሰን፤ እንደሚሉት ለዚህ ተልዕኮ ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ወታደሮች ያስፈልጋሉ። ሆኖም ግን እስካሁን ወታደሮች ለመላክ ፈቃደኛነታቸውን ከገለጹ ሃገራት አንዳቸውም ስንት ወታደር እንደሚያዋጡ አላሳወቁም። እንዲያም ሆኖ እንዲህ በርካታ ቁጥር ያለው የወታደር ኃይል ወደ ግጭት አካባቢ መላክ የፖለቲካ ውዝግብ እንደሚያስከትል አያነጋግርም። 

ጦርነት ውስጥ ባሉት ሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረሰ ምንም ዓይነት ስምምነት በሌለበት የአውሮጳ ሃገራት ወታደሮችን በሰላም አስከባሪነት የማሰማራቱን ሃሳብ ከወዲሁ ሩሲያ ተቃውማለች። የሚሰማራው ኃይል የኔቶ ወታደር ነው የሚል ግምቷንም ይፋ አድርጋለች። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን አማካሪ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤

«አሁን አውሮጳውያን ስለሰላም አስከባሪ ወታደሮች ብዙ እያወሩ ነው። ፈረንሳይ እና ብሪታንያ። ይህ በእውነትም እየሆነ ነው። ሆኖም ግን ሁለታችንም ሰላም አስከባሪ ወታደሮች የሚሰማሩበትን ደንብ እናውቃለን። እስካሁን በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ ውይይቶች አልተደረጉም። ስለዚህ መናገር አስቸጋሪ ነው። እነዚህ የኔቶ አባል ሃገራት ናቸው፤ እናም የኔቶ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ግዛት ይሰማራሉ። ስለዚህ ይህ እጅግ አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፤ እስካሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ተጨባጭ ንግግር የለም።»

ተንታኞች እንዳሉት በቴክኒክ ደረጃ አውሮጳውያን ሰላም አስከባሪዎች ወታደሮችን ለማሰማራት የተመድን ማረጋገጫ ያስፈልጋቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሩሲያ እና ቻይና በሚገኙበት የጸጥታው ምክር ቤትን ይለፍ ያገኛል ተብሎ ግን አይታሰብም። በፅንሱ የጨነገፈ እንደማለት ነው።

ቮራ አንቾል/ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW