ተፈናቃይ ገበሬዎች እርሻ ጀመሩ
ሐሙስ፣ ሰኔ 22 2015
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጠለያ ጣቢያ የቆዩና ወደ ቀያቸው የተመለሱ ዜጎች በግብርና ስራ መሰማራታቸውን አስታወቁ፡፡ ወደ ቤታቸው ተመልሰው በእርሻ ስራ የተሰማሩ ነዋሪዎች የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም የታረሰውን መሬት በዘር ለመሸፈን የአፈር ማዳበሪያ ችግር እንዳገጠማቸው እየገለጹ ነው፡፡ የክልሉ የግብርና ቢሮ በበኩሉ ዘንድሮው የምርት ዘመን በተሻለ መልኩ አርሶ አደሩ በክልሉ ስር በሚገኙ 3ቱም ዞኖች ወደ መግባቱን ገልጾ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ምርት ዘመን 29 ሚሊዩን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ባበክር ሀሊፋ ጠቁመዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2013 ዓ.ም 475ሺ ህዝብ ተፈናቅሎ የቆየበት ሲሆን ከግንቦት 2014 ዓ.ም አንስቶ ወደየ ቀድሞ ቀያአቸው መመለሳቸውን የክልሉ መንግስት ከዚህ ቀድም ይፋ አድርጓል፡፡
በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም በካማሺ ዞን በታጣቂዎች እና መንግስት መካከል የዕርቅና የሠላም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ተፈናቅሎ በየመጠለያ ጣቢያው የነበሩ ሰዎች ወደየ ቀድሞ ቤታቸው መመለሳቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በካማሺ ዞን አጋሎ እና ያሶ ከተባሉ ቦታዎች ተፈናቅለው ለአንድ ዓመት ያህል በዞኑ ዋና ከተማ እንደ ቆዩ የነገሩን አቶ ወርቁ ጉዴታ እና አቶ ታጁ ከበደ ባሁኑ ወቅት ወደየ ቀያአቸው ተመልሰው መደበኛ ስራቸውን ጀምረዋል፡፡ በግብርና ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኙ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም በርካታ ሄክታር መሬት መታረሱን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በየወረዳቸው በግብርና ስራ ለተሰማሩ ሰዎች አስፈላጊውን የምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አለመደረጉን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በበቂ ሁኔታ ባለመታረሱ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚሹም አክለዋል፡፡
አቶ በለጠ የተባሉ የመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ነዋሪም በተመሳሳይ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምርት ዘር አቅርቦት የለም ብሏል፡፡ የአፈር ማዳበርያ ዋጋ በእጅጉ መጨመሩንና በኩንታል እስከ 10ሺ ብር እየተገዛ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ በአካባቢአቸው ይስተዋል የነበረው የጸጥታ ችግርም መሻሻሉንና በወረዳቸው አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፍ በሰጡን ማብራሪያ በክልል ደረጃ የማዳበሪያ እጥረት እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡ ለክልሉ የቀረበው የአፈር ማዳበሪያ መጠን በ44 በመቶ ቀንሶ የመጣ በመሆኑ ሊዳረስ አልቻለም ብሏል፡፡ አርሶ አደሩ እንደ ኮምፖስት ያሉ አማራጭ ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ተቋማቸው ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸው በክልሉ እስካሁን በአሶሳ፣መተከል እና ካማሺ 5 መቶ ሺ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም ምርት ዘመን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 1.1 ሚሊዩን ሄክታር መሬት በምርት ለመሸፈን ታቅዶ የነበረ ሲሆን 843ሺ ያህሉ ሄክታር መሬት በምርት መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አመልክተዋል፡፡ በዘንድሮ የምርት ዘመን ደግሞ 937ሺ ሄክታር በምርት ይሸፈናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ