1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮች ከጃራ መጠለያ በሦስት ቀናት ልቀቁ መባላቸው ያስከተለው ተቃውሞና ስጋት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2016

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በሦስት ቀናት ውስጥ ከአካባቢው ልቀቁ መባላቸውን ተቃወሙ። ውሳኔው በተፈናቃዮች ዘንድ መረበሽን እንደፈጠረም ተናግረዋል። አካባቢው ባልተረጋጋበት ሁኔታ ቀድሞ ወደ ነበሩበት የወለጋ ዞኖች እንሄዳለን የሚል ስጋትም አድሮባቸዋል።

በአማራ ክልል ጋራ የተፈናቃዮች መጠለያ
 ፎቶ ከማኅደር
በአማራ ክልል ጋራ የተፈናቃዮች መጠለያ ፎቶ ከማኅደርምስል Alamata City Youth League

የተፈናቃዮች ስጋት

This browser does not support the audio element.

 

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በሦስት ቀናት ውስጥ ከአካባቢው ልቀቁ መባላቸውን ተቃወሙ። ውሳኔው በተፈናቃዮች ዘንድ መረበሽን እንደፈጠረም ተናግረዋል። አካባቢው ባልተረጋጋበት ሁኔታ ቀድሞ ወደ ነበሩበት የወለጋ ዞኖች እንሄዳለን የሚል ስጋትም አድሮባቸዋል። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ በበኩሉ በአካባቢው ባለው የሰላም እጦት ምክንያት ግብዓት ወደ ቦታው ማድረስ ባለመቻሌ ውሳኔው ትክክል ነው ብሏል። በሂደትም ተፈናቃዮች ወደመጡበት የኦሮሚያ ክልል እንደሚሸኙ ገልጧል።

በ2010 ዓም የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በአንዳንድ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ይኖሩ በነበሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ተካሂደዋል። ብዙዎቹ ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች በርካቶች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ተወልደው ያደጉባቸውን አካባቢዎች እየለቀቁ ወደ አማራ ክልል ተሰደው ገብተዋል።

ወደ አማራ ክልል ከደረሱት መካከል አብዛኛዎቹ በሰሜን ወሎ ዞን ጃራበተባለ የመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ። አንዳንድ ተፈናቃች ለዶይቼ ቬሌ ሰሞኑን በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ ደብረ ብርሃን እንደሚዛወሩ እንደተነገራቸውና በሂደትም ወደ ኦሮሚያ ክልል እንደሚሸኑ መስማታቸውን አመልክተዋል። ሁኔታው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ከተናቃዮቹ አንዱ 10,400 እንደሆኑ እና የተባለው ትዕዛዝ ስጋት ማስከተሉን ዘርዝረዋል።

ሌላዋ ተፈናቃይ በበኩላቸው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ወለጋ መሄድ ከባድ እንደሆነ ገልጠው፣ ውሳኔውም ከፍተኛ ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ነው ያመለከቱት። ወደ ደብረ ብርሃንም ሆነ ወደ ኦሮሚያ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑት ተፈናቃይ መስተካከልና መረጋገጥ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ ይላሉ። 

በአማራ ክልል በሀብሩ ወረዳ ድሬ ሮቃ ቀበሌ በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ 10 ሺህ የሚሆኑ ወገኖች ይገኛሉ። ፎቶ፤ ከማኅደርምስል Alemenw Mekonnen/DW

«እዛ ያለው ሰላም ምን ያህል ነው? የኦሮሚያ ባለሥልጣናት መጥተው ያለውን ሰላም ለእኛ መግለፅ ይኖርባቸዋል፣ ከተፈናቃዩ ኮሚቴ ተዋቅሮ ኦሮሚያ ያለውን ምቹ ሁኔታ ይመልከትና ይምጣ፣ ይህ ሁሉ ካልተደረገልን አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ወለጋ ከምንመለስ በጅቡቲ በኩል ከአገር ወጥተን ስደተኛ እንሆናለን።» ነው ያሉት።  

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር ግብዓት ወደ አካባቢው ማድረስ አስቸጋሪ በመሆኑ ተፈናቃዮችን ወደ ደብረ ብርሃን ማዛወር አስፈልጓል ብለዋል። «ከዚያም ከታጣቂዎች ነፃ ወደ ሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ይላካሉ» ነው ያሉት፡፡ የአማራክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ «ተፈናቃዮች ቀስ በቀስ ወደ መጡበት ይመለሳሉ፣ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ደግሞ የአማራና የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ተስማምተዋል» ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ቀደሞ በኦሮሚያ በነበረው ግጭት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ተፈናቃዮች ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ወደ አማራ ክልል ገብተው እንደነበር መጥቀሱ ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW