ቱአሬጎች ከሊቢያው ጦርነት በኋላ
ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2004
የቱአሬግ አርብቶ አደሮች ‘አዛዋድ’ብለው በሚጠሩት የሰሜን ማሊው በረሃ በመንግሥት ወታደሮችና በቱአሪግ አማጽያን መካከል ከጥር መጀመሪያ አንስቶ የተኩስ ልውውጥ እና የአየር ድብደባም እየተካሄደ ነው ። ሰለ ውጊያው የሚወጡ ዘገባዎች ግን በርሰ በርስ የሚጋጩ ናቸው ። ስለ ሞቱና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር አስተማማኝ መረጃ የለም ። ይሁንና ከ120,000በላይ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተሰደው ወደ ተባበሩት መንግሥታት መጠለያዎች ሸሽተዋል ። ጉዳዩን በቀርብ የሚያውቁ ተንታኞች እንደሚሉት ውጊያው የሊቢያው ጦርነት መዘዝ ነው ። የዶቼቬለዋ Julia Hahn የዘገበችውን ሂሩት መለሠ አጠናቅራዋለች ።
እጅግ የደየኽየውና አስቸጋሪው ሰሜን ማሊ የሚገኘው በረሃ የቆዳ ስፋቱ ከፈረንሳይ ጋር ይስተካከላል ። በዚህ አካባቢ ከሳምንታት አንስቶ የማሊ ጦርና የአዛዋድ በሔራዊ የነፃነት ንቅናቄ በእንግሊዘኛው ምህፃር MNLA በመባል የሚጠራው አዲሱ የአማፅያን ቡድን እየተዋጉ ነው ። በ ጀርመኑ የ Bayreuth ዩኒቨርስቲ የማሊ ጉዳዮች አጥኚ Georg Klute እንደሚሉት የአሁኑ ውጊያ የሊቢያው ጦርነት መዘዝ ነው ።
« ከባዱ ውጊያ ፣የሊቢያው ጦርነትና የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO የሊቢያ ዘመቻ ወጤት ነው ። ምክንያቱም በሊቢያ አገዛዝ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ በርካታ ወታደሮች ወደ ደቡብ ተሰደዋልና ። »
በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሠረት ቁጥራቸው እስከ 4000 የሚደርስ የቱአሬግ ቅጥርኛ ተዋጊዎች ከሊቢያ በተለይም ወደ ኒዠር ና ማሊ ገብተዋል ። አበዛኛዎቹ በሊቢያው ህዝባዊ አብዮት ወቀት ለጋዳፊ ጦር ተሰልፈው ተዋግተዋል ። ቅጥረኞቹ የማሊን ድንበር አቋርጠው ጥር መጀመሪያ ላይ ሮኬቶች ና ሌሎች በቀላሉ የሚንቀሳቀሱ የጦር መሣሪያዎችን በሻንጣቸው ሸክፈው ነው ማሊ የገቡት ።
« እነዚህ የጦር መሣሪያዎች የጋዳፊ ጦር መሆናቸው ፍፁም ግልፅ ነው ። የጦር መሣሪያዎቹ የማሊ ጦር ከታጠቃቸው መሣሪያዎች እጅግ በጣም የተሻሉ ናቸው ። በአማፅያን ዘንድ ያለው አዲሱ ነገር ይሄ ነው ። »
ይላሉ በፍራንክፈርት ዩኒቨርስቲ የሰነ ሰበ ምሁር የማሊው ተወላጅ ማማዱ ዲያዋራ ።
MNLA ራሱን ፣ የአብዮታዊ ንቅናቄ ቡድን ፣ የቱአሬጎች ድምፅ አድርጎ የሚቆጥረው ። ከዚህ በተጨማሪም አረቦችን ማውሮችንና ፉላኒዎችንም ደጋፊዎቼ ናቸው ነው የሚለው ። ግቡ አዝዋድ የምትባል ነፃ ሃገር መመሥረት ነው ።ሙሳ አግ አሳሪ የአማፅያኑ ቃል አቀባይ ናቸው ። ከመንግሥት ጋር የሚካሄደው ድርድር ያልሰመረበትን ምክንያት ያስረዳሉ
« በሰላማዊ ፣ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ሞክረናል ። ሆኖም መፈናፈን የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ። አዎ መደራደር እንፈልጋለን ። ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ መንግሥት መልስ የሚሰጠን በጦር እርምጃ ነው ። »
የቱአሬጎች ትግል እድሜ ማሊ ነፃነትዋን ካወጀችበት ጊዜ ጋር ይስተካከላል ። በማሊና በሌሎቹም የሳህል ሃገራት አናሳ የሆኑት አርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍሎች በመንግሥት ውስጥ ውክልና የለንም የሚል ስሜት ነው ያላቸው ። እጎአ ከ 1960 አንስቶ በተለይም ማሊና ቻድ የሚገኙት አርብቶ አደሮች በየጊዜው እንዳመፁ ነው ። እጎአ ከ 2005 እስከ 2009 ዓም የተካሄደው የቅርብ ጊዜው አመፅ ነው ። እነዚህን ግጭቶች ለማስቆም የተካሄዱት ድርድሮች ከሽፈዋል ። ለማሊው ፐሬዝዳንት የሃገሪቱ መከፈል ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም ። በሚያዚያ አጋማሽ አካባቢ ምርጫ ይካሄዳል ። እስከዚያ ድረስ የማሊ ጦር አማፅያኑን ድል ማድረግ ነወ ፍላጎቱ ። የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሜሊያ ቦቤዬ ማይጋ ፣ መንግሥት የደኽየውን ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ኤኮኖሚ ለማልማት ፣ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሱን አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ ። ያም ሆኖ ግን ስህተት መኖሩንም ያምናሉ ።
« እርግጥ ነው መንግሥት እዚያ በቅርበት የለም ።ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ዘልቋል ። መንግሥት ይህን ግዛት መቆጣጠር እንዳይችል የሚንቀሳቀሱ በርካታ ቡድኖች አሉ ። »
መነገሥት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ባለመቆጣጠሩ ምክንያት ተጠቃሚ የሆነው MNLA ብቻ አይደለም ። አስቸጋሪው ሰሜን ማሊ ከረዠም ጊዜ አንስቶ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ፣ የአክራሪ ሳላፊስቶችና በመግሬብ የአልቃይዳ አባላት መነኻሪያ ሆኗል ። በመግሬብ የአልቃይዳ ቡድን ባለፉት ጊዜያት አገር ጎብኝዎችን በማገት ይታውቃል ። የቱኣሬግ አማፅያን ከዚህ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ይጠረጠራል ። ይሁንና ደያዋራ እንደሚሉት ለዚህ ማረጋገጫ የለም ።
ሂሩት መለሠ
ተክሌ የኋላ