1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

ቲክቶክን አብዝቶ መጠቀም የማስታወስ ችሎታ እንደሚቀንስ ያውቃሉ?

ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017

በአሁኑ ጊዜ እንደ ቲክ ቶክ ያሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሰዎችን ሀሳብ በመበታተን ይጠቀሳሉ።በዚህ የተነሳ በርካታ ሰዎች ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ በአንድ ነገር ላይ ማተኮር እየተቸገሩ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።ይህ እንዴት ይከሰታል? እንደ ቲክ ቶክ ያሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በአእምሯችን ላይ ምን ተፅዕኖስ ያሳድራሉ?

Symbolbild | Die Plattform Tiktok bietet ein hohes Suchtpotenzial
ምስል፦ Tim Wegner/epd-bild/picture alliance

ቲክቶክን አብዝቶ መጠቀም የማስታወስ ችሎታን እንደሚቀንስ ያውቃሉ?

This browser does not support the audio element.

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በአሁኑ ወቅት መረጃ ለማግኘት፣ መስተጋብር ለመፍጠር  እና የፈጠራ ሀሳብን ለመግለጽ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን  እነዚህ ዲጅታል መድረኮች ሰዎች በአንድ ነገር ላይ ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ ማተኮር እንዲቸገሩ  ማድረጋቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። ምክንያቱም እነዚህ መድረኮች ትኩረት የሚከፋፍሉ ናቸው።በተለይም እንደ ቲክ ቶክ  ያሉ ዲጅታል መድረኮች የማስታወስ ችሎታን እና በአንድ ነገር ላይ የማተኮር ችሎታችን እንዲቀንስ እያደረጉ ነው።የኒዎሮ ሳይንስ ባለሙያዎች ለዚህ አዲስ ችግር የቲክ ቶክ አእምሮ ወይም «TikTok brains» የሚባል አዲስ ቃል ይዘው መጥተዋል።

በሰዎች አእምሮ ላይ ተመራማሪ የሆኑት ሄኒንግ ቤክ  ብዙም ባይሆን የሰዎች አእምሮ ሁልጊዜ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ይፈልጋል ይላሉ።«አንጎል ሁል ጊዜ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ይፈልጋል። ምክንያቱም  በጣም አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ። አደጋ ሊመጣ ወይም አዲስ ነገር ሊመጣ ይችላል። ምናልባት ሊያመልጥዎ የሚችል አስፈላጊ ኢሜይል ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ የመሻሻል እድልን ያመጣሉ።»ብለዋል።

ምንም እንኳ ይህ ግፊት  የአእምሮ ተፈጥሯዊ ተግባር ቢሆንም ፤ በዚህ ወቅት ግን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ  ያለማቋረጥ ትኩረትን እየከፋፈሉ ነው። ይህም ለትኩረት መቀነስ አስተዋፅኦ እንዳለው ባለሙያው ይገልፃሉ።«እነዚያን መተግበሪያዎች በተጠቀምንበት እና እነዚያን ቪዲዮዎች በተመለከትንበት ቅጽበት ወደ  ትኩረት መቀነስ  ይመራናል። ከዚያ የተመለከትነውን በትክክል  ሳናደንቅ እና ሳናጣጥም ወዲያውኑ ወደ ሌላ እንቀጥላለን ። ነገር ግን ረዥም ፊልም ስንመለከት መጨረሻ ላይ  በጣም ጥሩ ነበር በማለት እናደንቃለን።»

«የቲክ ቶክ አእምሮ»ምንድን ነው?

ብሬን ታፕ/ BrainTap/ የተባለው የአእምሮ ደህንነት መተግበሪያ መስራች ዶክተር ፓትሪክ ፖርተር  እንደሚሉት ፤የቲክ ቶክ አእምሮ፤  ዲጅታል መድረክን በብዛት በሚጠቀሙ  ግለሰቦች ላይ የሚታየውን የግንዛቤ እና የነርቭ ለውጦችን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ይህም በተለይ ትኩረትን በመቀነስ ይገለጻል። ይህ ክስተት ነገሮችን የማድነቅ እና የማጣጣም ፍላጎት ማነስ  እና ረዘም ላሉ እና ውስብስብ ለሆኑ ስራዎች ትዕግስት መቀነስን ያካትታል።

በአንጎላችን ውስጥ ምንድነው የሚከናወነው?

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በጀሮአችን የሰምንሰማው መረጃ  ሁል ጊዜ ወደ  አውዲታሪ ኮርቴክስ/auditory cortex/ ወደ ሚባለው የአንጎላችን ክፍል ፤ የምናያቸው መረጃዎች ደግሞ ቪዥዋል ኮርቴክስ/ visual cortex/ወደ ሚባለው የአንጎላችን ክፍል ይሄዳል።በዚህ ወቅት ታዲያ አንጎላችን የሰማነው እና ያየነው ነገር አዝናኝ በሆነ ቁጥር «ዶፓሚን» የተባለውን የደስታ ንጥረ ቅመም ያመነጫል። እያንዳንዱንየቲክ ቶክ አዝናኝ ይዘት በምናይበት እና በምንሰማበት ጊዜም ይሄው «ዶፓሚን» የተባለ ንጥረ ቅመም ከአንጎላችን ይለቀቃል። አንጎላችን ይህንን የደስታ ስሜት በተደጋጋሚ ለማግኘትም ተጨማሪ የቲክ ቶክ ይዘት እንድንመለከት ያስገድደናል።ይላሉ ሄኒንግ ቤክ። በመሆኑ፤ በርካታ ሰዎች ጊዚያቸውን ስልካቸው ላይ እንዲጠፉ ይገደዳሉ።

«ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህን ቪዲዮዎች እየተመለከቱ እና እያስተናገዱ ያሉት የአንጎል ክፍሎች በዚያ ወቅት ምንም ማወቅ ስለማይችሉ ነው። በሌላ አገላለጽ፣ እየተመለከትነው እንዳለን አናውቅም።ስለዚህ በዚያ ላይ ቁጥጥር እናጣለን።» ብለዋል።

የቲክቶክ አጠቃቀም ከማስታወስ ችግር፣ከትግስት ማጣት ከድብርት፣ እና ጭንቀት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጥናት አመልክቷል።ምስል፦ Dado Ruvic/REUTERS

እነዚህ የአንጎል ሂደቶች የሚጎዱን ወይንም የሚረዱን እንዴት ነው?

ባለሙያዎች «የቲክቶክ አንጎል»  የእንቅልፍ መዛባት እና የእንቅልፍ ጥራት መጓደል እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።

በአጠቃላይ ቲክቶክ  ከፈጣን መረጃ ሂደት እና ከዘርፈ ብዙ ስራዎች  ጋር የተያያዙ የነርቭ ስርዓትን በማጠናክር ፤በፍጥነት የማሰብ ሂደትን የተሻለ ሊያደርግ ይችላል። በተቃራኒው ግን አእምሮአችን ለነገሮች ጥልቅ  እና ቀጣይነት ያለው ትኩረት የመስጠት አቅሙ እየቀነሰ ይሄዳል። በዚህም ጊዜ ተወስዶ  ለሚሰሩ የግንዛቤ ስራዎች ኃላፊነት ያላቸው የነርቭ ህዋሳት ይዳከማሉ።በዚህም ሰዎች ትኩረት  እና ትግስት አልባ እንዲሁም የማስታወስ ችሎታቸው ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል።«አንድ መተግበሪያ  ጠቅ ማድረግ ብቻ ነው ያለብኝ። ከዚያ በኋላ አእምሮዬ ሌላ ነገር ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ሁልጊዜ ሶስት ነገሮችን ለማድረግ ከተገደድኩ.፤በአዕምሮዬ ውስጥ የሶስቱ ነገሮች ንድፍ ይሳላል። እና ያለምንም ማሰላሰል ወዲያው ያንን መተግበሪያ  እጠቀማለሁ።» በማለት ሄኑንግ ቤክ ገልፀዋል።

ልጆች ለቲክ ቶክ ተፅእኖ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው

በእድገት ደረጃ ላይ ያሉት የታዳጊ ወጣቶች  አእምሮዎች ደግሞ ለዚህ የቲኪቶክ ተጽእኖ የበለጠ ተጋላጭ ይሆናል።ምክንያቱም የአዋቂዎች አእምሮ ሙሉ በሙሉ የተገነባ እና የበሰለ የእድገት ደረጃ ላይ ያለ ሲሆን፤ የአዳጊ ወጣቶች አእምሮ ደግሞ እድገቱን ያልጨረሰ እና ገና በመሰራት ላይ ያለ በመሆኑ ይህ ችግር እድገቱን ሊገታ ይችላል።ተመራማሪው ሄኒንግ ቤክ ለልጆች  ከዚህ የበለጠ ጉዳት የለም ይላሉ።«የልጅን አእምሮ በአንድ ብርጭቆ ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ ከማድረግ የበለጠ የከፋ ነገር የለም። ዲጅታል መሣሪያዎች ልጆች በራሳቸው እንዳያስቡ ያደርጓቸዋል።የሚያስቡት ከቪዲዮው ወይም ከሚከሰቱት ነገሮች ጋር ስለሚስማማ ፍጥነት ነው። ነገር ግን ለአንድ ልጅ በራሱ የተለየ ፍጥነት መጫወት እና ምን እንደተከሰተ ማሰብ  ወሳኝ ነው» ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ልጆች እና ወጣቶች በየቀኑ በማህበራዊ አውታረ መረቦች ላይ ሰዓታትን ያሳልፋሉ።በዩኤስ አሜሪካ በታዳጊዎች ላይ የተደረገው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው 80 በመቶዎቹ ከጓደኞቻቸው ጋር የመቀራረብ ስሜት የሚፈጥሩት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  በኩል ነው።ያም ሆኖ በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ የቲክቶክ አጠቃቀም  ከማስታወስ ችግር፣ከትግስት ማጣት ከድብርት፣ እና ጭንቀት ጋር የተቆራኘ መሆኑንም አሳይቷል።

የአዳጊ ወጣቶች አእምሮ እድገቱን ያልጨረሰ እና ገና በመሰራት ላይ ያለ በመሆኑ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን አብዝቶ መጠቀም የአእምሮ እድገትን ሊገታ ይችላል።ምስል፦ picture alliance / PHOTOPQR/VOIX DU NORD/MAXPPP

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም እና በሰዎች ባህሪ መካከል ያለውን ግንኙነት አጥኚ የሆኑት ዶክተር ጀስቲን ማርቲን በበኩላቸው ከፍተኛ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም በአእምሮ ጤና ላይ ተፅዕኖ አለው።«እጅግ በጣም ከባድ ሆኖ ነው ያገኘነው።የማህበራዊ መገናኛኛ   ዘዴዎች  አጠቃቀምከድባቴ እና ከጭንቀት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ደርሰንበታል። ነገር ግን የሚወዱት መተግበሪያ በቀን ለስድስት ሰአት ወይም ከዚያ በላይ በሚጠቀሙ ልጆች ብቻ ነው።» ብለዋል።

ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  የአመጋገብ ችግርን በተመለከተ አሉታዊ ተጽእኖ አላቸው። ወጣቶች  ጤናማ ያልሆኑ የውበት ፉክክርን  እንዲከተሉ ግፊትንም ይጨምራሉ.። በመተግበሪያዎች ላይ የሚለጥፏቸው ነገሮች ሁልጊዜ ሌሎች አስተያየት እንዲሰጡ ይጋብዛሉ። ነገር ግን የሚያገኙት ምላሽ ሁል ጌዜ አወንታዊ ላይሆን ይችላል።  ይህም ጀስቲን ማርቲን እና ቡድናቸው በልጆች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በጥናታቸው ተገንዝበዋል።«ብዙውን ጊዜ በበይነመረብ ላይ ይዘቶችን  የሚለጥፉ ልጆች የመንፈስ ጭንቀት፣ የመረበሽ ስሜት፣ መናደድ እና ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው»በማለት ገልፀዋል።እነዚህ ስሜቶች ደግሞ ለሚሰጧቸው አሉታዊ አስተያየቶች ወይም ችላ ለመባላቸው ምላሽ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።

ለልጆች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀምን መገደብ

ለዚህም፤ የልጆችን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም  መገደብ እና መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል። በተለይ  በአስራዎቹ እድሜ ለሚገኙ አዳጊዎች እነዚህን ዲጅታል መድረኮች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ትምህርት ቤቶች ሃላፊነት እንዳለባቸው ተመራማሪው ያስረዳሉ።

 «አስገራሚ  ሆኖ ያገኘሁት አንዳንድ ሀገሮች የግል ስልኮች በትምህርት ቤቶች መታገዳቸው ነው።በእርግጥ ቀድሞውኑ እዚያ እንዲፈቀድ የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? ምንስ  እሴት ይጨምራል? አንድም ምክንያት አላውቅም።እንዲያውም በተቃራኒው ነው። 20  ዓመት አእምሮ ቢያንስ  የሚበስልበት ጊዜ ነው እንበል ።ቢያንስ ነገሮችን ውድቅ ለማድረግ ወይም ለማቀድ እና ነገሮችን ለማመዛዘን። ያ ማለት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ወይም ልጆች እነዚህን መተግበሪያዎች በአግባቡ መጠቀም አይችሉም ማለት ነው።» በማለት ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር ቲክቶክ የንቃተ ህሊና ተፈጥሮን እንደሚቀይር ይገልፃሉ። የአሁኑ ትውልድ ከቀደምት ትውልዶች በተለየ ሁኔታ ልዩ መረጃዎችን በማህደረ ትውስታ ውስጥ ከማከማቸት ይልቅ አንጎላቸውን እንደ መፈለጊያ ሞተር እየያዙ ነው ይላሉ።ይህ ለውጥ የመጣውም መረጃ በቀላሉ የሚገኝ እና በድር ላይ የሚከማች መሆኑን በማወቅ ነው።በዚህም የተነሳ አእምሮአቸው ከመረጃው  ዝርዝር ይልቅ መረጃን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ማለትም የት ወይም እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በማስታወስ ላይ የተካነ እየሆነ መምጣቱን ባለሙያው አመልክተዋል።

ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወጣቶች ጤናማ ያልሆኑ የውበት ፉክክርን እንዲከተሉ ግፊትንም ይጨምራሉ.። ምስል፦ Tim Wegner/epd-bild/picture alliance

ሚራ ቫተርኮተ ይዘቶችን በመፍጠር እና በማሳተም ለአምስት ዓመታት ያህል በተለያዩ ዲጅታል መድረኮች የሰራች የገመድ ዝላይ ባለሙያ ነች። ችግሩን  ለመፍታት ለተጠቃሚዎች አዳዲስ ዘዴዎችን ታካፍላለች።«በእርግጥ ሰዎችን ለማነቃቃት እና ለማነሳሳት ለሁሉም ሰው አዘጋጅቻለሁ። ነገር ግን በዋናነት አዳዲስ ዘዴዎችን ለማካፈል ነው። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ምድነው ከባዱ ነገር የሚለውን ለማየትም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ብዙ ጊዜ አሳልፋለሁ። በአሁኑ ጊዜ ስልተ ቀመር እና ዲጅታል መድረኮች በፍጥነት እየተቀየሩ ነው። እና ሰዎች የበለጠ ፈጣን እና ፈጣን መሆን ይፈልጋሉ። በእርግጥ ፈታኝ ነው፣ ግን ደግሞ አስደሳች ነው። » በማለት ገልፃለች።

ሚራ ፤ለማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች የመጀመሪያዎቹ ሶስት ሰከንዶች የሚፈልጉትን ለመወሰን አስፈላጊ ናቸው ትላለች።የዲጅታል መድረኮች  አጠቃቀሟን ለመገደብም የራሷ  ስልት አላት።«ሁልጊዜ የራሰህን መርህ መጠበቅህን ማረጋገጥ።ለጥናትም ይሁን የእረፍት ጊዜህን ለማሳለፍ በዚህ ጊዜ ለምን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ እንዳለህ ማወቅ ያስፈልጋል። ያ በጣም አስፈላጊው ነገር  ነው። »ብላለች።

ከችግሩ የመውጫ  መንገዶች

ስለሆነም ባለሙያዎች ዲጅታን መሳሪያዎችን  እንደ ስፖርት ወይም ሌላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባሉ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች መተካትን ይመክራሉ።ከሰዎች ጋር መነጋገር እና ያለ ስልክ ሌሎች የመዝናኛ ቦታዎችን ማዘውተር  በዚህ ወቅት ስልክን ቤት መተው እና ራስን ለዚያ መርህ ማስገዛት ያለ ቲክ ቶክ «ዶፓሚን»ን ለማግኘት መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመኝታ ክፍል ውስጥ ስልክ አለማስቀመጥ፣ ዲጅታል መድረኮችን የምንጠቀምበትን ጊዜ ለመገደብ የማንቂያ  ምልክትን ማድረግ፣ እና ቢያንስ ለ15 ደቂቃ ጥዋት እና ማታ መጽሐፍ ማንበብም ይመከራል። እንደባለሙያዎቹ፤አዳዲስ ልምዶችን ለመገንባት ከስምንት እስከ 12 ሳምንታት ይወስዳል።ለዚህም መርህን አጥብቆ መያዝ የበለጠ ይረዳል።

ፀሀይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW