1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቲክ ቶክን ለበጎ ተግባር ያዋለች ወጣት

ዓርብ፣ ጥር 14 2013

ወጣቷ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴን በተለይም ቲክ ቶክን በመጠቀም በቅርቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ በመሰብሰብ በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ሕዛናት መርጃ ማዕከል ውስጥ በገንዘብ እጥረት የተነሳ የልብ ቀዶ ጥገና ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ህፃናት እንዲደርስ አድርጋለች።

Hiwot Tadesse - junge äthiopische Schauspielerin nutzt Social Media um spenden zu Sammeln
ምስል Privat

«በጥቂት ቀናት ሩብ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር አሰባስባለች»

This browser does not support the audio element.


የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለመዝናናት፣ መረጃ ለማግኘትና ከሰዎች ጋር  ያለንን መስተጋብር  ለማጠናከር  በማገልገል ላይ ይገኛሉ።አሁን አሁን ደግሞ እነዚህ  የትስስር ገጾች ሰዎችን ለመርዳት ሲውሉ ይታያሉ። የዛሬው የወጣቶች አለም ዝግጅትም ቲክ ቶክ የተባውን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በመጠቀም በጎ ተግባር በማከናወን ላይ ያለችን ወጣት በእንግድነት ጋብዟል።
ሕይወት ታደሰ ትባላለች።በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል የቲያትር ምሩቅ ስትሆን በሙያዋ ጋዜጠኛና ተዋናይት ነች። ሰዎችን መርዳት «ውስጤ ያለ ነገር ነው» የምትለው ወጣት ህይወት ከሙያዋ በተጨማሪ ሰዎችን ለመርዳት በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችም ትሳተፋለች። ወጣቷ ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ኑሮዋን በአሜሪካን ሀገር በማድረጓ ከሙያዋና ከሀገሯ ኢትዮጵያ ብትርቅም በሀገር ቤት የሚገኙ ችግረኞችን ከመርዳትና የበጎ አድራጎት ስራዎችን ከማከናወን ግን ያገዳት ነገር የለም።በመሆኑም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴን በተለይም ቲክ ቶክን በመጠቀም በቅርቡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ በመሰብሰብ በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ሕዛናት መርጃ ማዕከል ውስጥ በገንዘብ እጥረት የተነሳ የልብ ቀዶ ጥገና ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ህፃናት እንዲደርስ አድርጋለች።

ምስል Privat

«በመጀመሪያ መነሳሳት የፈጠረልኝ የመሰረት መብራቴ የሰራችው የልቡ ህሙማን ማስታወቂያ ነው።ከዚያ ልክ እንደ ጓደኛ ሆነን እንደ ግሩፕ ሆነን የምናሳልፍ ግሩፕ አለንና አማከርኳቸው።ይህንን ነገር አስቤአለሁ። እያንዳንዳችን አስር አስር ዶላር ብናዋጣ አንድ ህፃን ማሳከም እንችላለን የሚለውን ነገርኳቸው።ከዚያም በላይ ማዋጣት እንችላለን። ደስ ይለናል። ይህ የተቀደሰ ሀሳብ ነው አሉ። ወዲያውኑ ነው የጀመርነው።ከዚያ ወደ 208,550 ብር በአራት ቀናት ብቻ ሰበሰብን ማለት ነው።»ብላለች።
ወጣቷ እንደምትለው በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ እንደ ልብ ተዘዋውሮ እርዳታ ማሰባሰብ አስቸጋሪ በመሆኑ ቲክ ቶክን እንደ አማራጭ ተጠቅማለች።ይሁን እንጅ ብዙውን ጊዜ ቲክ ቶክ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማጋራት ለመዝናናትና ለዋዛ ፈዛዛ ብቻ የሚያገለግል ተደርጎ ስለሚታይ በዚህ የትስስር ገፅ የገንዘብ ማሰባሰባሰብና የእርዳታ ሀሳብ ማቅረብ ቶሎ ተቀባይነት ለማግኘት አስቸጋሪ ይመስላል።«መልካም ልብ ያላቸው ሰዎች በየትኛውም ቦታ አሉ»የምትለው ህይወት ግን ተሞክሮዋ ከዚህ የተለዬ መሆኑን ነው የምትገልፀው።

«ወደ «ሶሻል ሚዲያ» ስንሄድ ልባችን ያለንን ማንነት ነው ይዘን የምሄደው።ቲክቶክ፣ ፌስቡክም ይሁን የትኛውም ሚዲያ ላይ ስንሄድ ልባችን ውስጥ ያለንን ሃሳብ ይዘን ስለምንሄድ ቲክ ቶክ ለኔ ከባድ አልሆነም።»ብላለች። ህይወት አያይዛም ሀላፊነት ወስዶ  የሚያነሳሳ ከተገኘ በየማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ «ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በየቦታዉ አሉ።»በማለት ገልፃለች።
በቲክ ቶክ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ከመጀመሯ በፊት  ወጣቷ ከሌሎች ቅን ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ ለሚገኙና ራሳቸውን በወጉ መቆጣጠር ለማይችሉ ህሙማንም የንፅህና መጠበቂያዎችን በማሰባሰብ ወደ ሃገር ቤት ስትልክ መቆየቷንም ገልፃለች። 

ምስል Privat

ሀገር ቤት በነበረችበት ወቅት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የመጎብኘት፣ የመሳተፍና ድርጅቶቹ ልገሳ እንዲያገኙ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ሌሎችን የመወትወት ልምድ እንደነበራት የምትናገረው ወጣት ህይወት ያኔ ያየችው የድርጅቶቹ የገንዘብና የቁሳቁስ ችግር ባለችበት አሜሪካን ሀገርም የእርዳታውን ስራ እንድትቀጥል አድርጓታል።
«ውጭ ሀገር ያሉትን ሰዎች እንደመጠየቅ ላይቀል ይችላል ኢትዮጵያ እያለሁ ነገር ግን፤ሁሉንም መቄዶኒያንም እየ።ሄድኩ እጎበኝ ነበር።ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅትን፣የተለያዩ ድርጅቶችን ከባለቤቴ ጋር እየሄድን እንጎበኝ ነበር።እዚህ መጥቼ ለመቄዶኒያ «ዳይፐር»እንሰበስብ ያነሳሳኝ እዚያ እያለሁ መጀመሪያ ላይ ያየሁት ችግራቸው ነው።» ካለች በኃላ «የጎላ ነገር ባይሆንም እኔና ባለቤቴ በግል የተለያዩ  እድዳታዎችን እናደርግ ነበር።» ከዚያ በተጨማሪ እርሷና ባለቤቷ ለእርዳታ ድርጅቶቹ ሙያዊ እገዛ በመስጠትና ፌስቡክ ላይ በማስተዋወቅ እገዛ ያደርጉ እንደነበር አመልክታለች።የመጀመሪያ ልጃቸውን የልደት በዓል ክበበ ፀሀይ በተባለ የልጆች ማሳደጊያ ድርጅት ውስጥ ለህፃናቱ መፅሀፍ በማሰባሰብ ማክበራቸውንም ታስታውሳለች።   
ወጣት ህይወት ታደሰ የልጆች እናትና የቤተሰብ ሀላፊ በመሆኗ በምትኖርበት ሀገር ኑሮን ለማሸነፍ ከሚደረገው ውጣውረድና የስራ ጫና በተጨማሪ ልጅ ማሳደግም ቀላል አይደለም።ያም ሆኖ ራሷን ከችግሩ ጋር አስማምታ ሌሎችን ለመርዳት በመስራት ላይ ትገኛለች።ለዚህም የባሌቤቷና የሌሎች ቅን ሰዎች እገዛ ረድቶኛል ትላለች። 

 «አዲስ ከመሆናችን አንፃር በተለይ እኔ አሜሪካን ሀገር ከመጣሁ ገና ሁለት ዓመቴ ነው።ሶስት ልጆች አሉኝ።ከባድ ነው።ግን ካለሁበት ነገር ጋር አያይዤ መሄድ እችላለሁ።ለምሳሌ «ዳይፐሩ»ን ስሰበስብ በስልክ ነበር የምሰበስበው።ፌስቡክና የተለያዩ ሚዲያዎች« ፕሮሞት»ካደረኩኝ በኃላ ባለቤቴ ነበር የሚቀበልልኝ።»ካለች በኃላ፤ ከባለቤቷ በተጨማሪ ሌሎች ጓደኞቻቸው እገዛ እንዳደረጉም ገልፃለች። አያይዛም «እናትነት ከባድ ቢሆንም፤ ቤት ውስጥ ያለው ነገር ከባድ ቢሆንም፤ ችግሩን ለመቀነስ የተገኘውን አጋጣሚና ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለመልካም መጠቀም ነው።»ብላለች።

ምስል Privat

በቅርቡ ያሰባሰበችው ገንዘብ ለልብ ህሙማን ህፃናት ማዕከል መድረሱን ገልፃ፤ገንዘቡ የህፃናትን ልብ ለመጠገን የሚውል በመሆኑ ደስታ ፈጥሮላታል።ይህንን በጎ ተግባር ለወደፊቱም ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በስፋት የመቀጠል ዕቅድም አላት።ሌሎች ወጣቶችም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ለበጎ አላማ እንዲያውሏቸው፤ተከታዮችም ይህንን መሰሉን በጎ ተግባር በመደገፍና በማበረታት የበኩላቸውን እንዲወጡ መክራለች። «በጣም ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች« ሶሻል ሚዲያ»ቸውን ለመልካም ነገር ቢያውሉት።የግድ ለእርዳታ ብቻ ባይሆንም፤ለተለያየ መልካም ሀሳብ፤ የሰዎችን ተሰጦአቸውን የሚያወጡ ሰዎችን በማስተዋወቅ ሊሆን ይችላል።መልካም ነገር ቢሰሩበት፣ጥሩ ነገር ሰላም ያለው ነገር ቢያወሩበት።ከዚያ በተጨማሪ ጥሩ የሚሰሩ ሆነው ጥቂት  ተከታይ ያላቸው  አሉ።እኔ  ያን ያህል ብዙ ተከታይ የለኝም እንጅ ቢኖረኝ  ከዚያ በላይ በጣም ብዙ ገንዘብ መሰብሰብ ይቻል ነበር።እና መልካም ልብ ያላቸው ሰዎች እንዲቀላቀሉን መልዕክቴ ነው።»

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW