1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ስፖርትሰሜን አሜሪካ

ታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ በአሌክሳንደሪያ፤ቨርጂኒያ

ታሪኩ ኃይሉ
እሑድ፣ ጥቅምት 3 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካኼዱ የተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ገቢ ማሰባሰብን አላማው ያደረገ፣ ስድስተኛው ታላቁ አፍሪቃ ሩጫ አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ ተካሄደ። የውድድሩ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ፣ ዝግጅቱ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልዕ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

 ታላቁ  አፍሪቃ ሩጫ አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ ሲካሔድ የተሳተፉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካኼዱ የተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ገቢ ማሰባሰብን አላማው ያደረገ፣ ስድስተኛው ታላቁ አፍሪቃ ሩጫ አሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ ተካሄደ። ምስል Nini Legesse/Wegene Ethiopian Foundation

ታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ በአሌክሳንደሪያ፤ቨርጂኒያ

This browser does not support the audio element.

ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ/ ግራንድ አፍሪካን ረን/ በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በሁለተኛው ቅዳሜ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚካሄድ፣የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የመዝናኛ ሩጫ ነው። የታላቁ አፍሪካ ሩጫ መስራችና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጋሻው አብዛ "አብሮነት መሻል ነው" በሚል መርዕ ትላንት የተካሄደው ይኸው ዝግጅት፣ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልዕ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

"ከሩጫም በላይ ነው፤ማኀበረሰባችንን ማገናኘት፣ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአትሌቲክስ ስፖርት ነውና፣ እንደ መሰባሰቢያ መድረክ አገልግሎ፣ ሁላችንም ተሰብስበን በዓላችንን የምናከብርበት፣ በስራ ዓለም ደግሞ ብዙ አንገናኝም፣ብዙ ኢትዮጵያኖች አለንና መገናኘት የምንችልበት መድረክ ሆኖ፣ በተለይም እንዲህ እንቁ  የሆኑ አትሌቶቻችንም ዕንቁ የሆኑ የማኀበረሰባችን አካሎችና በአርቱም በኪነጥበብም ዙሪያ፣ ብርቅዬ አትሌቶች ጋር ቅዳሜ አብሮ ማሳለፍ መቻሉ ትልቅ ነገር ነው።"

በአሜሪካ የሚገኘው ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማኀበር ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን ችግረኞች

በስፖርቱ ዘርፍ፣ የማራቱን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና ሌሎች እውቅ የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶች በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

የበጎ አድራጎት ድጋፍ

ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ባዘጋጃቸው ሁነቶች ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ አድርጓል።

ታላቁ አፍሪካ ሩጫ መስራችና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጋሻው አብዛ ውድድሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልዕ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።ምስል Nini Legesse/Wegene Ethiopian Foundation

ዘንድሮም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግረኛ ቤተሰቦችን ከድህነት ለማውጣት ለሚንቀሳቀሰው፣"ወገኔ የኢትዮጵያዊያን ማኀበር" ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መካኼዱን፣የማኀበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኒኒ ለገሰ ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል።

ችግረኛ ቤተሰቦችን ለመደገፍ የተነሳው ወገኔ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ

"ግራንድ አፍሪካን ረን፣ዘንድሮ ወገኔን ስለመረጠ፣ የድጋፍ አጋር አድርጎን  ሩጫው ላይ ወገኔ ደግሞ የወጣት ክበብ አባሎቻችንን አንቀሳቅሰን፣ደጋፊዎቻችንን አንቀሳቅሰን፣ሯጮች የአቅማቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ተመቻችቶልናል።"

የአፍሪቃ ኢምፓክት ሽልማት

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከጎዳና ላይ ሩጫው ጎን ለጎን፣ኖቫ ኮኔክሽንስ የሚያዘጋጀው፣ የጎርጎሮሣዊው 2024 አፍሪካ ኢምፓክት ሽልማት በዛሬው ዕለት ይካሄዳል።

ዘንድሮም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግረኛ ቤተሰቦችን ከድህነት ለማውጣት ለሚንቀሳቀሰው፣"ወገኔ የኢትዮጵያዊያን ማኀበር" ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መካኼዱን፣የማኀበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኒኒ ለገሰ ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል።ምስል Nini Legesse/Wegene Ethiopian Foundation

ይህ ዓመታዊ የዕውቅና ሽልማት፣ በአሜሪካና በአፍሪቃ በሙያቸው ታላቅ ስራ የሰሩ ግለሰቦችን ለማክበር የሚዘጋጅ ሲሆን፣በዓመቱ በስፖርት፣በስነ ጥበብ እና በሥራ ፈጠራ ዘርፎች ለማኀበረሰባቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦና ለለውጥ ላደረጉ፣ የላቀ ተሳትፎ የሚሸለሙበት መድረክ ነው።

“ገበታ ለወገኔ” በስዊዘርላን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ

ዘንድሮ በጋዜጠኝነት፣አንጋፋዋ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ፣ በስነጥበብ ዘርፍ ድምፃዊት አስቴር አወቀ፣በስፖርቱ ዘርፍ የማራቶንና እና የአምስት ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቶች አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና ጉዳፍ ጸጋዬ፣በንግድ ዘርፍ ደግሞ ርብቃ ኃይሌ ተሸላሚ ይሆናሉ ተብሏል።

ባለፉት አምስት የታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ ዝግጅቶች፣የኢትዮጵያ ብርቅዬ አትሌቶች፣ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ስለሺ ስህን፣ ሚልዮን ወልዴና ሌሎችም በክብር እንግድነት መገኘታቸውን፣ ኖቫ ኮኔክሽንስ ለዶይቸ ቨለ ከላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።

ታሪኩ ኃይሉ 

እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW