ታሪካዊው የወለጋ ሙዚየም
ዓርብ፣ ጥር 30 2017
ታሪካዊው የወለጋ ሙዚየም
ከተመሰረተ 38 ዓመታትን ያስቆጠረው የወለጋ ሙዚየም በያዝነዉ ዓመት መስከረም ወር ላይ በ10 ሚሊዩን ብር ዕድሳት ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ሙዚየሙ በኢጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ብዙ ያልተነገረላቸው የጥቁር አንበሳ ሰራዊት አባላት ስለፈጸሙት ገድል የሚዘክር ታሪክን አስቀምጠዋል፡፡ በ 1928 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ ሰራዊቶች ካቃጠሉት የኢጣሊያን ጦር አውሮፕላን መካከል፤ አንዱ የሞተር ቅሪት በሙዚየሙ መግቢያ ላይ ይገኛል፡፡
የወለጋ ሙዚየም በምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የአራቱ ወለጋ ዞኖችም ማለትም የምዕራብ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ቀሌም ወለጋ እና የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን እና ሙዚየሙ በተመሰረተበት ደርግ ዘመን አካባቢው በሚጠራበት የወለጋ ክፍል ሀገር ስር የነበሩ ሌሎች አካባቢዎችን መረጃዎች ሰብስቦ የያዘ ነው፡፡ የወለጋ ሙዚየም በ1979 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ግንባታው በወቅቱ ከህዝብ በተሰበሰበ 380,000 ብር መሠራቱን በሙዚየሙ የተጻፈው ታሪኩ ያስረዳል፡፡
ሙዚየሙ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት ተቋሙን እያስተዳደረ የሚገኘው የምስራቅ ወለጋ ዞንባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ባህልና ቱሪዚም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ባያና ሙዚየሙ ስራ ከጀመረ ከረጅም ዓመታት በኃላ በመስከረም ወር 2017 ላይ ዕድሳቱ ተጠናቆ በአዲስ መልክ አገልግሎት መስጡት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የጉብኝዎችም ቁጥርም አሁን ላይ እጨመረ እንደሚገን ወ/ሮ እመቤት ባያና አመልክተዋል፡፡
‹‹ ሙዚየሙ ተገንብቶ ከ38 ዓመታት በኃላ ነው ዕድሳት ያገኘው፡፡ በደርግ ዘመን ነው የተገነባው አድሳት ብቻም ሳይሆን መብራት አልነበረውም፡፡ አንድ ድርጅት ባደረገልን ድጋፍ አስር ሚሊን በሚደርስን ብር ታድሷል፡፡ ሙዚየሙ ከረጅም ዓመት በፊት ስራ ሲጀምር የተሰባሰቡ ቅርሶች ብቻ የያዘ በመሆኑ ሌሎች የቀሩ ህብረተሰቡ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ተጨማሪ ቅርሶችን ከየወረዳው አሰባስበን ወደ ሙዚየሙ እያስባን እንገኛለን።››
የጥቁር አንበሳ ሰራዊት ገድል
የወለጋ ሙዚየም በጣሊያ ወረራ ወቅት የጥቁር አንበሳ ጦር ሰራዊት የፈጸሙትን ገድልም መዝገቦታል፡፡ በሙዘየሙ መግቢያ ላይ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ዳግም በወረረችበት ወቅት በነቀምት አቅራቢያ የጥቁር አንበሳ ሰራዊት ካቃጠሉት 3 የኢጣሊያን አውሮፕላን መካከል የአንዱ የሞተር ቅሬት ተቀምጠዋል፡፡ የሙዚየሙ ባለሙያ ዮሰፍ ሞሲሳ እንደተናገሩት የጥቁር አንበሳ ሰራት ቡድን በጣሊያ ዳግም ወረራ ወቅት በወለጋ ውስጥ የተቋቋሙ የጦር ሰራዊት ናቸው፡፡
‹‹በ1928 ኢጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በተለያየ አቅጣጫ አድርጋ ነበር ነገር ግን በታሪክ እንደምታወቀው አልተሳካትም፡፡ በዛን ወቅት ነቀምቴን ለመያዝም ሞክራ ነበር፡፡ ሀብተ ማሪያም ኩምሳ አካባቢውን በሚስተዳድርበት በዛን ወቅት ኢጣሊያኖች በኬ ቦኔያ በሚባል ቦታ ትልልቅ የጦር አውሮፕላን ይዞ ሰፍሮ ነበር፡፡ የጥቁር አንበሳ ሰራዊትም በሰኔ 20 1928 ዓ.ም ካወደሙት 3 የኢጣሊያን አውሮፕላን መካከል የአንዱ አውሮፕኑ ሞተር ክፍል እዚህ ይገኛል፡፡››
የኩምሳ ሞሮዳና አብድሳ አጋ ታሪክ በሙዚየሙ ተቀምጠዋል
ከ1881 ዓ.፣ም ጀምሮ ለ35 ዓመታት ወለጋን ማስተዳደራቸውን በመዚየሙ ውስጥ የተብራራው ኩምሳ ሞሮዳ ከ1881 አስከ 1916 ዓ.ም ሲገለገሉባቸው ነበሩት ቁሳቀሶችና ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር የተጻጻፉት የተለያዩ ደብዳቤዎች በመዚየሙ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም ወለጋ ውስጥ የማህበረሰቡን የዕድ ጥበብ ስራዎች፣ ማህበረሰቡ ከጥንት ,ጀምሮ ሲገለገለባቸው የነበሩ ቁሳቀሶችን እና በወለጋ ውስጥ የሚገኙ ከ12 በላይ የማዕድን ዓይነቶች በዚሁ ሙዚየም ተብራርተዋል፡፡
‹‹ በዚህ ሙዚየም 1700 የሚሆኑ ቅርሶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ቅርሶች የወለጋ ህዝብ ከድሮ ጀምሮ ያለውን ባህልና ታሪክ የሚያሳዩን ናቸው፡፡ ማዕደናት በማውጣት የሚሰራቸው እንደ ብረታ ብረት ስራዎች፣ ከቆዳ፣ከእንጨት የሚሰሩና ሌሎች ዕዴ ጥበቦችን ያካተተ ነው፡፡ በወለጋ የቀድሞ አርበኞች ታሪካና ምስሎች በውስጡ የያዘ ሲሆን እንደ ጀግናው አብዲሳ አጋ እና ኩምሳ ሞሮዳ ታሪክ እና ብዙ ነገሮችን በውስጡ ይዟል፡፡›› የወለጋ ሙዚየም በ‹‹ኤም‹‹ እና ‹‹ዳቢሊው›› የኢንግሊዘኛ ፊደል ቅርጽ የተገነባ ሲሆን ድዛይኑ በጀመርን ሀገር እንደተሰራ በሙዚየሙ ውስጥ ተጽፎ ይገኛል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ