1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2016

በዚህ ሳምንት ቅዳሜ ስለሚጀምረው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል። ኢትዮጵያዊት አትሌት ፈጣን ሰአት ስላስመዘገበችበት የዱባይ የማራቶን ሩጫ እና የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ዘገባ ይኖረናል።

አይቮሪኮስት አቢጃን ከተማ የሚገኘው የአላሳን ዋታራ ስታዲየም
የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የሚከናወንበት አይቮሪኮስት አቢጃን ከተማ የሚገኘው የአላሳን ዋታራ ስታዲየምምስል Sia Kambou/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዱባይ ማራቶንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ትናንት ድል ተቀዳጅተዋል ። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሊቨርፑል አርሰናልን በገዛ ሜዳው ከውድድሩ አሰናብቶታል ። በትናንቱ ግጥሚያ የግብጹ አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ ለሊቨርፑል አልተሰለፈም ። ግብጽ በአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ የፊታችን እሁድ ከሞዛምቢክ ጋ በምታደርገው ግጥሚያ ከሞሐመድ ሳላኅ ብዙ ትጠብቃለች ። በአስተናጋጇ ሀገር አይቮሪኮስት እና ጊኒ ቢሳዎ የፊታችን ቅዳሜ ስለሚጀምረው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግጥሚያዎች ቅድመ ዳሰሳ አድርገናል ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት ከተማ ትናንት በዱባይ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ክብረ-ወሰን በመስበር ለድል በቅታለች ። ትእግስት ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት የ2:16:07 ጊዜ በዓለማችን ከተመዘገቡ 8 ፈጣን ሴቶች መዝገብ ውስጥ ስሟ እንዲሰፍር አስችሏታል ። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች እስከ ዐሥራ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትለው የገቡ ሲሆን፤ ከመሀላቸው አራተኛ ደረጃን ይዛ ጣልቃ የገባችው ለጀርመን የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሜላት ቀጀታ ብቻ ናት ። በዚህም መሠረት፦ አትሌት ሩቲ አጋ በ2:18:09፤ እንዲሁም አትሌት ደራ ዲዳ ከሩቲበ1 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ብቻ ተቀድማ የሁለተኛ እና ሦስተኛውን ደረጃ ተቆጣጥረዋል ። 

በተመሳሳይ የወንዶች ማራቶን ፉክክርም ኢትዮጵያውያኑ ማንንም በመሀላቸው ጣልቃ ሳያስገቡ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከታትለው በመግባት ለድል በቅተዋል ። በዚህ ውድድር አትሌት አዲሱ ጎበና 2:05:01 በመሮጥ አሸናፊ ሆኗል። ኢትዮጵያውያኑ ለሚ ዱሜቻ እና ደጀኔ መገርሳም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ከአዲሱ የተበለጡትም በ19 እና 41 ሰከንዶች ነው ።  ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ስፖርታዊ ክንዋኔዎች

ሯጮች በውድድር ላይ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል Charlie Neibergall/AP/picture alliance

በቻይና ሺያሜን ማራቶን ውድድርም  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ለድል መብቃታቸውን የቻይናው ሺኑዋ ዘግቧል ። ከብርቱ ንፋስ ጋ በመታገል ጠንካራ ፉክክር በታየበት የወንዶች ውድድር፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት አሠፋ ቦኪ  2:06:46 ሮጦ በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል ። ከአሰፋ በ6 ሰከንዶች ለጥቂት የተበለጠው ኬንያዊው ሯጭ ፌሊክስ ኪፕቶ 2ና በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸልሟል ።  የሞሮኮው አትሌት ዖትማኔ ኤል ጉምሪ በሦስተኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኝ ውድድሩን ያጠናቀቀው ከአሰፋ በ32 ሰከንዶች ተበልጦ ነው ።

የሴቶች ፉክክሩን፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በቀለች ጉደታ 2:22:54 ሮጣ በማጠናቀቅ በአሸናፊነት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልማለች ።  ሞሮኳዊቷ ፋጢማ ኤዛህራ ሁለተኛ  ደረጃን አግኝታለች ። የቻይናዋ ሯጭ ዣንግ ዴሹን በሦስተኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኗም ተዘግቧል ።

እግር ኳስ

የግብፅ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እና የእንግሊዙ ሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ ከመሀል ቀይ የለበሰውምስል David Blunsden/Action Plus/picture alliance

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ሦስተኛ ዙር ግጥሚያ ሊቨርፑል ትናንት አርሰናልን በገዛ ኤሚሬትስ ሜዳው 2 ለ 0 ኩም አድርጎ ከውድድሩ ውጪ አሰናብቶታል ። የግብፅ ብሔራዊ የእግር ኳስ አጥቂው ሞሐመድ ሣላኅ ባልነበረበት የትናንቱ ግጥሚያ ሊቨርፑል የበላይነትን ይዞ አጠናቋል ። ለሊቨርፑል የመጀመሪያዋን ግብ በ80ኛ ደቂቃ ላይ በገዛ መረቡ ላይ ያስቆጠረው የአርሰናሉ ጃኩብ ኪቪዮር ነው ። ኳሷን ወደ ግብ ክልሉ የላካት ግን በዕለቱ ድንቅ ብቃቱን ዐሳይቶ የነበረው የሊቨርፑሉ ተመላላላሽ ተከላካይ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ነው ። ትሬንት በትናንቱ ጨዋታ አንድ ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ የግቡ ማእዘን ላይ ነጥሮ ተጨናግፎበታል ። ሁለተኛዋን ግብ መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 95ኛ ደቂቃ ላይ ለሊቨርፑል ያስቆጠረው ሉዊስ ዲያዝ ነው ። ሉዊስ ትናንት እጅግ ጎልቶ ታይቷል ። ዳርዊን ኑኔዝም ግብ ማስቆጠር ባይችልም አርሰናል ላይ ብርቱ ጫና ፈጥሮ ተከላካዮቹን አስጨንቋል ። የፈረንሳዩ ተከላካይ ኢብራሒም ኮናቴ የምሽቱ ድንቅ ተጨዋች መሆኑን አስመስክሯል ።  የታኅሣሥ 15 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቀደም ሲል ከካራባዎ ዋንጫም የተሰናበተው አርሰናል አሁን የቀሩት ፕሬሚየር ሊጉ እና የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ግጥሚያዎች ብቻ ናቸው ።  በዚሁ የኤፍ ኤ ካፕ ሦስተኛ ዙር ግጥሚያ ዛሬ ማታ ዊጋን ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል ። ትናንትና በነበሩ ግጥሚያዎች ኖቲንግሀም ፎረስት ከብላክፑል ሁለት እኩል እንዲሁም ሉቶን ታውን ከቦልተን ጋ ያለምንም ግብ ተለያይተው ነጥብ ተጋርተዋል ። የኤፍ ኤ ካፕ ሦስተኛ ዙር ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስትያም ይቀጥላሉ ።  የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች ለ12 ዙር በጥሎ ማለፍ የሚከናወኑ ናቸው ። ከዚያም ሩብ ፍጻሜ፤ ግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ግጥሚያዎች ተደርገው ውድድሮቹ ግንቦት ወር ውስጥ ይጠናቀቃሉ ።

በርካታ አፍሪቃዊ የእግር ኳስ ተጨዋቾች በአፍሪቃ ዋንጫ ምክንያት ከኤፍ ኤ ካፕ፤ ከፕሬሚየር ሊጉ እና ሌሎች የአውጳ ሊጎች ላይ ሰሞኑን አይገኙም ። ቡድኖቹን እና ተጨዋቾቹን በተመለከተ የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ዳሰሳ አድርጓል ።

ከስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ጋ የተደረገው ሙሉ ቃለ መጠይቅ እዚህ ይገኛል

This browser does not support the audio element.

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር የፊታችን ቅዳሜ በአዘጋጅ ሀገሯ አይቮሪኮስት እና ጊኒ ቢሳዎ መካከል በሚደረገው ግጥሚያ ይጀምራል ። በነጋታው እሁድ ናይጄሪያ እና ኤኳቶሪያል ጊኒም ይጋጠማሉ ። ግብፅ ከሞዛምቢክ፤ ጋና ከኬፕ ቬርዴ ጋ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት እሁድ ዕለት ነው ። በዘንድሮ የአፍሪቃ ዋንጫ ከሚሳተፉ 24 ሃገራት መካከል የትኞቹ ይጠበቃሉ?

በማጣሪያው ማለፍ ያልቻለችው ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት በውድድሩ የሉም ። ምሥራቅ አፍሪቃን ወክላ የምትሰለፈው ብቸኛ ሀገር ታንዛኒያ ናት ። የነገ ሳምንት ከሞሮኮ ጋ ትጋጠማለች ። የምሥራቅ አፍሪቃ ቡድኖች ከውድድሩ የራቁበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ታንዛኒያስ ምን ያህል ትጠበቃለች?

ለአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ወደ እየ ሀገራቸው በማቅናት የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ እና የማንቸስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናናን ጨምሮ 31 ተጨዋቾች በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አይገኙም ። ይኼ እንግዲህ የጀርመን ቡንደስሊጋ፤ የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪኣ ላይ የሚሰሰለፉ ተጨዋቾችን ሳንቆጥር ነው ። የአፍሪቃውያኑ ተጨዋቾች አለመኖር በአውሮጳ የእግር ኳስ የሊግ ቡድኖች ላይ ምን ተጽእኖ ያሳርፋል? የትናንቱ ሊቨርፑል 2 ለ0 አርሰናልን ያሸነፈበትን የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታን መነሻ አድርገን እንቃኝ እስኪ?

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የፊታችን ቅዳሜ አይቮሪ ኮስት ውስጥ ሲጀምር ከጀርመን ቡንደስሊጋም 24 ተጨዋቾች ለአፍሪቃው ውድድር ወደየሃገሮቻቸው በመሄዳቸው በቡንደስሊጋው እንደማይኖሩ ታውቋል ። የታኅሣሥ 8 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በሌሎች አጫጭር መረጃዎች፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ላለፉት 15 ዓመታት ያገለገለው ሽመልስ በቀለ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሉን ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ አድርጓል  ። ሽመልስ ከሀገር ውጪ  ለሱዳኑ ኤልሜሪክ እና ለሊቢያው አሊቲሃድ  ተሰልፎም ተጫውቷል ። የግብጾቹ ፔትሮጄት፤ ኤል ማካሳ፤ ኤል ጉና እና ኢንፒ ቡድኖችም ሽመልስ ከተሰለባቸው ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ ። በሀገር ውስጥ ደግሞ የትውልድ ከተማው ሐዋሳ ከነማ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ተጠቃሾች ናቸው ።

እንግሊዝ ለንደን የሚገኘው ዌምብሌ ስታዲየምምስል Gary Oakley/Zumapress/picture alliance

የፈረንሳዩ ተከላካይ ራፋኤል ቫራኔ ለተደጋጋሚ ጉዳት በመዳረጉ የማንቸስተር ዩናይትድ ቆይታው አጠራጣሪ መሆኑን ተገልጿል ። ከአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ጋም ተጨዋቹ ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ተዘግቧል።  የ30 ዓመቱ ተከላካይ ምናልባትም የተጨዋች ዝውውር መስኮቱ ሳይዘጋ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሊያቀናም ይችላል ተብሏል ።

በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ስመ ጥር ዝና ካተረፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የ78 ዓመቱ ፍራንስ ቤከን ባወር ትናንት ማረፉ ተገለጸ ። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዕውቁ የኳስ ሰው ማረፉን ዛሬ ዐስታውቋል ። ቤንከንባወር በጀርመን የእግር ኳስ ታሪክ በተጨዋችነትም ሆነ በአሰልጣኝነት ዘመን የዓለም ዋንጫ ካነሱ ሦስት ጀርመናውያን መካከል አንዱ ነው ። ፍራንስ ቤከን ባወር ያረፈው ከጤና ችግር ጋ በተያያዘ መሆኑም ተዘግቧል ።  በጀርመን የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድም «ንጉሡ» በሚል ቅጽል ስም ይታወቃል ። ለጀርመን ስፖርት ታላቅ አስተዋጽዖ ያበረከተው ይህ የስፖርት ሰው በዕድሜዎቹ መገባደጃ ላይ ግን ጀርመን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2026 የዓለም ዋንጫን እንድታዘጋጅ ለማስቻል በተፈጸመ ቅሌት ውስም ስሙ ይነሳል ። 

በጀርመን እግr ኳስ ታሪክ ስመ ጥር ዝና ካተረፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የ78 ዓመቱ ፍራንስ ቤከን ባወርምስል SvenSimon/picture alliance

የእንግሊዝ  ካፕ (ካራባዎ) ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ግጥሚያ ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ ። ነገ ቸልሲ ሚድስቦሮውን ይገጥማል ። ረቡዕ ደግሞ ሊቨርፑል ፉልሀምን በሜዳው አንፊልድ ያስተናግዳል ። የመልስ ግጥሚያዎች ከሁለት ሳምንት በኋላ ይከናወናሉ ። 92 ከኤፍ ኤ ካፑ በሊቨርፑል የተሰናበተው አርሰናል የእንግሊዝ የእግር ኳስ ቡድኖች ከሚሳተፉበት ከዚህ የካራባዎ እግር ኳስ ዋንጫም ቀደም ሲል ተሰናብቷል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW