ታንዛንያ፤ አዲስዋ ፕሬዚዳንት ቃለ-መኃላ ፈፀሙ
ዓርብ፣ መጋቢት 10 2013
ማስታወቂያ
የታንዛኒያ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሙሉሁ ሃሳን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ-መሃላ ፈፀሙ። ሳሚያ ሙሉሁ ሃሳን ዛሬ የሃገሪቱ ስድስተኛ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ቃለ-መሃላዉን የፈፀሙት መዲና ዳሬ ሰላም በሚገኘው ቤተ-መንግሥት በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ አማካይነት ነዉ። ሳሚያ ሃሳን ስልጣኑን ሲረከቡ በታንዛንያ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚዳንትም ያደርጋቸዋል። የ 61 ዓመቷ አዲስዋ የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሙሉሁ ሃሳን ስልጣኑን የተረከቡት ከትናት በስትያ ረቡዕ ፕሬዚዳንት ጆን ማጊፉሊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸዉን ተከትሎ ነዉ። ሳሚያ ባለፉት አምስት ዓመታት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሃገራቸዉን አገልግለዋል፤ በቀጣይ ማጊፉሊ የተረከቡትን ሁለተኛ ዘመነ ስልጣን ተረክበዉ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ፕሬዚዳንትነት ያገለግላሉ። ታንዛንያ ከራስ ገዝዋ ዛንዚባር የሚያስተዳድሯት ፕሬዚዳንት ስታገኝ የ61 ዓመትዋ አዲስዋ ተሽዋሲ ሳሚያ ሙሉሁ ሃሳን ሁለተኛዋ ናቸዉ። ሳሚያ ሃሳን ከሕዝበኛ ከነበሩት ሟቹ ጆን ማጊፉሊ የሚለዩት በስምምነት ላይ የተመሰረተ አቋም ስላላቸዉ እንደሆነ ተዘግቦአል። አዲስዋ የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ባለትዳር እና የአራት ልጆች እናት ናቸዉ።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ