ታግተው ወይም ተማርከው የነበሩ 271 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልለ ተወላጆች ተለቀው አርባ ምንጭ ገቡ
ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ህዳሴው ግድብ የምንጣሮ ስራ ለማከናወን ሲሄዱ በታጣቂዎች “ታገቱ” የሚላቸው፣ የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ ለወታደራዊ ስልጠና ሲጓዙ “ማረክኋቸው” ያላቸው 271 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልለ ተወላጆች ተለቅቀው አርባ ምንጭ መግባታቸውን የጋዱላ ዞን አስተዳዳሪና ታግተው ነበር ወይም ተማርከው ነበር የተባሉ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
ወደ አካባቢው ተጉዘው ነበር ከተባሉ 273 ሰዎች መካከል 271ዱ ናቸው አርባምንጭ ከተማ የደረሱትም ተብሏል፡፡
ከ20 ቀናት በፊት መነሻቸውን ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋርዱላና አሌ ዞኖች አድርገው ወደ ታላቁ ህዳሴው ግድብ ለስራ ሲጓዙ ነበር የተባሉና ደብረ ማርቆስ አቅራቢያ በፋኖ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ወጣቶች ተለቅቀው ዛሬ አርባ ምንጭ ከተማ መግባታቸውን የጋርዱላ አስተዳደርና የተለቀቁ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምንጣሮ ስራ ሊያከናውኑ ወደ አካባቢው ሲንቀሳቀሱ በታጣቂዎች እንደታገቱ ሲገልፅ፣ የፋኖ ታጣቂዎች በበኩላቸው “ወጣቶቹ ለወታደራዊ ስልጠና ወደ ማሰልጠኛ ሲንቀሳቀሱ የተማረኩ” ናቸው ይላሉ፡፡
ወጣቶቹ ከ19 ቀናት በኋላ ተለቅቀው ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ አርባምንጭ ከተማ መግባታቸውን ከተለቀቁ ወጣቶች መካከል ማሙሽ ጎዳና የተባለ ወጣት አረጋግጠዋል፡፡“እኛን ወስደውን ነበር፣ ተጉዘን ነበር፣ በኋላ በፋኖ ተይዘን ነበር፣ አቆዩን በ5ኛው ሳምንት አርብ እለት ቀን 10 ሰዓት አካባቢ ለቀቁን፣ ከዚያም በእለቱ ጉዞ ጀምረን ቅዳሜ ቀን 10 ሰዓት አካባቢ አዲስ አበባ ደረስን፣ የእኛ ዋና አስተዳዳሪ ተቀበለን፣ አሁን አርባ ምንጭ ነን፡፡” ብለዋል፡፡አንድ የቅርብ ዘመዳቸው ተይዞባቸው የነበር የጋርዱላ ነዋሪ ሰዎቹ በምን መንገድ እንደተለቀቁ ባያውቁም በግልፅ ባታወቅም ወጣቶቹ እንዲለቀቁ የአካባቢው ነዋሪ ልመናና ተማፅዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ የጋርዱላ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ኩናሎ አዲስ አበባ ሄደው ወጣቶቹን መቀበላቸውን ጠቅሰው ወደቦታው ከተንቀሳቀሱት 273 ወጣቶች መካከል 271 በእጃቸው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡“በእጃችን ያሉት 271 ናቸው፣ ወደ ቦታው የተጓዙት 273 ቢሆኑም የተመለሱት 271 ናቸው”ወጣቶቹ እንዴት ተለቀቁ? ማንስ ነው የተቀበላቸው ስንል አቶ ብርሀኑን ጠይቀናቸው ነበር፡፡
“”እኛ የምናውቀው ከደቡብ ክልል፣ ከጋርዱላ ዞን፣ ከፌደራል መንግስት፣ ከአማራ ክልል አመራሮችና ከምስራቀ ጎጃም ዞን የስራ ኃላፊዎች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ጋር በመሆን በመተባበር ልጆች ሊለቀቁ ችለዋል፣ ሲለቀቁ ግን ማንም አልተረከባቸውም፣ ራሳቸው በ4 የህዝብ ትራንስፖርት ሲመጡ አዲስ አበባ ላይ ነው ያገኘናቸው፣ ያጀባቸውም የለም፣ ልጆቹን ያገኘናቸው ቅዳሜ ማታ ነው፣ አሁን አርባ ምንጭ ደርሰዋል፡፡»
ለወጣቶቹ መለቀቅ አስተዋዕኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን ሲሉ አንድ የጋርዱላም ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡አንዳንድ ቤተሰቦች አስካሁን የወጣቶቹን መለቀቅ አልሰሙም፣ ምክንያታቸው ደግሞ አብዛኛዎቹ የተለቀቁ ወጣቶች ስልካቸው አይሰራም ወይም የላቸውም፣ እንደ ጋርዱላ አስተዳዳሪ አቶ ብርሐኑ ግን ወጣቶቹ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቤተሰቦቻቸውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአማራ ክልል መንግስትም ሆነ ከፋኖ ታጣቂዎች በኩል ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
አለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ