ቴለግራም የሃሳብ ነጻነት መድረክ ወይስ የወንጀለኞች መሸሸጊያ?
ረቡዕ፣ መስከረም 22 2017
ቴሌግራም በግላዊነት ፖሊሲው ላይ ትልቅ ማሻሻያ ማድረጉን በቅርቡ አስተውቋል። ነገር ግን አዲሱ የቴሌግራም የግላዊነት ማሻሻያ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለባለስልጣናት አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ እያከራከረ ነው። አንዳንዶች የተጠቃሚን መረጃዎች ለመንግስታት ማጋራት ወንጀልን ለመዋጋት ይረዳል ሲሉ፤ በሌላ በኩል መንግስታት ዜጎቻቸውን እንዲከታተሉ እና እንዲጨቁኑ ይረዳቸዋል።በማለት ይከራከራሉ።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት፤ በአዲሱ የቴሌግራም የግላዊነት ፖሊሲ ላይ በማተኮር የተሰናዳ ነው።
ቴሌግራም በግላዊነት ፖሊሲው ላይ ትልቅ ማሻሻያ ማድረጉን በቅርቡ አስተውቋል። የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያው አሁን ለህጋዊ ጥያቄዎች ምላሽ የተጠቃሚ ውሂብን ለባለስልጣኖች ያጋራል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ900 ሚሊዮን በላይ ንቁ ተጠቃሚዎች ያሉት ቴሌግራም፤ሁለት ዋና ዋና አገልግሎቶችን ለተጠቃሚዎቹ ይሰጣል፡ አንደኛው የመልዕክት መላላኪያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የማህበራዊ ትስስር መድረክ ሆኖ ያገለግላል።
ከታዋቂ የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎች አንዱ የሆነው ቴሌግራም፡ ሚስጥራዊ ውይይቶችን ለማድረግ የሚፈቅድ ልዩ ባህሪ አለው። ይህም ሁለቱም ተጠቃሚዎች ማለትም ለኪውም ሆነ ተቀባዩ የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች መሰረዝ ይችላሉ። ዋትስ አፕ ተመሳሳይ ባህሪ የለውም።.መልዕክቶችን ሚስጥራዊ ለማድረግ ከጫፍ እስከ ጫፍ ምስጠራን/end-to-end encryption/ ይጠቀማል። ነገር ግን በመልዕክት ተቀባዩ መሳሪያ በኩል ምንም ቁጥጥር ለማድረግ አያስችልም።
ፐልሲአፒ የተባለ ዲጅታል መድረክ መስራች የሆነው አቶ ብሩክ በልሁ ለበርካታ አመታት የቴሌግራም ተጠቃሚ ነው።ብሩክ እንደሚለው ቴሌግራምን ተወዳጅ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ይህ የግላዊነት ባህሪው ነው።
ክፍት የሆነ የመረጃ ምንጭ /open source/ መጠቀሙም ቴሌግራም በተጠቃሚዎች ዘንድ ተፈላጊ ያደረገው ሌላው ባህሪ መሆኑን ይገልፃል።
ኮሜዲያን እና ፖድካስተር ፅላተ ሰለሞን ላለፉት ስምንት አመታት የቴሌግራም ተጠቃሚ ነች። ፅላተ ቴሌግራምን የመረጠችው ፋይሎችን ለረዥም ጊዜ ስለሚያስቀምጥ ነው ትላለች።
ባለሁለት ሰይፉ ቴሌግራም
ከጎርጎሪያኑ 2013 ጀምሮ ወደ መድረኩ ብቅ ያለው ቴሌግራም፤ በብዙዎች ዘንድ ከመረጃ ደህንነት አንጻር አስተማማኝ ተደርጎ ይቆጠራል። በአንድ ጊዜ እስከ 200 ሺህ አባላት ያሉት ቡድን/ግሩፕ/ መመስረት የሚያስችለው ይህ መተግበሪያ ከየትኛውም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በበለጠ ከይዘት ክትትል እጁን በማንሳት ነፃ ሀሳብ እንዲራመድ በማድረግ ይታወቃል። ይህም ከኢራን እስከ ሆንግ ኮንግ ያሉ የዲሞክራሲ ተሟጋቾች ራሳቸውን እንዲያደራጁ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል።በአንጻሩ ቴለግራም የመናገር ነፃነት ማሳያ ሳይሆን ለወንጀለኞች ምቾትን ፈጥሯል፤ በሚል ይተቻል።
በኒዮርክ የቴክኖሎጅ ከፍተኛ ህጋዊ አማካሪ የሆኑት ናታሊያ ክራፒቪያ ከሚተቹት መካከል አንዷ ናቸው።
«ወንጀለኞች ምን እንደሚያስቡ እና ለምን ቴሌግራምን በጣም እንደወደዱት ለመገመት ከባድ ነው። በእርግጥ ፓቬል መድረኩን ማራኪ አንዲሆን አድርጎ አስተዋውቆት ነበር ። ከደህንነት አንፃር ግንኙነቶቹ ግላዊ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ነው ። እንዲሁም እሱ ከመንግስታት ጋር አይተባበርም።ስለዚህ መረጃህ በእሱ ዘንድ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ነገር ግን፣ የሲቪል ማኅበራት ባለፉት ዓመታት እንዳመለከቱት ይህ እውነት አይደለም።»
ቴለግራም እና የሃሳብ ነጻነት
የ39 ዓመቱ የቴሌግራም መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፓቬል ዱሮፍ እራሱን የመናገር ነፃነት ጠበቃ አድርጎ ይመለከታል። እናም የከዚህ ቀደም የተጠቃሚዎችን ውሂብ ለመንግሥታት ለማጋራት ፈቃደኛ አልነበረም።
በጎርጎሪያኑ 2014 ዓ/ም ቪ ኮንታክት/V-Kontakte/ ከተባለው የማህበራዊ አውታረ መረብ መድረክ የዩክሬን ተጠቃሚዎችን የግል መረጃን ለሩሲያ የደህንነት ሀላፊዎች እንዲያስተላልፍ ተጠይቆ ባለመተባበሩ ይህንን ዲጅታል መድረክ ለመሸጥ ከመገደዱ ባሻገር ለስደት ተዳርጓል።በዚህ ሁኔታ የተጠቃሚዎችን መረጃበተመለከተ ከመንግስታት ጋር ባለመተባበሩ ቀደም ሲል በሩሲያ በኋላም በፈረንሳይ ችግር ገጥሞታል።
ከፍተኛ የቴክኖሎጅ አማካሪዋ ናታሊያ ክራፒቪያ ግን ይህ የዱራፍ አካሄድ ከግል ፍልስፍና የሚመነጭ እና ጉድለት ያለበት ነው ሲሉ ከአቻ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ጋር በማወዳደር ይተቻሉ።
«እንደ ፌስቡክ ጎግል ያሉ አቻ ኩባንያዎች፣ ባለፉት ዓመታት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርገዋል። ይዘትን ክትትልን እና ከመንግስታት ጋር መረጃ መጋራትን በተመለከተ የሚከተሏቸው የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች አሉ።ቴሌግራምም እንደዚህ ዓይነት ፖሊሲዎች አሉት። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ እኛ የተገነዘብነው ቴሌግራም የሚያደርገው ነገር ሁሉ በዱራፍ ግላዊ ፍልስፍና እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እንዲሁም ግላዊነት ላይ ባለው የግል አመለካከቱ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው።እኛ እንደተመለከትነው እነዚህ ተግባራዊ ያደረጓቸው አብዛኛዎቹ አመለካከቶች እና ፖሊሲዎች በጣም ጉድለት ያለባቸው ናቸው።»
አዲሱ የቴሌግራም የግላዊነት ህጎች
የቴሌግራም መስራች ፓቬል ዱሮፍ በጎርጎሪያኑ ነሐሴ 24 ቀን 2024 ዓ/ም ፓሪስ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለ እና ምርመራ ከተደረገበት ወዲህ፤ በግላዊነት ፖሊሲው ላይ ትልቅ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።
ቴሌግራም ከዚህ በፊት ለባለሥልጣናት የደንበኞቹን መረጃ አሳልፎ ይሰጥ የነበረው በሽብር ከተጠረጠሩ ብቻ ሲሆን፤በአዲሱ የቴሌግራም የግላዊነት ህግ ግን ትክክለኛ እና ህጋዊ ጥያቄ ከቀረበ የተጠቃሚዎችን የበይነመረብ አድራሻዎችን፣የስልክ ቁጥሮችን፣ መልዕክቶች እና ሌሎች መረጃዎችን ለባለስልጣናት ማጋራትን ያጠቃልላል።
ነገር ግን አምባገነን መንግሥታት ባሉባቸው ሀገራት አስተማማኝ የመረጃ መለዋወጫ ሆኖ ሲያገለግል ለቆየው ቴሌግራም፤ አዲሱ ማሻሻያ ተጠቃሚዎችን አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ስጋት አሳድሯል።
ብሩክ የቴሌግራምን የግላዊነት ፖሊሲ ማሻሻያ በሁለት መንገድ ይመለከተዋል። በአንድ በኩል ህገወጥነትን ለመከላከል በሌላ በኩል ደግሞ ለክትትል ሊውል ይችላል የሚል ስጋት አለው። በግሉ ግን የቴሌግራም የግላዊነት ፖሊሲ ማሻሻያ ምንም ተፅዕኖ እንደማያሳድርበት ገልጿል።
ፅላተ በበኩሏ ማሻያው ህገ ወጥነትን ለመቆጣጠር ፣ያልተገቡ እና ፀያፍ ይዘቶችን ለማስወገድ፣ህገ ወጥ የበይነመረብ ንግድን ለመቆጣጠር እና የእእምራዊ ንብረት ስርቆትን ለማስቀረት ይረዳል የሚል እምነት አላት። ነገር ግን «በህግ ላይ መተማመን ለሌላቸው» ጎጂ የሚሆንበት ሁኔታ እንዳለም አስረድታለች።
አዳዲስ የሰውሰራሽ አስተውሎት የይዘት ክትትል
ፖሊሲዎቹን እያዘመነ ያለው ቴሌግራም፤ ከአዳዲስ የግላዊነት ህጎች በተጨማሪ የደህንነት መጠበቂያ ስርዓቶችንም የይዘት ክትትል ማድረጊያ ዘዴዎችንም በዲጅታል መድረኩ እያካተተ ነው። ቴሌግራም አሁን ህገወጥ ይዘቶችን ለመሰረዝ የይዘት ክትትል ለማድረግ ሰውሰራሽ አስተውሎትን እና ቦቶችን እየተጠቀመ ነው። ተጠቃሚዎችም ችግር ሲያጋጥማቸው «ሪፖርት ቦት»በሚባሉት አዲሱ የቴሌግራም ማሻሻያ በኩል ማሳወቅ እና ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ። ህገወጥነትን ለመከላከል የቴሌግራም መፈለጊያ ወይም /search function/ ዘምኗል።
ይህም ቀደም ሲል የወንጀል ድርጊቶችን ይስብ ከነበረው አነስተኛ የይዘት ክትትል የተሻለ ለውጥ ተደርጎበታል።
መንግስታት ዜጎቻቸውን እንዲከታተሉ እና እንዲጨቁኑ ያደርጋል
ያምሆኖ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለመንግስት ባለስልጣናት ማጋራት ወንጀለኞችን ከመቆጣጠር አንፃር ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ ፤ለተጠቃሚዎች የሚያመጣው ጉዳት እንዳለም የቴክኖሎጅ አማካሪዋ ይስማማሉ።
«አብረን እየሰራን ካለነው አካላት ወይም ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት ብዙ እየሰማን ነው። በጣም ያሳስባቸዋል ምክንያቱም መስተጋብራቸው በእውነቱ ፣ ሙሉ በሙሉ ግላዊነቱ የተጠበቀ አይደለም።ከጫፍ እስከ ጫፍ ግላዊነታቸው የተጠበቀው ሚስጥራዊ የመልዕክት ልውውጦች ብቻ ናቸው ። ዱራፍ በእርግጥ ቁልፍ አለው።እሱ የይለፍ ቃልም አለው ። በመሰረቱ መንግሥታትም ያንን ሊያገኙ ስለሚችሉ የሰዎችን የመልዕክት ልውውጦች ማንበብ ይችላሉ።የመንግስት ጥያቄ ደግሞ ህጋዊ ሊሆን ምናልባት ደግሞ ያልተመጣጠነ እና ህገ-ወጥ ሊሆን ይችላል።ስለዚህ ለማጋራት መገደዱ በጣም አሳሳቢ ነው።በተጨማሪም የተጠቃሚዎችን ሚስጥራዊነት ያለው የግል መረጃ እንዲሰጥም ሊገደድ ይችላል።»
የቴሌግራም መስራቹ ፓቬል ዱሮፍ በአሁኑ ጊዜ በዋስ ከእስር ተለቋል። የፈረንሣይ ባለሥልጣናት ዱሮፍን ከእስር ሲፈቱ፣ ግን እንዲሁ አልነበረም።ወንጀለኞችን በማገዝ እና ከባለሥልጣናት ጋር ባለመተባበር ክስ ቀርቦበታል። መደበኛ ምርመራም እየተካሄደበት ነው።ምርመራ ከሚደረግበት ወንጄሎች ውስጥም ህገ-ወጥ ግብይቶችን የሚያመቻች መድረክን ማስተዳደር፣ በልጆች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ጽሑፎችን ማሰራጨት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ማሳለጥ፣ ማጭበርበር እና ያለፍቃድ የተመሰጠረ የመልዕክት መላላኪያ አገልግሎት መስጠት ይገኙበታል።
የዲጂታል ግላዊነት ተሟጋቾች የፈረንሳይ እርምጃ የተጠቃሚ ውሂብን አሳልፈው ባለመስጠት የዲጅታል መድረኮች ዋና ስራ አስፈፃሚዎች በሌሎች ሀገራት እንዲከሰሱ ሊያበረታታ ይችላል።በማለት ይተቻሉ።
በሌላ በኩል አዲሱ የቴሌግራም የግላዊነት መመሪያ ጥቅም እና ጉዳትም እያከራከረ ነው። አንዳንዶች የተጠቃሚን መረጃዎች ለመንግስታት ማጋራት ወንጀልን ለመዋጋት ይረዳል ሲሉ፤ በሌላ በኩል የተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፎ መስጠት መንግስታት ዜጎቻቸውን እንዲከታተሉ እና እንዲጨቁኑ ያደርጋል በማለት ይከራከራሉ።እናንተስ ምን ትላላችሁ?
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ