«ወደ ዩንቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር አልቀነሰም» ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ
ዓርብ፣ ሰኔ 6 2017
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ 90 ያህል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተዘግተዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቶቹ የተዘጉት የትምህርት ሚኒስቴርን አሰራር መከተል ያልቻሉ ናቸው። « ትምህርት ሚኒስቴር ያደረገው የምታስተምሩትን ተማሪዎች ኦንላይን አስመዝግቡ ነው። ብዙዎቹ ግን ያ ፈተና ከመጣ ወዲህ ውጤታማነታቸው በጣም ስለቀነሰ፤ አንድም የማያሳልፉ እጅግ ብዙ ስለሆኑ በራሳቸው የተውት አሉ፤ ያ ማለት እንደ መዘጋት ነው።ግን ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ ጊዜ በኋላ ተዘግታችኋል ያላቸው አንድም የሉም። አሰራሩን መከተል ያልቻሉ በራሳቸው የወጡ ናቸው» ይላሉ።
የመውጫ ፈተና መሰጠት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ « ትምህርት ተለፍቶ የሚገኝ እንጂ በማጭበርበር አይገኝም» የሚል ባህሪ በተማሪዎች ዘንድ መታየት ጀምሯል የሚሉት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ እታች ያሉ ተማሪዎች ላይም እየተሰራ እንደሆ ገልፀዋል። ለዚህም በክፍል ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ቁጥር መቀነስ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ ገልፀው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅድመ 1ኛ ወይም ኪንደር ጋርደኖች ተሰርተዋል ብለዋል።
« በየዩንቨርሲቲው የማጠናከሪያ ትምህርት የሚከታተሉ ትልቅ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች አሉ» ። በማለት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ ወደ ዩንቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥርም አልቀነሰም ይላሉ።
የመምህራን ጉዳይ
በሀገሪቱ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ከመምህራን አቅም ጋርም የተያያዘ ነው። «መምህራን ላይ የኑሮ ጫና እንደሚኖር እንረዳለን » ሲሉ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ የመምህራን አመታዊ እርካታን በተመለከተ ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ ይናገራሉ።
በአማራ ክልል የሚገኙ የተማሪዎች እጣ ፈንታ
በአማራ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ብሔራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አልወሰዱም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እስካሁን ከትምህርት ገበታቸው እንደተነጠሉ ይገኛሉ። አቶ ኮራ እንደ አንድ የትምህርት ሚኒስቴር አመራር አካል « ትምህርት ፖለቲካ መሆን እንደማይችል ሁሉም መረዳት አለበት« በማለት ችግሩ በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሊፈታ እንደማይችል በቃለ መጠይቁ ጠቁመዋል።