1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

ትምህርት ሚንስቴር ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በትምህርት ቤቶች ለምን ከለከለ?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር ከአዲሱ 2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ፣ ታብሌቶች እና ሌሎች በትምህርት ሥራ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩና እና አዋኪ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ወደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዳይገቡ በጥብቅ መከልከሉን በቅርቡ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር  አርማ
የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር አርማ

ትምህርት ሚንስቴር ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በትምህርት ቤቶች ለምን ከለከለ?

This browser does not support the audio element.

 በአሁኑ ጌዜ  ከትምህርት ወይም ከህክምና ልዩ ፍላጎቶች በስተቀር። ስልኮችን የመከልከል እርምጃ  በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ነው።ለዚህም በትምህርት ላይ  የትኩረት ማነስ ፣በትምህርት ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር እና የሳይበር ጉልበተኝነት ስጋት ለክልከላው ገፊ ምክንያቶች ናቸው።

የዲጂታል መሳሪያዎች ጠቀሜታ ለተማሪዎች 

እንደ ላፕቶፕ ፣ ታብሌቶች እና ተንቀሳቃሽ ስልኮች ያሉ ዲጂታል መሳሪያዎች   ፈጣን እና ሰፊ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ለተማሪዎች አስፈላጊዎች ናቸው። እነዚህ ዲጅታል መሳሪያዎች በበይነመረብ  መድረኮች ላይ ትብብር እና ግንኙነትን ለማጎልበት ፣ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች  የተለያዩ  አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ፣ የርቀት የትምህርት እድሎችን ለማግኘት እና የዲጅታል ግንዛቤን ለማዳበርም ያግዛሉ። ያም ሆኖ የዲጂታል መሳሪያዎች በሁለት በኩል የተሳሉ ቢለዋ  ማለት ናቸው። ምክንያቱም ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ እና በክፍል ውስጥ በትምህርት ስዓት እነዚህን ዲጅታል መሳሪያዎችን በተለይም የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ስለሚጠቀሙ የመማር ማስተማተማሩን ስራ በማወክአሉታዊ ተፅዕኖ አላቸው።በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ የሚገኙት መመህር  ዮሴፍ ጥላሁን በትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች የኤለክትሮኒክስ አጠቃቀም ላይ ችግር መኖሩን ያስረዳሉ።«ትምህርት ቤት በነበረው ነባራዊ እውነታ ተማሪዎቹ የኤለክትሮኒክስ ዕቃዎችን የሚጠቀሙት ለአላስፈላጊ ነገር ነው። ለትምህርታዊ ነገር የሚጠቀሙ ቢሆን መልካም ነበር።ምክንያቱም ከጊዜው ጋር የሚሄድ ቴክኖሎጂ ስለሆነ።ነገር ግን  ተማሪዎቹ ያሉበት የአስተሳሰብ ደረጃ ያን ያክል ያደገ ስላልሆነ ፤ ለአላስፈላጊ ነገር ነው የሚጠቀሙት ኤለክትሮኒክሶቹን።»በማለት ገልፀዋል።

ተንቀሳቃሽ ስልኮች ተማሪዎች ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ እንዳይሆን በማድረግ በትምህርት አቀባበል ላይም ተፅዕኖ አለው።ምስል፦ picture-alliance/dpa

በዲጅታል መሳሪያዎች የተማሪዎችን ትኩረት ይከፋፍላሉ

ጊዜው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የገነኑበት በመሆኑም፤ ተማሪዎች ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ከማድረግ ይልቅ ወደ እነዚህ ዲጅታል መድረኮች በመሳብ በትምህርት አቀባበል ላይም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ጉዳዮች ጥናት የሚያደርገው የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት በእንግሊዝኛው ምህፃሩ (OECD) በጎርጎሪያኑ 2024 ዓ.ም ባደረገው ጥናት በክፍል ውስጥ ለመዝናናት የዲጂታል መሳሪያዎችን ከመጠን በላይ መጠቀም በተማሪዎችን የትምህርት አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።በፈረንሳይ 58% ተማሪዎች በዲጅታል መሳሪያዎች ትኩረታቸው እንደሚከፋፈል መናገራቸውን ጥናቱ አመልክቷል።በጥናቱ ከተሳተፉ  ተማሪዎች መካከል  59 በመቶ የሚሆኑት ላፕቶፖችን፣ስልክ እና ታብሌቶች በሚጠቀሙ እኩዮቻቸው ምክንያት ትኩረታቸው መከፋፈሉን ገልፀዋል። የመምህር ዮሴፍ አስተያየት ይህንን የሚያጠናክር ነው።እሳቸው እንደሚሉት ፈተና መኮራረጅን ጨምሮ  ተማሪዎች  ትምህርታቸው ላይ እንዳያተኩሩ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን በስልኮቻቸው ያከናውናሉ። 

የተማሪዎች የተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም የትምህርት አቀባበል ብቃታቸውን የሚጎዳ ሲሆን፤ በጥናት ሊያሳልፉ የሚገባቸውን ጊዜም ይሻማል።የህዝብን የኑሮ ሁኔታ በሚያሻሽሉ የሕዝብ ፖሊሲዎች ​​ላይ የመረጃ ፣ትንተና የሚያደርገው የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (OECD)  እንደሚመክረው እንደ ተንቀሳቃሽ ስልክ  እገዳዎች ያሉ መመሪያዎች ይህንን መሰሉን  ችግር ለመቀነስ ይረዳል።ይህንን በመገንዘብ ይመስላል ሰሞኑን የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስቴር  ከአዲሱ 2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ፣ ታብሌቶች እና ሌሎች በትምህርት ሥራ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩና አዋኪ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ወደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዳይገቡ በጥብቅ መከልከሉን  አስታውቋል።እሳቸው የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ቀደም ብሎ በትምህርት ቤት ደረጃ የተንቀሳቃሽ ስልክ ክልከላ መደረጉን የገለፁት መምህር ዮሴፍ፤ ትምህርት ሚንስቴር ያወጣው መመሪያ አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአዲሱ 2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ፣ በትምህርት ቤቶች ከልክሏል። ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በዓለም አቀፍ ደረጃ ክልከላ ያደረጉ  ሀገራት የትኞቹ ናቸው?

በትምህርት ቤቶች  የተንቀሳቃሽ  ስልክእገዳ የጣሉ ሀገራት ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ ፣ጣሊያን፣ ፊንላንድ እና ስዊድን ይገኙበታል። እንደ ብራዚል፣ ማሌዥያ፣ ጋና፣ አውስትራሊያ እና ብሪታኒያ ያሉ  ሀገራት በሀገር አቀፍ  ወይም በክልል ደረጃ እገዳዎችን ተግባራዊ አድርገዋል።ብራዚል፡ በ2025 መጀመሪያ ላይ  ስልኮችን በትምህርት ቤቶች የማገድ እንቅስቃሴውን ተቀላቀለች።በብሪታንያ ምንም እንኳን ውሳኔው ብዙ ጊዜ ለየትምህርት ቤቶች የሚተው ቢሆንም፤ርእሰ መምህራን ስልክ መጠቀምን እንዲከለክሉ ፡ መመሪያው ያበረታታል። በአውስትራሊያ፡ እንደ ኒው ሳውዝ ዌልስ እና ደቡብ አውስትራሊያ ያሉ አንዳንድ ግዛቶች እገዳዎችን አስተዋውቀዋል።ስዊድን ከ1ኛ-9ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ሰዓት እንዳይጠቀሙ እገዳን ተግባራዊ አድርጋለች።ስፔን፡ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ እገዳ ስትጥል፤ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የተንቀሳቃሽ ስልኮች አጠቃቀማቸውን የሚገድብ መመሪያ አፅድቃለች።

በአሁኑ ጌዜ  ከትምህርት ወይም ከህክምና ልዩ ፍላጎቶች በስተቀር። ስልኮችን የመከልከል እርምጃ  በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ ነው።ለዚህም በትምህርት ላይ  የትኩረት ማነስ ፣በትምህርት ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር እና የሳይበር ጉልበተኝነት ስጋት ለክልከላው ገፊ ምክንያቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስትር የአሁኑን የኤለክትሮኒክስ መሳሪያዎች ክልከላ ምክንያት በውል ባይገለጽም ከጥቂት ዓመታት በፊት ኩረጃን ለመከላከል በሚል በይነመረብ ከማጥፋትን ጨምሮ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ የመልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲፈተኑ አድርጓል። መምህር ዮሴፍ አዲሱ የትምህርት ሚንስቴር መመሪያ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይገልፃሉ።

በትምህርት ቤቶች የኤለክትሮኒክስ መሳሪያዎች መከልከል ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተሻለ ትኩረትን እንዲኖራቸው ያደርጋል።ምስል፦ Hideki Yoshihara/AFLO/IMAGO

የኤለክትሮኒክስ መሳሪያዎች ክልከላ ጥቅም

በትምህርት ቤቶች ውስጥ የዲጅታል መሳሪያዎችን አዘውትሮ መጠቀም ከትኩረት መቀነስ ባሻገር በተማሪዎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ መስተጋብር ያጠፋል።ለሳይበር ጉልበተኞችም ይጋልጣል።ከዚህ አንፃር ፤በትምህርት ቤቶች የሚደረጉ የኤለክትሮኒክስ መሳሪያዎች ክልከላ በክፍል ውስጥ የተሻለ ትኩረትን ለማዳበር እና ለተማሪዎች ተጨማሪ የጥናት ጊዜ በመስጠት የተሻለ የትምህርት አፈጻጸም እና ውጤት እንዲኖር ያስችላል። በተጨማሪም እንደየሳይበር ጉልበተኝነት ያሉ በይነመረብ ላይ የሚታዩ ጎጂ ባህሪያትን ለመከላከል ይረዳል።በተማሪዎች መካከል የበለጠ የፊት ለፊት መስተጋብር እንዲኖር በማድረግ ማህበራዊ ግንኙነትን ያጠናክራል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW